ቦይንግ በወንጀል እንዳይከሰስ የገባው ስምምነት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ተጎጂዎች ላይ የፈጠረው ቁጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች ላይ በደረሱ አደጋዎች ሕይወታቸውን ያጡ 15 ቤተሰቦች ቦይንግ ጥፋተኝነቱን አምኖ የወንጀል ክሱ እንዲቀርለት ከአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ጋር የደረሰው ስምምነት ውድቅ እንዲደረግ የፌደራሉ ፍርድ ቤትን እየጠየቁ ይገኛሉ።
ቦይንግ ከጥቂት ዓመታት በፊት በቀረበበት የአሜሪካ ፌደራል የአቪዬሽን አስተዳደርን የማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አምኗል።
ኩባንያው ከዚህ ቀደም ከፍትህ መሥሪያ ቤቱ ጋር በወንጀል እንዳይጠየቅ አሠራሩን ለማሻሻል ገብቶ የነበረውን ስምምነት መጣሱን ተከትሎ ነው የወንጀል ክስ የቀረበበት።
ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ክሱ እንዲቀርለት 243.6 ሚሊዮን ዶላር የወንጀል ቅጣት ለመክፈል መስማማቱንም ነው የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ያስታወቀው።
የ157 ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈው ከኢትዮጵያው አደጋ በተጨማሪ ለ189 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት በሆነው የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ ተመሳሳይ አደጋ ምክንያት አውሮፕላን አምራቹ በደኅንነት ጥያቄዎች ቀውስ ውስጥ ገብቷል።
በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው አሰቃቂ በተባሉት የቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን አደጋዎች የ346 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ ለአንድ ዓመት ያህልም በዓለም ዙሪያ ያሉ እነዚህ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ዕግድ ተጥሎባቸው ነበር።
ቦይንግ ጥፋተኝነቱን በማመን ገንዘብ ለመክፈል ከፍትህ መሥሪያ ቤቱ ጋር የገባው ስምምነት በአደጋዎቹ ለተቀጠፉ ሰዎች ሙሉ ኃላፊነቱን እንዳይወስደው የሚያደርግ ለኩባንያው ያደላ “ስምምነት” ነው ሲሉ የአደጋዎቹ ሰለባዎች ቤተሰቦች ተችተዋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ጆሴፍ ኩሪያ የተሰኙ አባቷን ያጣችው ዚፖራህ ኩሪያ ስምምነቱ ቦይንግን ተጠያቂ የማያደርግ እና “ቁንጥጫ” እንደማለት ነው ስትል ገልጻዋለች።
“አጸያፊ ነው። የአሜሪካ መንግሥት ቦይንግን ለመቅጣት እርምጃ አለመውሰዱን ማየት ፈታኝ ነው” ትላለች።
“እርማችንን መቼም አናወጣም። ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነው በወንጀል እንዳይጠየቁ ስምምነት መፈጸማቸው ለምንወዳቸው ቤተሰቦቻችን ሕይወት መቀጠፍ እነማን ወይም ማን ተጠያቂ እንደሆነ ልናውቅ አንችልም” ብላለች።
ቢቢሲ በአደጋው ሰለባዎች የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች ስምምነቱን አስመልክቶ ያሰሙትን ተቃውሞ በተመለከተ ቦይንግን በጠየቀው ወቅት አስተያየቱን ባይሰጥም ከፍትህ መሥሪያ ቤቱ ጋር የደረሰውን ስምምነት ዝርዝር አረጋግጧል።

የፎቶው ባለመብት, The Washington Post / Getty Images
መጋቢት 01/2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ናይሮቢ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አሰቃቂው አደጋ የደረሰው።
በዚህ አደጋ ከ35 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎችን ሕይወት ተቀጥፏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ከመድረሱ ከስድስት ወራት በፊት ደግሞ የኢንዶኔዢያው ላየን አየር መንገድ ከመዲናዋ ጃካርታ ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ ባሕር ላይ ተከስክሶ የ189 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።
የአሜሪካ ዐቃቢያነ ሕግ ቦይንግ ለሁለቱም አደጋዎች ምክንያት የሆነው የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓትን በተመለከተ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ተቆጣጣሪዎችን አጭበርብሯል በሚልም ከሦስት ዓመታት በፊት ክስ መሥርተውበት ነበር።
ቦይንግ ቺካጎ በነበረው የፍርድ ሂደት በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ መንገደኞች ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ተስማምቶ፣ በምላሹም የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ለአውሮፕላን አምራቹ ከ737 ማክስ ማክስ 8 አውሮፕላኑ ዲዛይን ጉድለት ጋር በተያያዘ በማጭበርበር ሴራ በወንጀል እንዳይከሰስ ከለላ ሰጥቶት ነበር።
ቦይንግ የሚያመርታቸውን አውሮፕላን ምርቶች ደኅንነት እና ጥራት ለማስጠበቅ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የክትትል እና የቁጥጥር መርሃ ግብር ስምምነትም ገብቶ ነበር።
ነገር ግን የአላስካው አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በር ስምምነቱ ጊዜው ከማለፉ ከሁለት ቀናት በፊት ታኅሣሥ 26/ 2016 ዓ.ም. ተገንጥሎ ከአየር ላይ መውደቁን ተከትሎ ስምምነቱን መጣሱ ተመልክቷል።
“አደጋው ከደረሰ ከአምስት ዓመታት በኋላ ቦይንግ ኃላፊነት መውሰድ ካልቻለ እና ይልቁንም ተጠያቂ የማያደርገውን እና ለእሱ ተመራጭ የሆነውን ስምምነት ከፈረመ የደኅንነት እርምጃዎችን እንዴት ይከተላል ብለን እንመን?” ስትል ዚፖራህ ትጠይቃለች።
የአደጋዎቹ ሰለባዎች ቤተሰቦች አውሮፕላን አምራቹን ለአደጋዎቹ ተጠያቂ ለማድረግ እና የደኅንነት ደንቦችንም እንዲያከብር ለማድረግ የአሜሪካ ባለሥልጣናት “ፍላጎት የላቸውም” ሲሉ ክስ አቅርበዋል።
ቦይንግ የወንጀል ክስ እንዲመሠረትበት የአደጋው ሰለባዎች ቤተሰቦች በተደጋጋሚ ሲጠይቁ የቆዩ ቢሆንም በአዲሱ ስምምነት ቦይንግ ከዚህ ክስ ያመልጣል።
“ይህ ስምምነት በቦይንግ ከፍተኛ አመራሮች ቸልተኝነት ምክንያት ሕይወታቸው የተቀጠፈ 346 ሰዎችን ከግምት ውስጥ አያስገባም” ሲል በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ መላ ቤተሰቡን ያጣው ፖል ንጆሮጌ ያስረዳል።
ይህ የቦይንግ እና የአሜሪካ ፍትህ መሥሪያ ቤት የገንዘብ ስምምነት በአሜሪካ የፌደራል ዳኛ መጽደቅ ይጠበቅበታል።
“ስምምነቱ በቴክሳስ ሰሜናዊ ግዛት ዳኛ ኦኮነር ፊት ሲቀርብ ይህንን እንዳያጸድቁ እጠይቃቸዋለሁ” ሲልም ፖል አክሏል።
ባለቤቱ ካሮል እና ሦስት ልጆቻቸውን የስድስት ዓመቱ ራያን፣ የአራት ዓመቷ ኬሊ እና የዘጠኝ ወር ሕጻኗ ሩቢ ከአማቱ ጋር ሆነው ዘመድ ለመጠየቅ ከቶሮንቶ ወደ ናይሮቢ ሲጓዙ በነበረበት ወቅት ነው በአደጋው በአንድ ላይ ሕይወታቸውን ያጡት።
“አብራሪዎች አውሮፕላኑን ለስድስት ደቂቃ ያህል ለማብረር ምን ያህል እንደታገሉ እና ቤተሰቦቼ በምን ያህል አስፈሪ እና አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ እያሰብኩ እንቅል አልባ ሌቶችን አሳልፋለሁ። ቤተሰቦቼን ለመርዳትም አብሬያቸው አልነበርኩም” ብሏል።
“ቤተሰቦቼን የማዳኑ ኃላፊነት የቦይንግ እና የሚመለከታቸው ሰዎች ነበር” ሲልም ከአደጋው ከጥቂት ወራት በኋላ በአሜሪካ ምክር ቤት ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር።
ጠበቃው ፖል ስምምነቱን በመቃወምም የአደጋዎቹ ሰለባዎችን ቤተሰቦች በመወከል ክስ መሥርቷል።
“ከቦይንግ ጋር የተደረገው የድርድር ስምምነት ሌሎች የወንጀል ተከሳሾች ላይ ተፈጻሚ የማይሆን እና ለ346 ሰዎች ሕይወት መቀጠፍ ኩባንያውን ተጠያቂ ላለማድረግ ያላግባብ የተፈጸመ ነው። ይህ ስምምነት ለኩባንያው ያደላ እና በአሳሳች እና ወንጀል ላይ የተመሠረተ ነው” ሲልም የሕግ ባለሙያው ያስገባው ክስ አትቷል።
በ737 ማክስ 8 አውሮፕላን ላይ የደረሱት የኢትዮጵያው አየር መንገድ እና የኢንዶኔዢያ ላየን ኤር አውሮፕላን አደጋዎችን ተከትሎ ቦይንግ የአብራሪዎቹን አቅም ጥያቄ ውስጥ በማስገባት እና ጥፋቱን ወደ ሌሎች በማዛወር ትችት ሲቀርብበት ነበር።
ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት ለደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አደጋ ምክንያት የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።
በሪፖርቱ መሠረትም ለአውሮፕላኑ አደጋ ምክንያት ቦይንግ የገጠመው ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም) የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግር እንደሆነም ገልጿል።
ቦይንግ 737 ማክስ 8 ለሁለት የአውሮፕላን አደጋዎች እና ለበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ተከትሎ በዓለም ላይ ያሉ አውሮፕላኖቹ እንዳይበሩ ዕግድ ተጥሎባቸው ነበር።
በቦይንግ አስፈላጊው ማስተካካያ ተደርጎ ተገቢው ምርመራ እና ሙከራ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለት ዓመት በፊት አውሮፕላኑን ወደ አገልግሎት መመለሱን መግለጹ አይዘነጋም።












