በዘንድሮ የሃጅ ጉዞ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ከ1300 መሻገሩን ሳዑዲ አረቢያ ገለጸች

አብዛናዎቹ ሟቾች በህገወጥ መንገድ የተጓዙ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, EPA

በዘንድሮ የሃጅ ጉዞ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር ከ1ሺህ300 መሻገሩን ሳዑዲ አረቢያ አስታወቀች። አብዛኛዎቹ ሟቾች ያለፈቃድ ወደ አገሪቱ ገብተው በከፍተኛ ሙቀት ረጅም ርቀት የተጓዙ ምዕመናን ናቸው ተብሏል።

የዘንድሮው የሃጅ ጉዞ የተካሄደው በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ወቅት ሲሆን የሙቀት መጠኑ ከ50 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ የሆነበት ጊዜ ነበር።

ከሟቾቹ ውስጥ ከሦስት አራተኛ በላይ ፍቃድ ሳይኖራቸው የገቡ እና በቂ መጠለያ ሳይኖራቸው በጠራራ በፀሐይ ሲጓዙ የነበሩ ናቸው ሲል የሳዑዲ አረቢያ የዜና ወኪል ኤስፒኤ አስነብቧል።

ከሞቱት መካከል አንዳንዶቹ አረጋውያን ወይም ሥር የሰደደ ሕመም የነበረባቸው መሆናቸውን ኤጀንሲው አክሎ ገልጿል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፋህድ አል-ጃላጄል ስለ ሙቀቱ አደገኛነት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እና ሃጃጆች ይህንን እንዴት መከላከል እንደሚችሉ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

ከ140 ሺህ በላይ ፍቃድ የሌላቸውን ጨምሮ የጤና ተቋማት ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ተጓዦችን ማከም የቻሉ ሲሆን አንዳንዶች አሁንም ሙቀቱ ባደረሰባቸው ጉዳት ሆስፒታል ይገኛሉ ብለዋል።

"ሟቾቹን አላህ ይቅር ብሎ ምህረቱን ይስጣቸው። ለቤተሰቦቻቸው ደግሞ ልባዊ መጽናናትን ይስጣቸው" ብለዋል ሚኒስትሩ።

ሳዑዲ አረቢያ የሃጅ ጉዞን አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ እያከናወነች አይደለም በሚል ተወቅሳለች። በተለይም ሕጋዊ ያልሆኑ ተጓዞች የአየር ማቀዝቀዣ ያላቸው ድንኳኖች እንዲሁም የሃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም ተብሏል።

የሳዑዲ አረቢያ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ማዕከል እንዳስታወቀው ከሆነ በመካ ያለው የሙቀት መጠን እስከ 51.8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከፍ ብሏል።

በርካታ አገራት ስለሞቱት ዜጎቻቸው ወቅታዊ መረጃ እያወጡ ቢቆዩም ሳዑዲ አረቢያ ግን በሟቾቹ ዙሪያ በይፋ አስተያየት አልሰጠችም ወይም ይፋዊ ቁጥር እስከ እሁድ ድረስ አላወጣችም።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የአረብ ዲፕሎማትን ጠቅሶ እንደዘገበው 658 ግብጻውያን ሞተዋል። ኢንዶኔዥያ በበኩሏ ከ200 በላይ ዜጎቿ ህይወታቸውን ማጣታታቸውን ስትገልጽ የ98 ህንዳዊያን ዜጎች ህይወትም አልፏል።

ፓኪስታን፣ ማሌዥያ፣ ዮርዳኖስ፣ ኢራን፣ ሴኔጋል፣ ሱዳን እና የኢራቅ ራስ ገዝ ክልል የሆነችው ኩርዲስታንም ዜጎቻቸው መሞታቸውን አረጋግጠዋል።

ሃጅ ሙስሊሞች ወደ ቅድስቷ መካ ከተማ የሚያደርጉት ዓመታዊ ኃይማኖታዊ ጉዞ ነው። በገንዘብም እና አካላዊ ብቃት ያላቸው ሙስሊሞች በሙሉ በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ የሃጅ ጉዞን ማጠናቀቅ አለባቸው።

በዚህ ዓመት ወደ 1.8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሃጅ ጉዞ ተሳትፈዋል ስትል ሳዑዲ አረቢያ ገልጻለች።

በሳዑዲ የነበረው ሙቀት ከ50 ዲግሪ ሴሊሺዬስ የሚያልፍበት ገዜ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በተለይም ያለሕጋዊ ፈቃድ የሚጓዙ ምዕመናንን ጨምሮ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጣፋ ማድቡሊ 16 የቱሪዝም ኩባንያዎችን ፈቃዳቸውን በመሰረዝ ወደ መካ ህገ-ወጥ የሃጅ ጉዞ የፈቀዱ ስራ አስኪያጆቻቸውን ጉዳይ ዓቃቤ ህግ እንዲመለከተው ቅዳሜ ዕለት ልከዋል።

ዮርዳኖስ ደግሞ አርብ ዕለት ሙስሊም ተጓዞችን በህገ ወጥ መንገድ እንዲጓዙ ያመቻቹ በርካታ የጉዞ ወኪሎችን በቁጥጥር ስር ማዋሏን ተናግራለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቱኒዚያው ፕሬዝዳንት ካይስ ሰኢድ የኃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትራቸውን አባረዋል።

የሃጅ ፈቃድ ለአገሮች በኮታ ስርዓት የሚመደብ ሲሆን ለግለሰቦች ደግሞ በዕጣ ይከፋፈላል።

ከፍተኛ ወጪ ማስወጣቱ ግን ብዙዎች ካለፍቃድ ለመጓዝ እንዲሞክሩ ያነሳሳቸዋል። በዚህ መልኩ ከተያዙ በቁጥጥር ስር ሊውሉ እና ሊባረሩ ይችላሉ።

ከሃጅ ጉዞ በፊት የሳዑዲ ባለስልጣናት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ህገወጥ ምዕመናንን ከመካ እንዳስወጧቸው ተናግረዋል።