በሩሲያ በሃይማኖት ተቋማት ላይ በተፈጸመ ጥቃት 15 የፖሊስ አባላት ተገደሉ

በሩሲያዋ ዳጊስታን ግዛት ማንነታቸው ይፋ ያልሆኑ ታጣቂዎች በፖሊስ አባላት እና በማምለኪያ ቦታዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ።
ታጣቂዎቹ በግዛቷ ማሃቻክላ እና ደርበንት ከተሞች በሚገኙ በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን እና የአይሁዶች ማምለኪያ ስፍራዎች ላይ ጥቃት ከፈተዋል።
በዚህ ጥቃት 15 የፖሊስ አባላት፣ አንድ ቄስ እና አንድ ጥበቃ መገደላቸውን የዳጊስታን ግዛት መሪ ሰርጌይ ሜሊኮቭ ተናግረዋል።
የግዛቷ ኃላፊዎች ከጥቃት ፈጻሚዎቹ መካከል 6ቱ መገደላቸውን እና ፖሊስ የተቀሩትን ለመያዝ አሰሳ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለስልጣናቱ የጥቃት ፈጻሚዎቹን ማንነት ይፋ ባያደርጉም ዳጊስታን ከዚህ ቀደም በእስላማዊ ቡድኖች ጥቃት የሚፈጸምባት ግዛት ናት።
እሁድ ሰኔ 16/2016 ዓ.ም. በተፈጸመው ጥቃት ሁለት ቤተ-ክርስቲያኖች እና ሁለት የአይሁዶች ማምለኪያ ስፍራ ዒላማ ተደርገዋል።
ማቻካላ በተባለችው ከተማ አንድ የኦርቶዶክስ ቄስ ተገድለዋል።
ማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተጋሩ እና ጥቃቱ ሲፈጸም የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ጥቁር የለበሱ እና በኃይል የታጠቁ ሰዎች የፖሊስ አባላት ላይ ሲተኩሱ አይሳይተዋል።
ደርበንት በተባለችው እና የጥንታዊ የአይሁዶች ማኅብረሰብ መገኛ በሆነችው ከተማ፤ ታጣቂዎች የአይሁዶች ማምለኪያ ስፍራን አጥቅተው በእሳት አያይዘውታል።
ጥቃቱን ተከትሎ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ግለሰቦች መካከል አንድ የአካባቢው ባለስልጣን እንደሚገኙበት ተገልጿል። ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ባለስልጣኑ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከጥቃት ፈጻሚዎቹ መካከል ሁለቱ ወንድ ልጆቻቸው ስለሆኑ ነው።
ከተቀረው ሩሲያ አንጻር አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች መኖሪያ የሆነችው ዳጊስታን አብዛኛው ነዋሪ ሙስሊም ነው።
በግዛቱ የሚንቀሳቀሰው እስላሚክ ኢሚሬት ኦፍ ዘ ካኡካሰስ የተባለ እስላማዊ ቡድን ከዚህ ቀደም በዳጊስታን እና አጎራባች በሆኑት ቼችንያ፣ አንጉሸቲአ እና ካባራዲኖ-ባልካሪያ ግዛቶች ከእአአ 2007 – 2017 ባሉት ዓመታት ጥቃት ሲፈጽም ነበር።
ከጥቂት ወራት በፊት ታጣቂዎች ከሞስኮ አቅራቢያ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ላይ ጥቃት መክፈታቸው ይታወሳል።
ለዚህ ጥቃት እስላሚክ ስቴት ኃላፊነቱን ቢወስድም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ የሃይማኖት መቻቻል እና የተለያየ ዘር ያላቸው በአንድነት የሚኖሩባት አገር በመሆኗ በጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን ዒላማ ልትደረግ የምትችል አገር አይደለችም ብለው ነበር።
የሩሲያ ባለስልጣናት ከሞስኮ አቅራቢያ የተፈጸመውን ጥቃት ያሴሩት ዩክሬን እና “የምዕራባውያን የጋራ ስብስብ” ነው የሚል እምነት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።












