የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ በኢትዮጵያ በተከሰከሰው አውሮፕላን ሰበብ ቦይንግ በወንጀል እንዲከሰስ ሃሳብ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ በግዙፉ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ላይ የወንጀል ክስ እንዲመሠረትበት ለአገሪቱ ፍትህ መሥሪያ ቤት ምክረ ሃሳብ አቀረበ።
ዐቃቤ ሕግ ይህን ምክረ ሃሳብ ያቀረበው ቦይንግ በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ ከተከሰከሱት አውሮፕላኖች ጋር በተያያዘ የካሳ ስምምነት መድረስ ባለመቻሉ ነው።
ከአምስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከዲዛይን ችግር ጋር በተየያዘ ምክንያት ሁለት አውሮፕላኖች ተከስክሰው 346 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ምክረ ሃሳብን ተከትሎ የአገሪቱ የፍትህ መሥሪያ ቤት በኩባንያው ላይ እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም. ድረስ ክስ የሚመሠረት እንደሆነ ውሳኔ መስጠት አለበት ተብሏል።
የቀድሞ የቦይንግ ከፍተኛ ኃላፊ እና የአየር ትራንስፖርት ደኅንነት ባለሙያ የሆኑት ኤድ ፒርሰን ከፍትህ መሥሪያ ቤቱ የሚጠበቀው ውሳኔ እጅግ በጣም ተጠባቂ ውሳኔ ይሆናል ብለዋል።
“737 ማክስ እና 787 አውሮፕላኖች ችግር አለባቸው።የአውሮፕላኖቹ ችግር ደግሞ የተቋሙ አመራር ነጸብራቅ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንግድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን መጋቢት 2011 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ከተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት መከስከሱ ይታወሳል።
ከዚህ አደጋ ከስድስት ወራት ቀደም ብሎ ተመሳሳይ አውሮፕላን በኢንዶኔዢያ ባሕር ላይ ተከስክሶ ሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
እነዚህን አደጋዎች ተከትሎ በመላው ዓለም ከ18 ወራት በላይ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደው መቆየታቸው ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት በአውሮፕላን አደጋዎቹ ሕይወታቸውን ያጡ ቤተሰቦች ዐቃቤ ሕግ ቦይንግ ላይ የ25 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲጥል እና የወንጀል ክስ እንዲመሠረትበት ጠይቀዋል።
እአአ 2021 ቦይንግ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል እንዲሁም ለሁኔታዎች ተገዢ ለመሆን ከተስማማ በኋላ ዐቃቤ ሕግ ኩባንያው ላይ ክስ እንዲመሠረት እንደማይጠይቅ ከመግባባት ተደርሶ ነበር።
ይሁን እንጂ ከአንድ ወር በፊት የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ አውሮፕን አምራቹ የገባውን ቃል አላከበረም ብሎ ነበር።
ፍትህ ቢሮ ኩባንያው በዲዛይን እና በትግበራ እንዲሁም የአሜሪካ የማጭበርበር ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም ብሎ ነበር።
ባለፈው ሳምንት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴቭ ካልሁን ከአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነበር።
በዓመት 33 ሚሊዮን ዶላር የሚከፈላቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኩባንያው ካለፈው ስህተቱ ተምሯል ቢሉም ሴናተሮቹ ግን ኩባንያው የቀድሞ ሠራተኞች ላይ ያለውን የበቀል ልማድ ማስተካከል ተስኖታል ሲሉ ተችተዋል።
የቀድሞ የቦይንግ ሠራተኞች 737 ማክስ 8፣ 787 ድሪምላይነር እና 777 ሞዴል አውሮፕላኖች ከፍተኛ የሆነ የምርት ጥራት ችግር አለባቸው ይላሉ።
737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ላይ ከደረሰው የመከስከስ አደጋ በተጨማሪ በቅርቡ ንብረትነቱ የሳውዝዌስት አየር መንገድ የሆነ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በረራ ላይ ሳለ በአደገኛ ሁኔታ ወደ ግራ እና ቀኝ ተንጦ ነበር።
የአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳደር ግንቦት 17/2016 ዓ.ም. ያጋጠመውን ክስተት እየመረመርኩ ነው ብሏል።
ሌላኛው 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ሚያዝያ 2016 ዓ.ም. ለበረራ እየተነሳ ሳለ የሞተሩ ሽፋን ተገንጥሎ ከወደቀ በኋላ ምርመራ እየተደረገ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ከጥቂት ወራት በፊት የአላስካ አየር መንገድ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን አየር ላይ ሳለ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ ተገንጥሎ መውደቁ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ደግሞ ንብረትነቱ የዩናይትድ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 777 አውሮፕላን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በከፍተኛ ፍጥነት ከፍታውን አጥቶ፣ አፍንጫውን ዘቅዝቆ በአደገኛ ሁኔታ ቁልቁል መብረሩ ተገልጾ ነበር።
አውሮፕላኑ ከፓስፊክ ውቅያኖስ ጋር ለመላተም ሰከንዶች ብቻ ሲቀሩት 775 ጫማ (236 ሜትር) ከፍታ ላይ የበረራ አቅጣጫውን አስተካክሏል ተብሏል።












