ሄዝቦላህ የጦር አዛዡን መገደል ለመበቀል በእስራኤል ላይ ከ200 በላይ ሮኬቶችን ተኮሰ

ሄዝቦላህ የጦሩ አዛዥ የሆነው ታሊብ አብዱላህ በእስራኤል ጥቃት መገደሉን ተከትሎ ጥቃቱን እንደሚያጠናክር ዝቷል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ሄዝቦላህ የጦሩ አዛዥ የሆነው ታሊብ አብዱላህ በእስራኤል ጥቃት መገደሉን ተከትሎ ጥቃቱን እንደሚያጠናክር ዝቷል።

በእስራኤል ጥቃት የተገደሉበትን የከፍተኛ አዛዦቹን ሞት ለመበቀል የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል ላይ በርካታ ሮኬቶችን በመተኮስ ጥቃት ፈጸመ።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ረቡዕ ዕለት ከ200 በላይ ሮኬቶች ከድንበር ታሻግረው መውደቃቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ የእሳት አደጋ ከማስነሳታቸው ባሻገር በሰው ላይ ጉዳት አላደረሱም ብሏል።

ይህ ጥቃት የተፈጸመው በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ከፍተኛ ባለሥልጣን በእስራኤል የአየር ጥቃት በተገደለ የቡድኑ አዛዥ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በእስራኤል ላይ የሚፈጸመው ጥቃት መጠን፣ ኃይል እና ውድመት እንደሚጨምር ከዛቱ በኋላ ነው።

ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመ ካለፈው መስከረም በኋላ በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል በየዕለቱ የከባድ መሳሪያ የተኩስ ልውውጦች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

በዚህም ቢያንስ 88 ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ከ375 በላይ ሰዎች ሊባኖስ ውስጥ መገደላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት እና የተባበሩት መንግሥታት ገልጸዋል። ከእስራኤል በኩል ደግሞ 18 ወታደሮች እና 10 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የአገሪቱ ጦር አስታውቋል።

በድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በሰሜን እስራኤል እና በደቡብ ሊባኖስ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ተፈናቅለዋል።

ትናንት ረቡዕ ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ የተኮሳቸው ከፍተኛ መጠን ያላቸው ሮኬቶች በጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ “ታይቶ የማይታወቅ” ነው ሲሉ የእስራኤል መገናና ብዙኃን ገልጸውታል።

የእስራኤል ጦር ኃይል እንዳለው እስከ ዕኩለ ቀን ድረስ ከ170 በላይ ሮኬቶች ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተተኩሰው የተወሰኑት እንዲመክኑ ሲደረግ፣ በርካቶቹ ግን በተለያዩ ስፍራዎች ላይ ወድቀው የእሳት አደጋ እንዲፈጠር ምክንያት መሆናቸውን ገልጿል።

በምላሹም እስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን እና “የሽብርተኛ ይዞታዎችን” በአውሮፕላን እና በመድፍ መደብደቡን አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሊባኖስ መንግሥት ዜና ተቋም እንደዘገበው የእስራኤል የአየር ጥቃት አንድ ቤት አውድሞ አንድ ሰው አቁስሏል። ጨምሮም በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የጦር አውሮፕላን እና የድሮን ጥቃቶች መፈጸማቸውን አመልክቷል።

ጠዋት የጀመረው የሄዝቦላህ የሮኬት ጥቃት እስከ ከሰዓት የቀጠለ ሲሆን ከሊባኖስ የተተኮሱት የሮኬቶች ብዛትም 215 እንደሆነ ‘ሃሬትዝ’ የተባለው የእስራኤል ጋዜጣ ዘግቧል።

ሮኬቶቹ ያስነሱት እሳትም የእስራኤል “ቁልፍ ስፍራዎችን እና ተቋማትን አደጋ ላይ የጣለ” ነው ሲል የአገሪቱ የእሳት እና ነፍስ ማዳን ባለሥልጣን ገልጿል።

ሄዝቦላህ በበኩሉ ረቡዕ ዕለት በእስራኤል ላይ ቢያንስ 17 የጥቃት ዘመቻዎችን ማካሄዱን ጠቅሶ፣ ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ እስራኤል በአራት አባላቱ ላይ ለፈጸመችው “ግድያ” ምላሽ ነው ብሏል።

ቡድኑ በጥቃቱ ኢላማ ካደረጋቸው መካከልም የእስራኤል ጦር ሠራዊት ማዘዣን፣ የወታደራዊ የአየር ቅኝት ጣቢያን እና “ወታደራዊ ፋብሪካ” እንደሚገኙበት ቡድኑ ገልጿል።

የሄዝቦላህ ከፍተኛ ባለሥልጣን ማክሰኞ ምሽት ለቀብር ለተሰበሰቡ ሰዎች ባደረጉት ንግግር “እስራኤል ካለፈው ልምዷ አልተማረችም” በማለት፣ ተጨማሪ የቡድኑ መሪዎች ሰማዕት ሲሆኑ ትግሉ እየተጠናከረ እንደሚሄድ እና ቡድናቸው የሚፈጽመው ጥቃትም “በዓይነት፣ በመጠን እና በሚያደርሰው ጉዳት እየበረታ ይሄዳል” ብለዋል።

የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው የሄዝቦላህ አዛዥ እና ሦስቱ አባላቱ የተገደሉት ማክሰኞ ሌሊት በቡድኑ የዕዝ እና የመቆጣጠሪያ ማዕከል ላይ በፈጸመው የአየር ጥቃት ነው።

የተገደለው ጦር አዛዥ አብዱላህ “በደቡባዊ ሊባኖስ ካሉ የሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዦች መካከል ዋነኛው ነው” ያለው የእስራኤል ጦር፣ ግለሰቡን “ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሽብር ጥቃት በእስራኤል ሲቪሎች ላይ ያቀደ እና የፈጸመ ነው” በማለት ከሶታል።

በሊባኖስ ያሉ የደኅንነት ምንጮች ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት አብዱላህ ከእስራኤል ጋር የሚዋሰነው የደቡብ ድንበር ማዕከላዊ አካባቢ የሄዝቦላህ አዛዥ እንደነበረ እንዲሁም ሥልጣኑም የቡድኑ ዋነኛ ጦር የሆነው ‘የራድዋን ኃይል’ አዛዥ ከነበረው እና ባለፈው ጥር ወር በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደለው ዊሳም ጣዊልም የበለጠ ነው።

ባለፈው ሳምንት ከሊባኖስ በተተኮሰ ሮኬት በተነሳ የሰደድ እሳት ምክንያት በሰሜናዊ እስራኤል ከ1400 በላይ ሄክታር መሬት ከተቃጠለ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ መንግሥታቸው በሰሜን በሊባኖስ በኩል “ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ” መዘጋጀቱን ተናግረው ነበር።

አክለውም “በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በአካባቢው ደኅንነት እንዲሰፍን እናደርጋለን” ብለው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሆኑት ሌተናንት ጄኔራል ሄርዚ ሃሌቪ ጦራቸው በሄዝቦላህ ላይ “ጥቃት ለመክፈት ዝግጁ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።