አሜሪካ ለይታ ማዕቀብ እጥልበታለሁ ያለችው የእስራኤል ጦር ክፍል ማነው? ለምንስ የተለየ ሆነ?

የኔትዛህ ይሁዳ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Nahal Haredi

አሜሪካ ኔትዛህ ይሁዳ በተባለው የእስራኤል ጦር ክፍል ላይ ማዕቀብ ልትጥል ነው የሚል ያልተረጋገጡ ዜናዎች መውጣታቸውን ተከትሎ የቴል አቪቭ ባለሥልጣናት ቁጣቸውን እያሰሙ ነው።

አክሲዮስ የተባለው ድረ ገጽ እንደሚለው ከሆነ ይህ የጦር ቡድን በዌስት ባንክ በፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ነው ማዕቀቡ ሊጣልበት የታሰበው።

ይህ እርምጃ እውነት ከሆነ አሜሪካ በእስራኤል የጦር ክፍል ላይ የጣለችው የመጀመሪያው ማዕቀብ ይሆናል።

የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ ላይ ስለሚጣል ማዕቀብ “ምንም የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን” የእስራኤል ጦር አስታውቋል። ሻለቃው በስምሪት ላይ መሆኑን እና ለዓለም አቀፍ ሕጎች ተገዢ መሆኑንም አክሏል።

ሠራዊቱ “ውሳኔው ከተላለፈም ይገመገማል” ሲል በማለት በጦር ክፍሉ ተፈጽመዋል የሚባሉ “ያልተለመዱ ድርጊቶች ካሉ የማጣራት ሥራም ይቀጥላል” ሲልም አክሏል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ ላይ ማዕቀብ የሚጥል ከሆነ ቡድኑ ማንኛውንም ዓይነት የአሜሪካ ወታደራዊ ዕርዳታ ወይም ሥልጠና እንዳያገኝ ዕገዳ እንደሚጣልበት የአሜሪካ ምንጮች ገለጸዋል።

የኔትዛህ ይሁዳ ጸሎት እያደረገ

የፎቶው ባለመብት, AFP / Getty Images

ባለፉት ጥቂት ወራት ከአብዛኞቹ የእስራኤል ዜጎች በተለየ መልኩ የሃሬዲ አይሁዶች ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ መሆናቸው በአገሪቱ ቁጣን አባብሷል።

እስራኤል ውስጥ ለወንዶች ሦስት ዓመት እና ለሴቶች ደግሞ ሁለት ዓመት የሚቆይ ወታደራዊ አገልግሎት ግዴታ ነው።

የእስራኤሉ ፐብሊክ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የአገሪቱን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ከሆነ የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ ፍልስጤማውያን ላይ ስላደረሳቸው ጥቃቶች የምርመራ ውጤት እንዲሰጣት አሜሪካ በተደጋጋሚ እስራኤልን ጠይቃለች።

ዘገባዎቹ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቁጣ የተሞላበት ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

ቤንያሚን ኔታንያሁ ሊጣሉ የሚችሉትን ማዕቀቦች “የአይረቤነት ጥግ እና የሞራል ውድቀት” በማለት ገልጸዋቸዋል።

የእስራኤል ጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ በበኩላቸው በአገራቸው የጦር ክፍል ላይ አሜሪካ ማዕቀብ ለመጣል ማቀዷን “አደገኛ” ብለውታል።

ባለሥልጣኑ ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ዋሽንግተን ውሳኔ እንደገና እንድታጤነው ጠይቀዋል።

ሁለት ወታደሮች መጽሐፍ እያነበቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዚህ ጦርነት ወቅት በኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ ላይ ማዕቀብ መጣል “የእስራኤልን ሕጋዊነት ይጎዳል” ብለዋል ጋንትዝ።

“ጦሩ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር ለተጣጣመ ትዕዛዝ ስለሚገዛ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ምንም ምክንያት የለም” ብለዋል።

የእስራኤል የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን-ጊቪር በበኩላቸው በዋሽንግተን ለታቀደው ማዕቀብ ምላሽ እንዲሆን በአገራቸው በኩል የሚተላለፈውን የፍልስጤም አስተዳደር ገንዘብን እስራኤል እንድትወርስ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍልስጤም ባንኮች ላይ “ተከታታይ ከባድ ማዕቀቦችን እንዲያዘጋጁም” ጠይቀዋል።

ሁሉም ማዕቀብ “በፍልስጤም አስተዳደር ውስጥ ያሉ የእስራኤል ጠላቶች ላይ ያነጣጠሩ ይሆናሉ” ብለዋል ቤን-ጊቪር።

የጦር ካቢኔ ሚኒስትር የሆኑት ጋዲ ኢሰንኮት በበኩላቸው በሻለቃው ላይ ማዕቀብ መጣል “ስህተት ነው” ሲሉ ውሳኔውን ለማደናቀፍ ቃል ገብተዋል።

አክራሪ ኦርቶዶክስ የጦር አባላት

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ደግሞ እርምጃውን “ፍጹም እብደት እና የፍልስጤምን መንግሥት በእኛ ላይ ለመጫን የተደረገ ሙከራ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

የእስራኤል ተቃዋሚ መሪ ያየር ላፒድ በበኩላቸው “በመንግሥት ሕገ-ወጥ ፖሊሲ እና ፖለቲካዊ ውድቀት ምክንያት የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች የእስራኤል ጦር እና መሪዎቹ ናቸው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ኔትዛህ ይሁዳ በተባለው የእስራኤል ጦር ክፍል ላይ የሚጣለው ማዕቀብ “ስህተት በመሆኑ መወገድ አለበት" ብለዋል።

በተቃራኒው ሃሳባቸውን የሰጡት የእስራኤል ሌበር ፓርቲ መሪ ሜራቭ ሚካኤል ደግሞ የሻለቃው “መጥፎ እና ብልሹ ባህሪ ለዓመታት” እንደሚታወቅ በመግለጽ የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ እንዲፈርስ ጠይቀዋል።

የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ አባላት በሥልጠና ላይ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ አባላት በሥልጠና ላይ

በኔትዛህ ይሁዳ ውስጥ ያለው ማነው?

ብዙ የሃሬዲ አይሁዶች ወደ እስራኤል ጦር ለመቀላቀል ፍቃደኛ አይደሉም። ምክንያታቸው ደግሞ ቶራህን (የመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥ አምስት ቅዱስ መጻሕፍትን) እና ሌሎች የሃይማኖት መጻሕፍትን ያለማቋረጥ በመማር ጊዜያቸውን በማሳለፋቸው መሆኑን ዋና ራባይ ይዛክ ዮሴፍ ተናግረዋል።

ሁሉም ወጣት ሃሬዲዎች ግን ሃይማኖታዊ ኮሌጅን ስለማይቀላቀሉ አንዳንዶቹ በልዩ ሁኔታ ወደ ጦር ሠራዊቱ በመግባት ሃይማኖታዊ ጥናታቸውን ጎን ለጎን እንዲያከናውኑ ይደረጋል።

ናሃል ሃሬዲ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 1999 የተቋቋመ እና የሃሬዲ የእምነት መሪዎችን (ራባይ) በአባልነት ያቀፈ ነው።

በሃይማኖት ትምህርት የማይከታተሉ ወጣት ሃሬዲዎች በእስራኤል ጦር ውስጥ በሚያገለግሉበት ሁኔታ ላይ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከእስራኤል ጦር ጋር በትብብር ይሠራሉ።

ይህ ትብብርም በሺህዎች የሚቆጠሩ የሃሬዲ ወታደሮችን ያቀፈ የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

“የሃሬዲ አባላት አኗኗራቸውን ሳይቀይሩ በእስራኤል ጦር ውስጥ በትልቅ ቦታ እንዲያገለግሉ የሚያስችላቸውን መርሆዎች እና ገደቦችን ይከተላሉ” ብሏል ናሃል ሃረዲ።

የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ አባላት

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ አባላት

እአአ በ1999 ሰላሳ አባላት ያሉት የሃሬዲ ወታደሮችን በማቀፍ የመጀመሪያ የጦር ክፍል በማቋቋም “ነሃል ሃሬዲ”፣ “ኔትዛህ ይሁዳ” ወይም “ሻለቃ 97” የሚል ስያሜ ሰጡት ስያሜው ጦሩ እንዲቋቋም ሃሳብ ባቀረበው የሲቪል ድርጅት ስም የተሰየመ ነው።

የእስራኤል ጦርም የመጀመሪያውን የሃሬዲ ተዋጊ ሻለቃ አቋቁሞ በራማላህ እና በጄኒን አዝምቷል። 'ዬዲዮት አህሮኖት' የተባለው የዕብራይስጥ ጋዜጣ እአአ በ2019 ባወጣው ዘገባ የእስራኤል ጦር የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ ከራማላህ ወደ ጄኒን እንዲዛወር ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል።

ጋዜጣው “ተከታታይ አለመሳካቶች” ብሎ ከጠራቸው ሙከራዎች በኋላም የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሻለቃው ወደ ጄኒን “ለዘመቻ” እንደሚዛወር ተናግሯል።

ኔትዛህ ይሁዳ ብርጌድ ዓርማ

የፎቶው ባለመብት, Netzah Yehuda Brigade website

የምስሉ መግለጫ, ኔትዛህ ይሁዳ ብርጌድ ዓርማ

እአአ በታኅሣሥ 2022 እስራኤል ሻለቃውን ከዌስት ባንክ አዘዋወረቸው። ጦሩ ይህንን ያደረገው በሻለቃው ወታደሮች ባህሪ ምክንያት ነው የሚለውን አስተባብሏል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሻለቃው በሰሜን አቅጣጫ እየተንቀሳቀሰ ነው።

እአአ ከ2024 መጀመሪያ አንስቶ ደግሞ ሻለቃው በጋዛ መዋጋት መጀመሩን 'ዘ ጄሩሳሌም ፖስት' ባወጣ ዘገባ አስታውቋል።

የቀድሞ የእስራኤል ጦር አዛዥ አቪቭ ኮቻቪ እንደተናገሩት፣ የኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃን ያካተተው ክፊር ብርጌድ በሊባኖስ፣ በሶሪያ እና በጋዛ ውስጥ መዋጋት ይችላል።

በአሁኑ ጊዜ አንድ ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች በኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ ውስጥ በሥልጠና ወይም በውጊያ ላይ ይገኛሉ።

የሻለቃው ወታደሮች በእስራኤል ጦር ውስጥ ሁለት ዓመት ከ8 ወር ያገለግላሉ።

ከሴት ወታደሮችም ሆነ ከወንድ ወታደሮች ጋር ምንም ግንኙነት አይኖራቸውም። ለጸሎት እና ለሃይማኖታዊ ጥናት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚሰጣቸውም 'ኢዝራኤል ታይምስ' ዘግቧል።

ኦማር አሳድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ ለምን ማዕቀብ ለመጣል ፈለገች?

የኔትዛህ ይሁዳ ብርጌድ አባላት ጥር 2022 የ79 ዓመቱን ፍልስጤማዊ-አሜሪካዊ ኦማር አሳድን በፍተሻ ኬላ አቅራቢያ በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ገድለዋቸዋል ተብለዋል።

ወታደሮቹ እጆቻቸውን በካቴና አስረው፣ አፋቸውን አፍነው መሬት ላይ ጥለዋቸዋል ሲሉ የአሳድ ቤተሰቦች ገልጸዋል። በኋላም ሕይወታቸው አልፎ አስከሬናቸው ተጥሎ ላይ ተገኘ።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ምርመራ ካደረገ በኋላ “በውሳኔ ስህተት፣ የሰውን ክብር ዋጋ በእጅጉ የሚጎዳ ድርጊት ተፈጽሞ” እንደነበር አስታውቋል።

ድርጊቱን ተከትሎ የኔትዛህ ይሁዳ ዋና አዛዥ ማስጠንቀቂያ ደርሶታል። አዛዡ እና ወታደሮቹ ደግሞ ከቦታቸው ተነስተዋል። በወታደሮቹ ላይ የተከፈተው የወንጀል ምርመራም ለፍርድ ሳይቀርቡ ተዘግቷል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በ2022 መገባደጃ ላይ ወታደሮቹ በፍልስጤማውያን ሲቪሎች ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በኔትዛህ ይሁዳ ሻለቃ ላይ ምርመራ ማድረግ ጀምሯል። 'ሃሬትዝ' ጋዜጣ ላይ እንደዘገበው ከሆነ ምርመራው የኦማር አሳድን ግድያንም ያጠቃልላል።

ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ ጦርነት ከጀመረ ወዲህ ዩናይትድ ስቴትስ በፍልስጤማውያን ላይ በደረሰ ጥቃት ምክንያት በሦስት ሰፋሪ ግለሰቦች ላይ ማዕቀቦችን ጥላለች።

ሴናተር ፓትሪክ ሌሂይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሴናተር ፓትሪክ ሌሂይ

የአሜሪካው የሌሂይ ሕግ ምንድን ነው?

የሌሂይ ሕግ ዩናይትድ ስቴትስ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸው በተረጋገጡ የውጭ መንግሥታት ላይ ዕርዳታን ያቋርጣል ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል።

እገዳው የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር የሥልጠና ፕሮግራሞችንም ያካትታል።

ለእንደዚህ ዓይነት ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ ከቀረቡ የአሜሪካ እርዳታ እንደገና ሊቀጥል ይችላል።

የሌሂይ ሕግ “የውጭ አገር የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ መፈጸማቸው ተዓማኒነት ባለው መረጃ ከተረጋገጠ” ተፈጻሚ ይሆናል ሲል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

ምርመራው ፖለቲካዊ፣ የደኅንነት እና ሌሎች ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ያጠቃልላል።

በአሜሪካ መንግሥት ፈቃድ የተሰጣቸው አካላት ይፋዊ እና ምሥጢራዊ መረጃዎችን ይገመግማሉ።

የአሜሪካ መንግሥት “ማሰቃየትን፣ ከፍርድ ውጪ ግድያን፣ በግዳጅ መሰወርን እና በሕግ ጥላ ስር አስገድዶ መደፈርን” እንደ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይቆጥራል።

የሌሂይ ሕግም እነዚህ ወንጀሎች መፈጸማቸው ሲረጋገጡ ተግባራዊ ይሆናል።

የሌሂይ ሕግ ስያሜውን ያገኘው እአአ በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ ሕጉ እንዲወጣ በጣሩት ሴናተር ፓትሪክ ሌሂይ ነው።