ለወራት ፍጥጫ ውስጥ የቆዩት እስራኤል እና ሄዝቦላህ ወደ ለየለት ጦርነት ይገቡ ይሆን?

እስራኤላዊው ዴቪዲ ካማሪ
የምስሉ መግለጫ, እስራኤላዊው ዴቪዲ ካማሪ

የእስራኤል እና ሄዝቦላህ ፍጥጫ አይሎ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሁለቱ ኃይሎች ወደለየለት ጦርነት ለመግባት ከአፋፍ ላይ መድረሳቸው ከባድ ስጋትን ፈጥሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሄዝቦላህ እና እስራኤል ወደ ጦርነት የሚገቡ ከሆነ በቀጠናው እጅግ ከባድ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራን ያስከትላል በማለት ቢያስጠነቅቅም፤ በየዕለቱ የሄዝቦላህ ሮኬት የሚወርድባቸው እስራኤላውያን ጦርነቱ ቢጀመር መፍትሄ ይሆናል ይላሉ።

እስራኤላዊው ዴቪዲ ካማሪ ሄዝቦላህ መቀመጫውን ካደረገባት ከሌባኖስ ድንበር አቅራቢያ ያለችው የእስራኤል ከተማ ነዋሪ ናቸው።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሄዝቦላህ ሌባኖስ ሆኖ የተኮሰው ሮኬት ከዴቪድ መኖሪያ ቤት ፊት ለፊት ነበር የወደቀው።

ኪርያት ሻሞን በተሰኘችው ከተማ ላይ በተተኮሰው ሮኬት የዲቪድ መኖሪያ ቤት ላይ ጉዳት አድርሷል።

“ትውልዴ እና እድገቴ እዚሁ ነው። ሁሌም ችግር ነው። በዕለቱ፤ ሁልጊዜ ቦምብ ነው። አንድ ቀን እዚህ ብታድሪ አእምሮሽን ነው የምትስቺው” ሲሉ ለቢቢሲዋ ጋዜጠኛ ሉሲ ዊሊያምሰን ይናገራሉ።

ከሳምንታት በፊት ከቤታቸው ፊትለፊት የወደቀው የሄዝቦላህ ሮኬት በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ካደረሰው ጉዳት በተጨማሪ መኪናቸውን በእሳት አንድዷል።

የሐማስን የመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃትን ተከትሎ ሄዝቦላህ ከፍልስጤማውያን ጎን በመሰለፍ የሮኬት ጥቃቶችን በእስራኤል ላይ ሲያዘንብ ቆይቷል። በዚህ ምክንያት አብዛኛው የኪርያት ሻሞን የድንበር ከተማ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።

ከመኖሪያዬ አልወጣም ብለው በከተማዋ ከቀሩ ጥቂት እስራኤላውያን መካከል ዴቪድ አንዱ ናቸው። “በእዚህ ለ71 ዓመታት ኖሬያለሁ። በጭራሽ ከዚህ ንቅንቅ አልልም። የሠራዊት አባል ነበርኩ ምንም የምፈራው ነገር ይለም” በማለት አዛውንቱ ይናገራሉ።

እኒህ አዛውንት ከተማዋን ለቆ መሸሽ መፍትሄ አይደለም ይላሉ። እንደ እርሳቸው “ሄዝቦላህን መግጠም። ሁሉንም ሄዝቦላህ መግደል” መፍትሄ የሚሰጥ አማራጭ ነው።

እስራኤል ከቡድኑ ለሚቃጣባት ጥቃት ምላሽ በመስጠት በሌባኖስ የሚገኙ ዒላማዎችን መትታ ከፍተኛ የሄዝቦላህ አመራሮችን ገድላለች።

በዚህ ወር ሄዝቦላህ ከተለመደው በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ እስራኤል አስወንጭፏል።

ይህን ተከትሎ በሄዝቦላህ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ለመክፈት እስራኤል ዝግጅት እያደረገች እንደሆነ አንዳንድ ምልክቶች አሉ።

የኪርያት ሻሞን ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቪቻይ ስተርን ባለፈው ሳምንት ከጽ/ቤታቸው አቅራቢያ የወደቀውን የሄዝቦላህ ሮኬት እያሳዩ፤ “እዚህ መስዕዋት እንደሚሆን በግ ቁጭ ብለን ሞታችንን እየጠበቅን ነው” ይላሉ።

“በዓለማችን ላይ በየዕለቱ የዜጎቹን ሞት የሚፈቅድ አገር ያለ አይመስለኝም። እዚህ መስዕዋት እንደሚሆን በግ ቁጭ ብለን በደቡብ እስራኤል ያደረጉት አይነት ደንገተኛ ጥቃት እስኪፈጽሙ ዝም ብለን እየተጠባበቅን ነው። ይህ ጨርሶ መሆን የሌለበት ነገር ነው” ይላሉ።

ከዚህች ከተማ 160 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በተኩስ አቁም ስምምነት ቢቆም በዚህ አካባቢም ያለውን ውጥረት ሊረግብ ይችላል።

እስራኤል ደቡባዊ ሌባኖስን ስትመታ ቆይታለች።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ደቡባዊ ሌባኖስን ስትመታ ቆይታለች።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ግን ሐማስ ሙሉ በሙሉ ሳይወገድ የጋዛውን ጦርነት ጨርሶ አላቆምም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ ሐማስን ጨርሶ የማጥፋት ዕቅድ ስኬታማ የመሆኑ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።

“ሐማስን ሙሉ በሙሉ የማስወገድ ወይም የማጥፋት ዕቅድ ዜጎችን ማሳሳት ይሆናል” ሲሉ ዕቅዱ ሊሳከ የሚችል እንዳልሆነ የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ ለአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

በሌባኖስ በኩል ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ፋቲማ ቤለሃስ ከእስራኤል ደንበር 7 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ጀባል ኤል ቦታም ነዋሪ ነች። እርሷ ከምትኖርበት አካባቢ የእስራኤል ጥቃትን ሽሽት ከ90ሺህ በላይ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ስፍራ እንዲዘዋወሩ ተደርገዋል።

ፋቲማ ልክ እንደ ዴቪድ ሁሉ መኖሪያ መንደሬን ጥዬ አልሄድም ብላ በጀባል ኤል ቦታም ቀርታለች።

“የት ነው የምሄደው? የምሄድበት ዘመድ የለኝ፤ ገንዘብ የለኝ፤ እዚሁ በቤቴ በክብር መሞት ይሻለኛል። ለመብታችን ስንታገል ነው የኖርነው። ልክ እንደ ፍልስጤማውያኑ ከመኖሪያችን ተገፍተን አንወጣም” በማለት ሌባኖሲያዊቷ ትናገራለች።

ሁሴን አባላን ደግሞ በቅርቡ ነው ከሌባኖሷ የድንበር ከተማ ወደ ሌላ ስፍራ የተዘዋወረው። ሁሴን በድንበር ከተማዋ ሕይወት ጭራሽ የማይገፋ ሆኖበት እንደነበረ ይናገራል።

የስልክ እና ኤሌክትሪክ አገልግሎት በየጊዜው እንደሚቋረጥ፤ ምርት እና አገልግሎት የሚያቀርቡ የንግድ ተቋማት በየጊዜው ሥራቸውን እንደሚያቆሙ ይገልጻል።

ሁሴን እርሱ ሸሽቶ ከወጣባት መንደር በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ላለመሸሽ እዚያው መቅረታቸውን ይናገራል።

ግጭቱ በሁለቱም ድንበሮች ውስጥ ላሉ ነዋሪዎች ስጋት እና ችግር እንደሆነው ሁሉ እስራኤል እና ሄዝቦላህ ወደ ሙሉ ጦርነት ቢሸጋገሩ ከፍተኛ ቀውስ በቀጠናው ይከሰታል።

በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በሚገባ የሠለጠኑ ተዋጊዎች ባለቤት ነው። በቅርቡ የሄዝቦላ መሪ ሐሰን ናስራላህ ጦርነቱ ቢጀመር የትኛውም የእስራኤል ክፍል ከስጋት ውጪ አይሆንም ብለዋል።

በየትኛውም ሰዓት ሊቀሰቀስ የሚችለውን የጦርነት ስጋት ተከትሎ አቅሙ እና አማራጩ ያላቸው የሌባኖስ ዜጎች ወደ ሌላ አገር ለመጓዝ ሻንጣ እና ፓስፖርታቸውን አዘጋጅተው ተቀምጠዋል።

ቶም ፔሪ
የምስሉ መግለጫ, ቶም ፔሪ

በሁለቱ ወገኖች መካከል ጦርነት ቢቀሰቀስ “ማሰብ ከሚቻለው በላይ ቀውስ ይከሰታል” ሲሉ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሳስበዋል።

ዋና ፀሐፊው ሁለቱ ወገኖች ጠብ ከሚጭሩ እንቅስቃሴያቸው እንዲቆጠቡም ጠይቀዋል።

ሄዝቦላህ በጋዛ አጋሩ የሆነው ሐማስ በእስራኤል ሲደበደብ፤ ሰላማዊ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ እጄን አጣጥፌ መቀመጥ አልችልም በማለት ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሱን ቀጥሏል።

እስራኤል ደግሞ የሄዝቦላንህ ሮኬት በማስቆም በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ተፈናቃዮችን መመለስ ተስኗታል።

ቶም ፔሪ ነዋሪነቱ ከሌባኖስ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ማላኪያ ነው። ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመኖሪያ ቤቱ ከጓደኞቹ ጋር ጊዜ እያሳለፈ ሳለ ከቤቱ ደጃፍ የሄዝቦላ ሮኬት መውደቁን ይናገራል።

“የተተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ማስጠንቀቂያ እውነት ነው። ጦርነት ቢነሳ ለሁላችንም በጣም ከባድ ነው” የሚለው ቶም፤ “ከጦርነት ውጪ ግን ሌላ አማራጭ ያለን አይመስለኝም” ይላል።

ቶም፤ “ለእኛ ሞት ነው የሚመኙት [ሄዝቦላህ]። ንግግር መፍትሄ የሚያመጣ አይመስለኝም። እስራኤል ሄዝቦላህን ካላጠፋች በስተቀር እኛን ከማጥፋት ወደኋላ አይሉም” በማለት ይናገራል።