ጠ/ሚ ዐቢይ ከፋኖ እና ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር መንግሥት ተከታታይ ንግግር እያደረግን ነው አሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, PM OFFIC/GB

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር መንግሥት ተከታታይ የሆነ ንግግር እያደረገ መሆኑን ተናግሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ኢትዮጵያ ተግባራዊ ባደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሸያ ፖሊሲ ላይ በጽህፈት ቤታቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር ሐሙስ 26/2016 ዓ.ም. ባደረጉት ውይይት ላይ ነው።

ኢትዮጵያ ታሪካዊ የሚባል የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ማሻሻ ማድረጓን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር እና ድጋፍን ማግኘቷ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ አገሪቱ ለወሰደችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ እርምጃ ትግበራ ሰላም እና መረጋጋት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም መንግሥታቸው አስፈላጊውን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

“ሰላም እና መረጋጋት ካልመጣ ኢንቨስትመንት አይመጣም፣ የቱሪስት ፍሰት በምንፈልገው መጠን አያድግም... ሰላም እና መረጋጋት የግድ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ለሁለት ዓመታት ከዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ገና እያገገመች ባለችው ኢትዮጵያ፤ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው ግጭት በአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ትልቅ አደጋን ደቅኖ ቆይቷል።

የፌደራሉ መንግሥት በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን በአማራ እና ኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ተከታታይ የሆነ ውይይት እያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስረድተዋል።

“እስካሁን አልገለጽኩትም፤ ዛሬ እንድታውቁት በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ንግግር ከጀመርን ውለን አድረናል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በርካታ ቡድኖች መሆናቸው እና አንድ አለመሆናቸው የንግግር ጥረቱ ላይ እክል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ተቅሰዋል።

“አንድ ስላልሆነ ኃይሉ፤ ከዚህኛው ስንነጋገር ከሌላኛው ጋር አንግባባም። ለንግግር እንዲመች አንድ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ነበር። ነገር ግን ንግግር እያደረግን ነው። በተቃርኖ ያሉ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር ንግግር የጀመሩ ቡድኖች አሉ” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተመሳሳይ እንዲሁ መንግሥት ‘ሸኔ’ ከሚለው እና በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ያለውን ልዩነት በንግግር ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “በተመሳሳይ የሸኔ ኃይሎች አንድ አይደሉም። ከተወሰኑ ቡድኖች ጋር እንዲሁ ቀጣይነት ያለው ንግግር እያደረግን ነው” በማለት ጥረቶቹ በቶሎ ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደረገውን ጉዳይ አንስተዋል።

መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና ከፋኖ ጋር የሚደረገው ውይይት ፍሬያማ እንዳይሆን ያደረገው “በአንድ ስም የሚጠሩ በርካታ ቡድኖች መኖራቸው ነው” ብለዋል።

“ከአንደኛው ቡድን ጋር መግባባት ብዙ ለውጥ ላያመጣ ይችላል” ካሉ በኋላ የሰላም መቋጫ ንግግር ስለሆነ የፌደራል መንግሥት ከኃይሎቹ ጋር ለንግግር የሚያደርገው ጥረት እንደሚያስቀጥል ተናግረዋል።

በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት ታጣቂ ቡድኖች ጋር ንግግር እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን በተመለከተ የፋኖ ቡድኖች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።

በአማራ እና ኦሮሚያ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር ንግግር ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ በትግራይ ክልል እንዲሁ ዳግም ግጭት እንዳይከሰት ተከታታይ የሆነ ውይይት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ወራት የፌደራል መንግሥቱን ወደ ግጭት ሊያስገቡ የሚችሉ ከአምስት ያላነሱ ትንኮሳዎች በትግራይ ኃይሎች አማካይነት ተፈጥረዋል።

“ወደማያስፈልግ መንገድ የሚወስድ በመሆኑ አያስፈልግም ብለን በተደጋጋሚ ተወያይተን [ከትግራይ ኃይሎች ጋር] ጉዳዩ መስመር እንሲይዝ አድርገናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፉት ሦስት ወራት ወደ ግጭት እንዳይገባ ከ10 ጊዜ በላይ ውይይቶች ነበሩ ብለዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነት ለማስቆም ከህወሓት ጋር ድርድር በማድረግ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ ግጭቱ መቆሙ ይታወቃል። ከህወሓት ሕጋዊ ሰውነት ጋር በተያያዘ ባለፉት ሳምንታት አለመግባባቶች መፈጠራቸው ይታወቃል።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ታንዛኒያ ውስጥ ለሁለት ጊዜ ንግግር ተካሂዶ ከስምምነት ይደረሳል ተብሎ ሲጠበቅ ያለውጤት መጠናቀቁ አይዘነጋም።