ፕሬዝዳንት ባይደን ልጃቸው በወንጀል ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ የችሎቱን ውሳኔ እንደሚያከብሩ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጃቸው ሃንተር ባይደን ከጦር መሳሪያ ግዢ ጋር በተያያዘ ወንጀል ጥፋተኛ መባሉን ተከትሎ የፍርድ ቤት ውሳኔን አከብራለሁ አሉ።
አንድ ሳምንት በወሰደ የፍርድ ሂደት 12 ዳኞች የ54 ዓመቱ ሃንተር ባይደን እአአ 2018 ላይ የጦር መሳሪያ ሲገዛ በሞላው ቅጽ ላይ አደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚ አይደለሁም ሲል በመዋሸቱ ጥፋተኛ ብለውታል።
በወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ሃንተር ባይደን የእስር ቅጣት ሊተላለፍበት ይችላል።
በአሜሪካ ታሪክ በሥልጣን ላይ የሚገኝ የፕሬዝዳንት ልጅ በወንጀል ክስ ጥፋተኛ ሲባል ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ይህ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠው ጆ ባይደን በቀጣይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ለመወዳደር የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት እንዲሁም የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በወንጀል ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ ነው።
ምንም እንኳ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲሰጥ ጆ ባይደን በችሎቱ ባይገኙም የሃንተር የእንጀራ እናት የሆኑት ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን፣ የሃንተር ባለቤት፣ እህቱ እና አጎቱ ሃንተርን ለመደገፍ በፍርድ ቤት ተገኝተው ነበር።
ከችሎቱ ብይን በኋላ ባይደን የፍርድ ውሳኔው ወደተሰጠባት ዴልዌር ግዛት በማቅናት ከልጃቸው ጋር ሲተቃቀፉ ታይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ የዳኞችን ውሳኔ ተከትሎ ባወጡት መግለጫ “ፕሬዝዳንት እንዲሁም አባት ነኝ። እኔ እና ጂል ልጃችንን እንወደዋለን አሁን በደረሰበት ማንነት እንኮራለን” ካሉ በኋላ የአገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት እንደሚያከብሩ እና የችሎቱን ውሳኔ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።
ዳኞች ከቀድሞ የሃንተር ባለቤት እንዲሁም ፍቅረኛ ምስክርነትን ሰምተው የሰነድ ማስረጃዎችን የተመለከቱ ሲሆን፣ ሃንተር ባይደን ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ እፅ በከፍተኛ መጠን እየተጠቀመ ጦር መሳሪያ መታጠቁን አረጋግጠዋል።
ፍርድ ቤቱ የፕሬዝዳንቱን ልጅ በወንጀል ጥፋተኛ ካለ በኋላ በቀጣይ ሳምንታት የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሜሪካ የወንጀል ሕግ መሠረት ሃንተር ጥፋተኛ የተባለበት ወንጀል እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስር የሚያስቀጣ ቢሆንም፣ ባለሙያዎች ይህ ቅጣት ሃንተር ላይ ይተላለፋል ብለው አይጠብቁም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ ሆኖ ሳለ ጦር መሳሪያ መታጠቅ ዘብጥያ የሚያወርድ ወንጀል ቢሆንም መሰል ቅጣት መተላለፍ የሚችለው “በጣም አደገኛ በሆኑ፤ ለምሳሌ በፖሊስ ክትትል ስር በሚገኙ ሰዎች ላይ ነው” ሲሉ በሳውዝ ቴክሳስ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ድሩ ስቴቨንሰን ይናገራሉ።
መምህሩ ሃንተር ላይ “እስከ 20 ወራት የሚደርስ የእስር ቅጣት የመተላለፍ ዕድሉ ሃምሳ ሃምሳ ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ” ይላሉ።
ይሁን እንጂ ሃንተር ባይደን ከዚህ ቀደም በወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ስለማያውቅ፣ ከአደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚነት እራሱን ለማራቅ ብዙ ርቀት መጓዙ፣ አደንዛዥ ዕጽ ከተጠቀመ ዓመታት ማለፋቸውን እንዲሁም በባሕሪው አደገኛ የሚባል ግለሰብ ባለመሆኑ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲሰጥ እንደ ቅጣት ማቅለያ የሚታዩ ጉዳዮች ናቸው በማለት መምህሩ ያስረዳሉ።
እአአ 2021 ላይ በታተመ መጽሐፍ ላይ ሃንተር ከፍተኛ የኮኬይን ተጠቃሚ መሆኑን ቢገልጽም፣ የመንግሥት የግል መረጃ መጠየቂያ ሰነዶች ላይ የትኛውንም ዕፅ በሕገ-ወጥ መንገድ ተጠቃሚ አይደለሁም ብሎ ስለመሙላቱ ሪፖርት ተደርጓል።
እአአ 2014 በደሙ ውስጥ ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ እፅ መገኘቱን ተከትሎ ከአሜሪካ ባሕር ኃይል እንዲሰናበት ተደርጎም ነበር።












