የሱዳኗ ወሳኝ ከተማ ኤል ፋሸር በአማጽያን እጅ ልትገባ እንደምትችል አሜሪካ አስጠነቀቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP
በምዕራባዊ ዳርፉር ትልቁ የሆነው እና በሱዳን ጦር ቁጥጥር ስር የሚትገኘው ብቸኛ ከተማ ኤል ፋሸር በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአማጽያኑ ቁጥጥር ስር ሊትወድቅ እንደምትችል በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አስጠነቀቁ።
የሱዳን ጦር እና የፍጥኖ ደራሽ ኃይሉ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገቡ 14 ወራት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ከተማዋ በአማጽያኑ ከበባ ስር ትገኛለች።
በሱዳን የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪሎ ፍጥኖ ደራሽ ኃይሉ የኤል ፋሸር ከተማን የሚቆጣጠሩ ከሆነ ዳርፉርን ከማዕከላዊ አስተዳደር ለመነጠል ይረዳናል ብለው ያምናሉ ሲሉ ለቢቢሲ ተናገረዋል።
መልዕክተኛው “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ” አገራቸው አሜሪካ ለዳርፉር የአገርነት እውቅና እንደማትሰጥ ገልጸዋል።
ዲፕሎማቱ በፍጥኖ ደራሽ ኃይል ውስጥ ኤል ፈሽርን መቆጣጠር ዳርፉርን እንደ አገር መመሥረት አድረገው የሚያስቡ አሉ ካሉ በኋላ ከዚህ “የህልም ዓለም” ሊነቁ ይገባል ሲሉ አክለዋል።
ጨምረውም ካለፈው ሚያዝያ ጀምሮ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጥቃቱን ባጠናከረባት ኤል ፋሽር ከተማ የተኩስ አቁም እንዲደረግም ጠይቀዋል።
“በፍጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከበባ ሚሊዮን ንጹሃን ሲራቡ እየተመለከትን ነው። የሚፈጸሙ የቦምብ ደብደባዎች ሆስፒታል ውስጥ ሰው እየገደሉ ነው። 45 ሺህ ነፍሰጡር ሴቶች በቂ ህክምና ብቻ ሳይሆን ለጤናማ እርግዝና የሚያስፈልግ ዕለታዊ ምግብ ለማግኘት ሲቸገሩ እየተመለከትን ነው። ኤል ፋሽር በቁጥጥር ስር የምትገባ ከሆነ ደግሞ ነገሮች እጅግ ይከፋሉ። አሰቃቂ ነገሮች ከጦርነት ሜዳ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ቦታዎችም እየሰማን ነው፤ ሰዎች ይሰደዳሉ” ብለዋል።
ይህ የአሜሪካ ማሳሰቢያ የመጣው ኤል ፋሽር ከተማን ለመቆጣጠር ደም አፋሳሽ ውጊያ ለሳምንታት ከተደረገ በኋላ ነው።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪል ሰዎች መውጪያ ያጡ ሲሆን፣ በርካቶች ርሃብ እንዳንዣበበባቸው ተገልጿል። ይህም በተከሰተው የምግብ እና የውሃ እጥረት የመጣ ነው።
ኤል ፋሽር በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የሸሹ ሰዎች መጠለያ ነበረች። አሁን ግን ወደ ጦርነት አውድማነት እየተቀየረች ነው።
ሲቪል ሰዎች የውጊያ ሰለባ እየሆኑ ሲሆን፣ ሆስፒታል እና መሰል ተቋማትም የጥቃት ኢላማ እንደደሆኑ እየተዘገበ ነው።
በከተማው አንድ የጤና ማዕከል ብቻ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በሆስፒታሉ አንድ የቀዶ ህክምና ባለሙያ ብቻ የሚገኝ ሲሆን፣ እሱም ያለ እረፍት ለመሥራት ተገዷል።
በኤል ፋሽር የሚደረገው ተደጋጋሚ ውጊያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ እያደረገ ነው። በርካቶች ደኅንነቱ የተጠበቀ ስፍራ በመፈለግ ወደ ሱዳን ምዕራባዊ ክፍል እየተመሙ ይገኛሉ።
የአሜሪካወ ዲፕሎማት ፔርሎ “ይህንን ማቆም አለብን። ይህንን ጦርነት ለማቆም መረጋጋት ይኖርብናል” ብለዋል።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ የተቀሰቀሰው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በተቀናቃኞቹ የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄኔራል አል ቡረሐን እና ጄኔራል ሐምዳን ዳጋሎ በሚመሩ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ይገኛል።












