የሱዳን ጦርነትን እያባባሱ ያሉት የኢራን እና የኤምሬትስ ድሮኖች

ኦምዱርማን ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አንድ ዓመት ባለፈው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የኦምዱራን ከተማ ነዋሪዎች መንቀሳቀሻ አጥተው በቤታቸው ተቀምጠው ይገኛሉ።

ኢራን እና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው የሱዳን ጦርነት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) በማቅረብ የተባበሩት መንግሥታትን የጦር ሕግ በመጣስ ሲከሰሱ ቆይተዋል።

ይህንን ክስ ለመደገፍ የቀረቡ ማስረጃዎችን ቢቢሲ ተመልክቷል።

እአአ መጋቢት 12/2024 ጠዋት ላይ የሱዳን መንግሥት ወታደሮች ባልተጠበቀ የጦር ግስጋሴያቸው ደስታቸውን እየገለጹ ነበር።ወታደሮቹ ደስታቸውን እየገለጹ የነበረው በመዲናዋ ካርቱም የሚገኘውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዋና መሥሪያ ቤት በመቆጣጠራቸው ነው።

ይህ ሕንጻ እንደ ሌሎች ከተሞች ሁሉ በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ሥር ነበር።

የመንግሥት ወታደሮች ይህንን ድል ሊቀዳጁ የቻሉት በኢራን ሰራሽ ድሮኖች እገዛ መሆኑን ቪዲዮዎች አመልክተዋል።

እንደ ሱዳን ግጭት ተቆጣጣሪ ዳይሬክተር ሱሊማን ባልዶ ከሆነ በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ የሱዳን ጦር በአየር ኃይሉ ላይ ጥገኛ ነበር።

ጦሩ የምድር ተዋጊ ስላልነበረው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) በምዕራባዊ ሱዳን የዳርፉርን እና የዋና ከተማዋን ካርቱምን አብዛኛውን ክፍል መቆጣጠር ችሎ ነበር።በመሆኑም የሱዳን ጦር አቅሙን ያሳይ የነበረው በአየር ኃይሉ አማካኝነት ነበር።

ጥር መጀመሪያ ላይም የጦሩ ድሮን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተመትቶ ሲወድቅ የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ታየ።

በኔዘርላንድስ የሰላም ድርጅት (ፓክስ) ውስጥ የድሮን ባለሙያ እንደሆኑት ዊም ሽዊዢንበርግ ከሆነ፣ የድሮኑ ስብርባሪ፣ ሞተር እንዲሁም ጭራ ሞሃጅር-6 የተባለ ኢራን ሰራሽ ድሮንን ይመስላል።

6.5 ሜትር ርዝማኔ ያለው ሞሃጅር - 6 ድሮን እስከ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል መብረር የሚችል ሲሆን በተሰጣቸው ኢላማ መሠረት ተተኳሾችን በመጣል ጥቃት መፈፀም ይችላሉ።

በዋዲ ሴዲና የጦር ሰፈር የታየው ድሮን 6.5 ሜትር ቁመት እና 10 ሜትር የክንፍ ርዝማኔ አለው።

የፎቶው ባለመብት, Planet Labs

የምስሉ መግለጫ, በዋዲ ሴዲና የጦር ሰፈር የታየው ድሮን 6.5 ሜትር ቁመት እና 10 ሜትር የክንፍ ርዝማኔ አለው።
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የድሮን ባለሙያው ሽዊዢንበርግ፣ ከካርቱም በስተሰሜን ከሚገኘው ዋዲ ሴዲና የጦር ሰፈር ድሮኑ ተመትቶ ከወደቀ ከሦስት ቀናት በኋላ በተነሳ የሳተላይት ምሥል ላይ የዚህን ድሮን ሌላ ገጽታ መለየት ችለዋል።

“እነዚህ ድሮኖች በቀላል ሥልጠና ኢላማቸውን በትክክል መለየት ስለሚችሉ ውጤታማ ናቸው” ብለዋል ሽዊዢንበርግ።

ሞሃጅር - 6 ድሮን ተመትቶ ከወደቀ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ደግሞ ሌላ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተመትቶ የወደቀ ድሮንን የሚያሳይ ቪዲዮ ወጣ።

ባለሙያው ይህንን ድሮን በአገሪቷ ውስጥ ከሚመረተውና የኢራን አባቢል - 3 ድሮን ዓይነት ከሆነው ጃዚል - 3 ድሮን ጋር አመሳክረውታል።

ጃዚል - 3 ድሮን በሱዳን ለዓመታት ጥቅም ላይ ውሏል። ነገር ግን ቢቢሲ እና ፓክስ እንደተመለከቱት በአሁኑ ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ጥር ወር ነበር።

ከዚያም በኋላ መጋቢት ወር ላይ ባለሙያው ሽዊዢንበርግ በዋዲ ሴዲና የጦር ሰፈር ላይ ከተነሳ የሳተላይት ምሥል ሌላ ዓይነት ጃዚል - 3 ድሮንን መለየት ችለዋል።

ይህም ኢራን ለሱዳን ጦር ድጋፍ እንደምታደርግ ማሳያ እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ። የሱዳን መንግሥት ምክር ቤት ግን ከኢራን የጦር መሣሪያ እንዳልተቀበለ ገልጾ ክሱን ውድቅ አድርጎታል።

“እነዚህ ድሮኖች የታጠቁት ኢላማቸውን እንዲመቱ በታዘዙ ተተኳሾች ከሆነ፣ተተኳሾች በሱዳን ስለማይመረቱ በኢራን የቀረቡ መሆናቸውን ያሳያሉ” ሲሉም ባለሙያው ያስረዳሉ።

ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይም የኢራን ቄሽም ፋርስ ኤር ንብረት የሆነው ቦይንግ 747 የመንገደኞች አውሮፕላን ከኢራን ባንዳር አባስ አየር ማረፊያ ተነስቶ ወደ ቀይ ባሕር አቅጣጫ ሲያመራ ከራዳር ዕይታ ውጭ ወጥቶ ነበር።

ከሰዓታት በኋላም ተመሳሳይ አውሮፕላን በአገሪቷ በስተምሥራቅ በምትገኘው እና የሱዳን ጦር ባለሥልጣናት መቀመጫ በሆነችው ፖርት ሱዳን አየር ማረፊያ ማረፉን የሳተላይት ምሥሎች አሳይተዋል።

በኋላ ላይም ይኸው አውሮፕላን ሲያኮበኩብ የሚያሳይ ፎቶ በኤክስ (ትዊተር) ገጽ ላይ ሲዘዋወር ታይቷል።

የቀሽም ፋርስ ኤር ቦይንግ 747 አውሮፕላን በፖርት ሱዳን

የፎቶው ባለመብት, X @SudanSena

የምስሉ መግለጫ, ሱዳንሴና በተባለ የትዊተር (ኤክስ) ገጽ ላይ የተጋራውና ቦታው ፖርት ሱዳን አየር ማረፊያ እንደሆነ በቢቢሲ የተለየው ምሥል የጦር መሣሪያ ሲጓጓዝ እንደነበር አመልክቷል።

አውሮፕላኑ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ለአምስት ጊዜ ያህል በረራ አድርጓል።ይህም ኢራን ሠራሽ ድሮኖች ጥቅም ላይ ከዋሉበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ቄሽም ፋርስ ኤር በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም የኢራን ዋነኛ አጋር ለሆነችው ሶሪያ የጦር መሣሪያዎችን እና ተዋጊዎችን በማጓጓዝ በቀረቡበት በርካታ ክሶች ምክንያት በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎበታል።

የእያንዳንዱ ወገን ዓላማ . . .

ሱዳን በሳዑዲ አረቢያ እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ከኢራን ጋር ያላት ግንኙነት 2016 ላይ ከማብቃቱ በፊት በወታደራዊ ትብብር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ግንኙነት ነበራት።

ሱሊማን ባልዶ እንደሚሉትም በርካታ የሱዳን የጦር መሣሪያዎች በኢራን ሞዴል በአገር ውስጥ የተሠሩ ናቸው።

የአሁኑ ጦርነት ከጀመረ ወዲህ ደግሞ የሱዳን መንግሥት ከቴህራን ጋር አዲስ ግንኙነት ጀምሯል።

በዚህ ጦርነት እያንዳንዱ ወገን የየራሱ ዓላማ እንዳለው ባልዶ ይናገራሉ።

“ኢራን በቀጠናው ወሳኝ መሠረት እንዲኖራት ትፈልጋለች።ስትራቴጂካዊ ቦታ ካገኘችም በጣም ዘመናዊ እና በርካታ ድሮኖችን ታቀርባለች” ብለዋል።

ቢቢሲ የሱዳን ጦር፣ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ቄሽም ፋርስ ኤር በቀረበባቸው ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ ቢያቀርብም መልስ አላገኘም።

ሆኖም የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ማሊክ አጋር ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ “ከማንም አካል የተቀበልነው የጦር መሣሪያ የለም። የጦር መሣሪያ በጥቁር ገበያ ይገኛል።” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህ በኤክስ (ትዊተር) ላይ የተጋራው ፎቶ 'ዛጂል 3' ድሮን የሚያሳይ መሆኑን በፓክስ ድርጅት የሚሰሩት የድሮን ባለሙያ ተናግረዋል

የፎቶው ባለመብት, @RapidSupportSdn

የምስሉ መግለጫ, ይህ በኤክስ (ትዊተር) ላይ የተጋራው ፎቶ 'ዛጂል - 3' ድሮን የሚያሳይ መሆኑን በፓክስ ድርጅት የሚሠሩት የድሮን ባለሙያ ተናግረዋል።

የተመድ የጦር መሣሪያ እገዳ ችላ ተብሏል

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጦርነቱ መጀመሪያ ወቅት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል 120 ሚሊ ሜትር ሞርታር ቦምቦችን መጣል የሚችሉ ኳድኮፐር ድሮኖች መጠቀሙን የሚያሳይ መረጃ ወጥቷል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩት ምሥሎችም የሱዳን ጦር አብዛኞቹን እነዚህን ድሮኖች መትቶ መጣሉን አሳይተዋል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የጦር መሣሪያ ባለሙያ የሆኑት ብሪያን ካስትነር የእነዚህ ድሮኖች ባለቤትነትን በተመለከተ ጣታቸውን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ ቀስረዋል።

“ኤምሬትስ እንደ ኢትዮጵያ እና የመን ላሉ አጋሮቿ እና ሌሎች የግጭት ቀጠናዎች ተመሳሳይ ድሮኖችን አቅርባለች።” ብለዋል።

ኳድኮፐር ድሮኖችን

የፎቶው ባለመብት, X @war_noir

የምስሉ መግለጫ, የሱዳን ጦር ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) ሲጠቀምባቸው የነበሩ በርካታ ኳድኮፐር ድሮኖችን ይዟል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ እንደቀረበው የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ከሆነ፣ የአቪየሽን ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች የመንገደኞች አውሮፕላን የጦር መሣሪያዎችን ከኤምሬትስ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሲያጓጉዝ እንደነበር ገልጸዋል። ዩኤኢ ግን ክሱን አስተባብላለች።

አውሮፕላኑ ከሱዳን ምዕራባዊ ድንበር ጥቂት ኪሎ ሜትሮች በሚርቀው እና የአርኤስኤፍ ይዞታ በሆነው በቻድ አምድጃራስ አየር ማረፊያ ከማረፉ በፊት መነሻውን ከአቡዳቢ አየር ማረፊያ አድርጎ በናይሮቢ እና ካምፓላ አየር ማረፊያ በኩል አልፏል።

ሪፖርቱ የአካባቢውን ምንጮች እና ወታደራዊ ቡድኖች ጠቅሶ እንደገለጸው የጦር መሣሪያ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ዳርፉር እና ወደተቀረው የሱዳን ክፍል ከማምራታቸው በፊት በሳምንት ለበርካታ ጊዜ በአምጃራስ አየር ማረፊያ ከሚያርፉ አውሮፕላኖች የጦር መሣሪያዎችን ሲያወርዱ ታይተዋል።

“ኤምሬትስ በሱዳን የኢኮኖሚ ፍላጎት አላት፤ በመሆኑም በቀይ ባሕር ላይ ሁነኛ መሠረት እንዲኖራት ትፈልጋለች” ብለዋል ባልዶ።

ሆኖም ዩኤኢ አውሮፕላኖቿ የጦር መሣሪያ አጓጉዘዋል መባሉን በማስተባበል፣ ይልቁኑም የሰብዓዊ እርዳታ ሲያጓጉዙ ነበር ብላለች።

የመንግሥት ባለሥልጣናትም ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ ኤምሬትስ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ግን በጉዳዩ ላይ በቢቢሲ ጥያቄ ቢቀርብለትም ምላሽ አልሰጠም።

በእርስ በርስ ጦርነቱ ሁለቱም ወገኖች ወደ አገሪቷ የሚያስገቧቸው ድሮኖች እአአ በ2005 የወጣውን የተባበሩት መንግሥታትን የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔን የሚጥስ ነው።

ውሳኔው የጦር መሣሪያ ለሱዳን መንግሥት እና በዳርፉር ለታጠቁ ቡድኖች እንዳይቀርብ ይከለክላል።

“በተዓምር ተረፍን”

በሱዳን ሰማይ ላይ ድሮኖች መታየት ከጀመሩ በኋላ በአገሪቷ ያለው ሁኔታ በከፊልም ቢሆን ተለውጧል።

የሱዳን ጦር በተለያዩ አካባቢዎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከበባ ውስጥ የነበሩ ወታደሮቹ እንዲወጡ ማድረግ ችሏል።አርኤስኤፍም ከመዲናዋ በስተምዕራብ ካሉ የተወሰኑ አካባቢዎች ለቅቆ ወጥቷል።

ሱሊማን ባልዶ እንደሚሉት እነዚህ ለውጦች የመጡት በኢራን ሠራሽ ድሮኖች ምክንያት ነው።

ግጭት እና ተቃውሞዎች ባሉባቸው አገራት መረጃዎችን እንደሚያሰባስበው ተቋም- ኤሲኤልኢዲ ከሆነ ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ቢያንስ 16 ሺህ 650 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅትም በጦርነቱ ምክንያት 12 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጿል።

አብዱላህ ማካዊ ጦርነቱን ሽሽተው ወደ ግብፅ ከተሰደዱ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ነው። እስከ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ድረስ ይኖር የነበረው በደቡባዊ ካርቱም ነበር። በዚያን ወቅት 'የአርኤስኤፍ ነው' ካለው የድሮን ጥቃት በተዓምር መትረፉን ይናገራል።

“ሮጬ ወደ ቤት ገባሁ። የኮንክሪት ጣራ ባለው ክፍል ገብተን፤ እኔ፣ እናቴ እና አራት እህት እና ወንድሞቼ በአልጋ ሥር ተደበቅን።” ብሏል።

አብዱላህ እነርሱ ካሉበት ቀጣይ ክፍል ላይ ድሮኑ ጥቃት ሲፈፅም እንደሰሙ ተናግሯል።

“በሌላኛው ክፍል ውስጥ ብንሆን ሁላችንም እንሞት ነበር። በተዓምር ነው የተረፍነው” ብሏል።

በ2024 መጀመሪያ ላይም ግጭቱ ከዋና መዲናዋ ካርቱም ወደተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ተስፋፍቷል።

በድሮን ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው የተዘገበውም በሰሜናዊ፣በምሥራቃዊ እና በማዕከላዊ ሱዳን አካባቢዎች ነው።

አብዱላህ ወደ ግብፅ ከመሰደዱ በፊት ቤተሰቦቹን ሰላማዊ ነው ባለው ፖርት ሱዳን አካባቢ ነበር ጥሏቸው የወጣው። አሁን ላይ ግን የድሮን ጥቃቶች እዚያም ሊደርሱ እንደሚችሉ ስጋት አለው።

“የሱዳን ሕዝብ ጦርነት ሰልችቶታል። ጦርነቱ እንዲቆም እንፈልጋለን። የውጭ አገራት ለሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የጦር መሳሪያ ማቅረባቸውን ቢያቆሙ ጦርነቱ ይቆማል።” ብሏል አብዱላህ።