የአሜሪካ ግዛቶች ስልኮችን ከትምህርት ቤቶች ለማገድ የፈለጉበት አነጋጋሪ ውሳኔ

የሞባይል ስልኮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መምህርት ናንሲ ስትሪት የተማሪዎቿን ትኩረት ለማግኘት ከስማርት ስልኮቻቸው ጋር መወዳደር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ታውቀዋለች።

እናት በመሆኗ ደግሞ ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት ስልኮቹ አስፈላጊ መሆናቸውንም በደንብ ትረዳለች።

“በአብዛኛው የሚደውሉት ወላጆች ናቸው” ስትል ትገልጻለች። በክፍሏ ውስጥ ስልክ መጠቀምን ባትፈቅድም ተማሪዎች ግን ሕጎቹን አዘውትረው ይጥሳሉ።

ስትሪት የምታስተምርበት ሎስ አንጀለስ አካባቢ፣ የአገሪቱ ሁለተኛው ትልቁ የትምህርት አውራጃ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የስማርት ስልክ መጠቀምን ከልክሏል።

በአሜሪካ ያሉ በርካታ ግዛቶች እና ትምህርት ቤቶች እያደገ የመጣውን ልጆች በስልኮች ላይ ያላቸውን ጥገኝነት እንዴት መቆጣጠር እንደሚችሉ እያጠየኑ ነው።

ከአሜሪካ ግዛቶች መካከል በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ የሆኑት ኒው ዮርክ እና ካሊፎርኒያ በጉዳዩ ላይ አዳዲስ ፖሊሲዎችን እየተመለከቱ ነው።

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የካሊፎርኒያ ገዢ ጋቪን ኒውሰም በመማሪያ ክፍል ውስጥ ስማርት ስልኮች እንዲታገዱ ጠይቀው ከሕግ አውጪዎች ጋር በፖሊሲው ላይ እንደሚሠሩም ተናግረዋል ። የኒውዮርክ ገዢ ካቲ ሆቹልም ተመሳሳይ ሕግ እንዲወጣ ድጋፍ ሰጥተዋል።

የኢንዲያና ግዛት አገረ ገዢ በቅርቡ ተግባራዊ የሚደረግ ስልኮችን ከመማሪያ ክፍል የሚያግድ ሕግ ላይ ፈርመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በትምህርት ቤቶች ውስጥ የስማርት ስልኮችን አጠቃቀም በተመለከተ በተለይም ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ በወጣቶች የአእምሮ ጤና ላይ ስጋት መፈጠሩን ተከትሎ ሊኖር የሚገባውን ፖሊሲ ላይ የነበረው ረጅም ክርክር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን የሚያመለክት ይመስላል።

አብዛኞቹ የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች የስልክ ፖሊሲ አላቸው። በ2021-2022 የትምህርት ዘመን 76 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ነክ ጉዳዮች ውጪ ስልክ መጠቀምን ከልክለዋል ሲል የአሜሪካ የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በቅርብ ጊዜ እየወጡ ያሉ ሕጎች የነበረውን አሠራር ለማጥበቅ ያለሙ ናቸው።

በሎስ አንጀለስ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል አስተማሪ የሆነችው ራፋኤላ ሆጅስ፣ ልጆች ትስስር የሚፈጥሩበት መንገድ አሳሳቢ እና አስደናቂ ለውጥ ማሳየቱን ተናግራለች።

“ሳይመቻቸው ሲቀር ስልካቸውን ያነሳሉ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግራለች።

በሪፐብሊካን እና በዲሞክራቲክ ፓርቲዎች ቁጥጥር ስር ያሉ የሕግ አውጪዎችም ባልተለመደ መልኩ ተመሳሳይ ፖሊሲዎች ላይ ተመሳሳይ አቋም ሲይዙ ታይተዋል።

ፍሎሪዳ ባለፈው ዓመት የግዛቱን ሕግ ተግባራዊ አድርጋ የትምህርት ተቋማት ስልኮችን በመማሪያ ክፍል ውስጥ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እና በትምህርት ቤት ዋይ ፋይ ላይ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን እንዲያግዱ የሚያደርገውን አሰገዳጅ አሠራር ተግባራዊ አድርጓል።

ትምህርት ቤቶች “ማኅበራዊ ሚዲያ የሚያስከትለው ማኅበራዊ፣ ስሜታዊ እና አካላዊ ተፅዕኖዎች ላይ መመሪያ እንዲሰጡም” ሕጉ ይጠይቃል።

ሜይን እና ቨርጂኒያንን ጨምሮ በርካታ ግዛቶች ውስጥ ያሉ አውራጃዎችም በስልክ አጠቃቀም ዙሪያ ጠንካራ ሕጎችን እያወጡ ነው። በካናዳም ኦንታሪዮ እና አልበርታን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች ተመሳሳይ መንገድ ጀምረዋል።

የተማሪዎች እና የስልክ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የማያልቀው ክርክር

በትህምርት ቤቶች ውስጥ ስልክን በተመለከተ ያለው ስጋት ስልኮች ለገበያ ከቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ አብሮ ብቅ ብሏል። በተወሰነ ጉዳዮች ላይ መግባባት ቢኖርም፤ አብዛኞቹ ግን የውዝግብ ምክንያት ሆነው ቆይቷል።

አሜሪካ ከአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ ጀምሮ የመገናኛ መሳሪያዎችን ከመማሪያ ክፍል ለማገድ ብዙ ሙከራዎችን አድርጋለች።

ቀደም ሲል የነበሩ ተቺዎች ስልኮች የተማሪዎችን ትኩረት ይሰርቃሉ፤ አለፍ ሲልም ከአደንዛዥ ዕፅ ነጋዴዎች ጋር ግንኙነት ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚልፍ ፍርሃት ያነሱ ነበር።

እአአ በ1999 በኮሎራዶ ኮሎምባን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተኩስ ተከፍቶ 13 ሰዎች መሞታቸው፤ አንዳንድ ወላጆች እና ትምህርት ቤቶች ለድንገተኛ አደጋ ወቅት ስልኮች ቁልፍ የመገናኛ መሳሪያ በመሆናቸው ጉዳዩን እንደገና እንዲገመግሙ አድርጓቸዋል።

በዚህም ምክንያት እአአ በ2002 የስልክ እገዳን የሻረውን የካሊፎርኒያን ሕግ ጨምሮ በርካቶች ሕጋቸውን ላላ አድርገዋል።

ስልኮች እንደ ማዘናጊያ፣ ለሳይበር ጥቃት እና ተማሪዎች የተሰጣቸውን የቤት ሥራ መኮረጅ የሚችሉበት መንገድ መሆናቸው ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ ክርክሩ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል።

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ያሏት ኒው ዮርክ ከተማም ጥብቅ እገዳን መተግበር ጀምራለች። እአአ በ2015 ሕጉ ተቀይሮ ትምህርት ቤቶች የራሳቸውን ፖሊሲ እንዲያወጡ አስችሏል።

የማኅበራዊ ሚዲያ እና የተማሪዎች የአእምሮ ጤና

አሁን ያለው የፖሊሲ ጉዳይ የሚመጣው ባለሙያዎች ስለተማሪዎች የአእምሮ ጤና እና የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ስጋታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ሰኞ ከአሜሪካ ከፍተኛ የጤና ባለሥልጣናት አንዱ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሲጋራ ላይ ካሉት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ማስጠንቀቂያ እንዲሰፍሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዋነኛው ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ቪቬክ ሙርቲ ማኅበራዊ ሚዲያ ህጻናትን ለጭንቀት እና ለድብርት ምልክቶች የማጋለጥ ዕድላቸውን ከፍ እንደሚያደርግ ቢከራከሩም በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶች የተለያየ ውጤቶችን አሳይተዋል።

“ልጆች ለመማር የሚሞክሩበት ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ጊዜም በስልካቸው ለጓደኞቻቸው መልዕክት የሚልኩበት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለሚተላለፉ መልዕክቶች ምላሽ የሚሰጡበት፣ የሚሠራጩ መልዕክቶች የሚመለከቱበት ሁኔታ አለ” ሲሉ ዶክተር ሙርቲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ይህም ለመማር ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤት ውስጥ ግንኙነቶችን እና ጓደኝነትን ለመፍጠርም በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል።”

በቀን ከሦስት ሰዓታት በላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያሳልፉ ታዳጊዎች እንደ ጭንቀት እና ድብርት ላሉ የአእምሮ ጤና ችግሮች የመጋለጥ ዕድላቸው በእጥፍ ይጨምራል በሚል በ2019 የታተመው እና በአሜሪካ የጤና ሚኒስቴር በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ጥናት ያሳያል።

ዕገዳው ይሳካ ይሆን?

የፖሊሲው ለውጡ ይጸና ይሆን? ትምህርት ቤቶች በደኅንነት እና በማኅበራዊ ሚዲያ የአደጋ ጥሪን በመገደብ መካከል ያለውን ሚዛን ለመጠበቅ ለዓመታት ታግለዋል።

ፖሊሲው ጠንካራ ማኅበረሰባዊ መግባባት ካልተፈጠረ እና በአፈጻጸም ላይ ወጥነት ከሌለው አይሳካም ሲሉ የብሔራዊ የትምህርት ቤቶች ደኅንነት አገልግሎት ፕሬዝዳንት ኬን ትራምፕ ተናግረዋል።

ትራምፕ አክለውም “ወላጆች ወይም ሌላ ሰው ከሩቅ ከሚመለከቱት እና ከሚያስቡት በላይ ብዙ ነገር አለው። በርካታ ውስብስብ ነገሮችም አሉት” ብለዋል።

በሎስ አንጀለስ የቦርድ አባላት ስልኮቹ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ እንዲታገዱ ድምጽ ሰጥተዋል። ፖሊሲው እንዴት ይተገበራል? የሚለው ግን አሁንም ግልጽ አይደለም።

በርካታ ትምህርት ቤቶች እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ባሉባት ሎስ አንጀለስ ነዋሪ የሆነችው የ18 ዓመቷ አሊሳ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ያለ ስልክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዴት እንደምትማር ማሰብ ያቅታትል።

“ግዙፍ ካምፓሶች አሉን። ያንን ሁሉ ተማሪ ማንም ሊከታተል አይችልም። የማንታይባቸው ብዙ ቦታዎች አሉ” ብላለች።