በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች የድንበር አካባቢዎች የሚካሄደው ግጭት እንዳሳሰበው ኢሰመኮ ገለጸ

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ የሚከሰቱ ግጭቶች ወደ ጂቡቲ ወደብ የሚደረጉ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን አስተጓጉሏል።
የምስሉ መግለጫ, በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ የሚከሰቱ ግጭቶች ከጂቡቲ ወደብ የሚነሱ እና ወደ ወደቡ የሚሄዱ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ አስተጓጉሏል።

በአፋር እና በሶማሌ የድንበር አካባቢ እያጋጠመ ያለውን በጦር መሳሪያ የተደገፈ ግጭት እየተከታተለው መሆኑን እና እያስከተለ ያለው ጉዳት እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች የድንበር አካባቢዎች ባሉ ነዋሪዎች መካከል እና በክልሎቹ የፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭቶች በተደጋጋሚ እየተከሰቱ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳይ ሲያደርሱ የቆዩ ሲሆን፣ ከወራት በፊት በሁለቱ ወገኖች መካከል ሰላም ለማውረድ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።

ኢሰመኮ አርብ ምሽት ባወጣው መግለጫ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ስሚካሄዱ በጦር መሳሪያ የተደገፉ ግጭቶች፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ስለሚደርሱ ጉዳቶች እና መፈናቀሎች በተመለከተ አሳሳቢ የሆኑ ሪፖርቶች እየደረሱት መሆንን አመልክቷል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር በሁለቱ ክልሎች መካከል ግጭቶችን ለማስወገድ ከስምምነት ተደርሶ እንደነበር ያስታወሰው ኮሚሽኑ፣ ከግንቦት መጨረሻ ሳምንት አንስቶ በተቀሰቀሱት ግጭቶች ምክንያት በግል እና በሕዝብ ንብረቶች ላይ ጉዳቶች ስለመድረሳቸው አቤቱታዎች እና ሪፖርቶች ሲቀበል መቆየቱን ገልጿል።

የአፋር እና የሶማሌ የአስተዳደር እና የፀጥታ ባለሥልጣናት በተጠቀሰው ጊዜ በክልሎቹ የፀጥታ ኃይሎች መካከል አልፎ አልፎ ግጭቶች ተካሂደው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እና መፈናቀል መድረሱን ለኮሚሽኑ ማረጋገጣቸውን ኢሰመኮ ጠቅሷል።

በሶማሌ እና አፋር ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ባሉ ቦታዎች በሁለቱም ክልሎች ለረጅም ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ ግጭቶች እያጋጠሙ ሁለቱም ወገኖች አንዳቸውን ሌላኛቸውን ሲከሱ ቆይተዋል።

ነገር ግን ይህንን ተደጋጋሚ ግጭት ለማስቆም በክልል ባለሥልጣናት፣ በማኅበረሰብ እና በሃይማኖት መሪዎች አማካይነት በተደረገ ንግግር በቅርቡ ስምምነት ተደርሶ ዳግም ግጭት አይፈጠርም የሚል ተስፋ በሁለቱም ወገኖች በኩል ተፈጥሮ ቆይቶ ነበር።

የአፋር እና የሶማሌ ክልሎችን የሚያሳይ ካርታ

አብዛኛው አርብቶ አደር የሆነ ማኅበረሰብ በሚገኝባቸው በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ ባሉ እንቅስቃሴዎች ምክንያት በነዋሪዎች መካከል በግንቦት ወር መጨረሻ ግጭቶች ተቀስቅሰዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሁለቱም ክልሎች በኩል ግጭቱ ከነዋሪዎች ባሻገር የክልሎቹ የፀጥታ ኃይሎች ተሳትፈውበታል በሚል ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ይከሳሉ።በተጨማሪም በግጭቶቹ ከሁለቱም ወገኖች የተለያዩ ቁጥሮች የተሰጡባቸው የሰዎች ሕይወት መጥፋቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

የሶማሌ የአገር ሽማግሌ የሆኑት ሐጂ አሊ ሙሳ ሐሰን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግጭቱ ለቀናት የዘለቀ መሆኑን እና በጦር መሣሪያ የታገዘ መሆኑን በመጥቀስ “በአንድ ቀን ብቻ 15 ሰዎች መሞታቸውን” እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

በአፋር በኩል ነዋሪ የሆኑት አቶ ያሲን አህመድም ግጭቱ በታጠቁ የክልል ኃይሎች መካከል በተለያዩ አካባቢዎች ለቀናት መካሄዱን እና በውል ቁጥሩን በማያውቁት የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሁለቱም ክልል ነዋሪዎች ለግጭቱ ምክንያት የሆነው ለዘመናት የዘለቀ የይዞታ ይገባኛል እንደሆነ በመጥቀስ አንደኛው ክልል ወደ ሌላኛው ዘልቆ በመግባት ቦታዎችን የመውሰድ ፍላጎት አለው ወይም ይዟል የሚል መሆኑን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ስለግጭቱ እና ስለደረሰው ጉዳት መረጃ ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን እስካሁን በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት ትክክለኛ አሃዝ አላገኘም።

የሁለቱም ክልሎች የሕዝብ ግንኙነት እና የኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣናትም ለቀናት ስለዘለቀው ግጭት ከቢቢሲ በስልክ የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች ከሰሙ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ግጭቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ስለደረሰው ጉዳት በአሃዝ ያመለከተው ነገር የለም።

ኮሚሽኑ በሁለቱ ክልሎች በኩል ለግጭቱ በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት እንዳለ አመልክቶ፣ የተፈጠረውን ችግር በአስቸኳይ ለማስቆም ከፌደራል መንግሥቱ በኩል ተጨማሪ ጥረቶች እና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ሁሉም ወገኖች ግጭቱ እንዳይባባስ እና ሰላማዊ ሰዎች እንዳይጎዱ እንዲያደርጉ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ጥሪ አቅርበዋል።