በተራራማ ስፍራ ለቀናት ጠፍቶ የነበረው ሰው በቀን 4 ሊትር ውሃ እየጠጣ ሕይወቱን ማቆየቱ ተገለጸ

ሉካስ ማክሊሽ ከቤተሰብ ጋር ሲገናኝ

የፎቶው ባለመብት, SVL Steve

በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት ለእግር ጉዞ ወጥቶ ለ10 ቀናት በተራራማ ስፍራ ጠፍቶ የነበረው ግለሰብ በቀን እስከ 4 ሊትር ውሃ እየጠጣ ሕይወቱን ማቆየቱ ተገለጸ።

ሉካስ ማክሊሽ የተባለው የ34 ዓመት ሰው በካሊፎርኒያ ሳንታ ክሩዝ ተራራማ ቦታ ለሦስት ሰዓታት የእግር ጉዞ ለማድረግ ከወጣ በኋላ ነበር ጠፍቶ የቆየው።

ማክሊሽ ተራራ በመውጣት ልምድ ያለው ቢሆንም በቅርቡ በተራራማ አካባቢው የተነሳው እሳት አቅጣጫ ጠቋሚዎችን በማውደሙ መመለሻው ጠፍቶበት 10 ቀናትን በጫካ ውስጥ ቆይቷል።

ማክሊሽ ሰኔ 3/2016 ዓ.ም. የእግር ጉዞ ለማድረግ ወጥቶ ሳይመለስ ሲቀር የቤተሰብ አባላት ለፖሊስ ጥቆማ ሰጥተው ለቀናት የቆየ ፍለጋ ሲደረግ ቆይቷል።

ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 13 ፖሊስ በአሳሽ ድሮን (ሰው አልባ አውሮፕን) ማክሊሽን ማግኘት ችሏል።

ፖሊስ በርካታ ሰዎች የማክሊሽን የድረሱልኝ ጩኸት ቢሰሙም ማክሊሽ ያለበትን ቦታ መለየት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል ብሏል።

ፖሊስ ማክሊሽ ተጎሳቁሎ እና ሰውነቱ ከስቶ ቢገኝም የደረሰበት ጉዳት ለሕይወቱ አሳጊ አይሆንም ብሏል።

ማክሊሽ ከኤቢሲ ኒውስ ጋር ባገረገው ቃለ መጠይቅ ለእግር ጉዞ ምቹ የሆነ ሱሪ እና ጫማ ተጫምቶ ለጥቂት ሰዓታት ጉዞ መውጣቱን ተናግሯል። “ባትሪ እና ተጣጣፊ መቀስ ብቻ ነበር በኪሴ የያዝኩት” ብሏል።

በ10 ቀናት ቆይታው ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ እየጠጣ እና በዱር ውስጥ ያገኛቸውን ጥቂት ፍሬዎች ሲመገብ መቆየቱን ተናግሯል።

ሉካስ ማክሊሽ በጫማው አማካይነት ውሃ እየሰበሰበ ሲጠጣ እንደነበረ ገልጿል።

“በየቀኑ እስከ 4 ሊትር ውሃ መጠጣቴን እርግጠኛ መሆን ነበረብኝ” ያለው ማክሊሽ፤ የዱር ፍሬዎችን እየለቀመ መብላቱን ጨምሮ ተናግሯል።

ፖሊስ በርካታ አባላቱን በማሰማራት ለፍለጋ ወጥተው በሕይወት ስለደረሱለት ማክሊሽ ምስጋናውን አቅርቧል።

የ10 ቀናት የዱር ቆይታው “ድካም እና ትንሽ ሕመም” ፈጥሮብኛል የሚለው ማክሊሽ፤ ከአሁን በኋላ በቅርቡ ለእግር ጉዞ ወደ ተራራ የምሄድ አይመስለኝም ብሏል።