የኢትዮጵያ የፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ተስፋ እና ስጋት፡ ምን ውጤት ይጠበቃል?

ኢትዮጵያ እአአ በ1896 ‘ሀ’ ተብሎ ወደ ተጀመረው ኦሊምፒክ መድረክ ብቅ ያለቸው 60 ዓመታትን ዘግይታ ነው። የመጀመሪያ ተሳትፎዋንም በ1956 በተካሄደው በ16ኛው የሜልበርን ኦሊምፒክ ነበረ።
አትሌቲክስ በኢትዮጵያ የውድድሩ ተሳትፎ እና ውጤት ትልቁን ድርሻ ይይዛል። በቦክስ እና በብስክሌት እሽቅድድም የተሳተፈችባቸው ጊዜያትም ነበሩ። በውሃ ዋናም በጣት የሚቆጠሩ ስፖርተኞች ኢትዮጵያን ወክለው በኦሊምፒክ ተሳታፊ ሆነዋል።
ፓሪስ ላይ ባለፈው ሳምንት ተጀምሮ እየተካሄደ ባለው 33ኛው የኦሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያ በምትታወቅባቸው ውድድሮች ምርጥ ስፖርተኞቿን ይዛ ትሳተፋለች።
ለመሆኑ ከፓሪሱ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ምን ትጠብቃለች? ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሜዳሊያ ከተገኘባቸው ውድድሮች ምን ውጤት ይጠበቃል? ሲል ቢቢሲ ውድድሩን ለዓመታት በቅርበት የተከታተሉ ሁለት ጋዜጠኞችን ጠይቋል።
ኢትዮጵያ እና ኦሊምፒክ
ተሾመ ቀዲዳ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የበሪሳ ጋዜጣ የስፖርት አዘጋጅ ነው። ደራርቱ ቱሉ ካሸነፈችበት ከባርሴሎና ኦሊሎምፒክ ጀምሮ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የኦሊምፒክ ውድድሮቹን ከስፍራቸው እና ከርቀት በቅርበት በጋዜጠኛነት ተከታትሏል።
“ኦሊምፒክ ሲባል ምንጊዜም ኢትዮጵያ ትጠበቃለች” የሚለው ተሾመ፣ ይህም በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን “ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምር እነአበበ ቢቀላን እና ሌሎችን እያነሱ” ተሳትፎዋን እና ተጠባቂነቷን በየጊዜው ይዘግባሉ።
ኢትዮጵያ ከሜልበርን ኦሊምፒክ ውጪ በተሳተፈችባቸው ውድድሮች ውስጥ ሜዳሊያ ሳታገኝ የቀረችበት አጋጣሚ የለም።
አንዳንድ ሜዳሊያዎች ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የመጀመሪያ ናቸው። “አበበ ቢቂላ እና ደራርቱ ቱሉን መውሰድ ይቻላል። ፋጡማ ሮባም በኦሊምፒክ የሴቶች ማራቶን አሸናፊ በመሆን ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ ናት” ይላል ተሾመ።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ የምትሳተፍባቸው ውድድሮች አነስተኛ ቢሆኑም በውጤት ረገድ ግን ስመ ገናና ናት።
እስካሁንም 23 የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊዎችን ስትወስድ፣ እንዲሁም 12 የብር እና 23 የነሐስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት የ58 የኦሊምፒክ ሜዳሊያዎችን ባለቤት ናት።
በዚህ መሠረትም ከኬንያ እና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ በአፍሪካ በኦሊምፒክ ውድድሮች ከፍተኛ ሜዳሊያ በማግኘት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ ከተሳትፎ ባለፈ በተለይም ደግሞ በረዥም ርቀት ሩጫዎች እንድትጠበቅ ሆኗል።
ፓሪስ ኦሊምፒክ እና ውጤት
ከዚህ በፊት ከነበሩት ልምዶች አንጻር ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሊምፒክም ሜዳሊያ የምትጠብቅባቸው ዘርፎች አሉ።
አትሌቲክስ፤ ከአትሌቲክስም መካከለኛ እና የረዥም ርቀት ሩጫዎች።
በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት የሠራው እና አሁንም የኢትዮጵያን ስፖርት በቅርበት የሚከታተለው ታምሩ ዓለሙ ኢትዮጵያ ከምትሳተፍባቸው ውድድሮች “በአትሌተቲክስ ሜዳሊያዎችን እጠብቃለሁ” ይላል።
“በ5 ሺህ፣ በ10 ሺህ እና በማራቶን በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ3 ሺህ መሰናክል ወንዶች ውጤት እጠብቃለሁ። ጉዳፍ፣ ዮሚፍ፣ ሐጎስ፣ ቀነኒሳ፣ አማኒ፣ ትዕግስት አሰፋ እና ለሜቻ ካላቸው ወቅታዊ ብቃት እና ልምድ የተነሳ ሜዳሊያ ውስጥ ይገባሉ ብዬ የምገምታቸው ናቸው” ሲል ታምሩ ግምቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
የተሾመም ግምት ከታምሩ ብዙ የራቀ አይደለም፤ “ካሉት ልጆች በብቃት እነለሜቻ፣ ቀነኒሳ እና ጉዳፍ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው። ቀነኒሳም በአራተኛው ኦሊምፒኩ በማራቶን ይጠበቃል። ከኬንያው አትሌት [ኤሊውድ ኪፕቾጌ] ቀጥሎ ጥሩ ሰዓት አለው። ጉዳፍ ፀጋይም ጥሩ ሰዓት አላት። ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ መሰናክል ጥሩ ሰዓት አለው። 5 ሺህ ሜትርን ጨምሮ በእነዚህ [ውድድሮች] ተስፋ ይኖራል ብዬ እጠብቃለሁ” ብሏል።
ታምሩ በተለመዱት ዘርፎች ውጤት ቢጠብቅም ከተፎካካሪዎች የሚኖረውን ትንቅንቅ ከፍተኛ እንደሚሆን ሳይጠቅስ ግን አያልፍም።
ተሳትፎ እና ወርቅ
ኢትዮጵያውያን በኦሊምፒክ ላይ ሲሳተፉ ውጤት መጠበቅ የተለመደ ነው። እገሌ ይጠበቃል ሲባልም ለወርቅ ሜዳሊያ ነው የሚጠበቀው የሚል ልማድ አለ። ለአንዳንድ አገሮች የኦሊምፒክ ተሳትፎ ብርቅ ሲሆን፣ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ግን ከወርቅ ውጪ ያለውን ድል እንደ ጥሩ ውጤት ያለመቁጠር ነገር ይታያል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በትውልድ ቅብብሎሽ ይታወቃል የሚለው ተሾመ “ከአነበበ እስከ ቀነኒሳ እና ጥሩነሽ ድረስ ከኦሊምፒክ እስከ ዓለም ሻምፒዮና ወርቅ ያመጣሉ ተብለው ነው የሚጠበቁት፤ ምክንያቱም አበበም፣ ማሞም ያሸንፋሉ ሲባሉ አሸንፈው ነው የሚመጡት” ብሏል።
ቀጥሎ እነምሩጽ ነበሩ። ኃይሌ፣ ደራርቱ፣ ቀነኒሳ፣ መሠረት እና ጥሩነሽም የትውልድ ቅብብሎሹን አስቀጥለዋል።
“እነዚህ ተካፈሉ ማለት ወርቅ አለ ማለት ነው” የሚለው ተሾመ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተስፋ የሚጣልባቸው አንድ ወይም ሁለት አትሌቶች መሆናቸውን ጠቁሟል።
“እንኳን ሕዝቡ ሚዲያውም በትክክል የሚያውቃቸው ውጤት አላቸው ብሎ የሚጠብቃቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው። ለምሳሌ ቀነኒሳ ታላቅ አትሌት ነው። በአሁኑ ሰዓት ጉዳፍ እና ለሜቻ ናቸው። ከዚህ ውጪ ደግሞ ዮሚፍ ቀጄልቻ ነው ያለው።”
“ሌሎች አትሌቶች አቅም የላቸውም ማለት አይደለም” የሚለው ተሾመ፤ ከእነዚህ ውጪ “ዛሬ ማን ወርቅ ያመጣል ብለን ብጠይቅ በጣም ያስቸግራል። አፍን ሞልቶ እከሌ ወርቅ ያመጣሉ ተብሎ የሚጠበቁ አትሌቶች በጣም ትንሽ ናቸው” ሲል አክሏል።

ለታምሩ የዘንድሮው ስብስብ ልምድ ያላቸውን እና አዳዲስ ስፖርተኞችን ያቀፈ ነው።
ፓሪስ ለቀነኒሳ የመጨረሻው የኦሊምፒክ ተሳትፎው ሊሆን ይችላል የሚለው ታምሩ፤ “በሜዳሊያ ይፈፅማል የሚል እምነት አለኝ” ይላል።
ጉዳፍ [በ5 ሺህ እና የ1500 የቤት ውስጥ] እና ትዕግስት [በማራቶን] ክብረ ወሰን ስላላቸው ውጤት ይጠብቃል።
አዲሱ ይሁኔ [በ5 ሺህ]፣ መዲና ኢሳ [በ5 ሺህ]፣ ፅጌ ገ/ሰላማ [በ10 ሺህ] እንዲሁም አማኒ በሬሶ [በማራቶን] ከአዲሶቹ የሚጠብቃቸው ናቸው።
ይህ በተለመዱት የረዥም ርቀት ውድድሮች ነው። ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች ስማቸው ባልገነነበት መድረክም ጥቂት ጭላንጭሎች አሉ።
የኬንያውያን የባህል ስፖርት ነው የሚባለውን 3 ሺህ መሰናክል በአሁኑ ጊዜ ክብረ ወሰኑ “እኛ እጅ ነው ያለው” ይላል ተሾመ።
እሸቱ ቱራ ሞስኮ ላይ በ3 ሺህ መሰናክል ነሐስ ካመጣ ጀምሮ [በዘርፉ] በኦሊምፒክ ተስፋ የሚጣልበት አንድም አትሌት አልነበረም።
“ይሄዳሉ ማጣሪያ ሳያልፉ ነው የሚመለሱት። በዓለም ሻምፒዮና የታየው ለሜቻ ግርማ አዲስ ስለሆነ [ተስፋ የሚጣልበት ውድድር] እሱ ነው ብዬ ነው የምገምተው። ከዚያ ውጪ የሚታወቁት ማራቶን፣ 5 እና 10 ሺህ ናቸው” አልፎ አልፎም በ1500 ሜትር ውጤት ብልጭ የሚልበት አጋጣሚ እንደሚኖር ያነሳል።
ታምሩ ደግሞ ከለሜቻ በተጨማሪ ፅጌ ዱጉማን [በ800] እና ብርቄ ሀየሎምን [በ1500] ያነሳል።
የሜዳ ላይ ስጋት እና ከሜዳ ውጭ ያለው እሰጥ አገባ
በበርካታ ወርቆች ደምቆ ከኦሊምፒክ ውድድሮች የሚመለሰው የኢትዮጵያ ቡድን ባለፉት ጥቂት ውድድሮች የወርቆቹ ቁጥር በአንድ ተገድበዋል።
ለምሳሌ በ2012 ኦሊምፒክ መሠረት ደፋር በ5 ሺህ፣ ጥሩነሽ ዲባባ በ10 ሺህ እና ቲኪ ገላና በማራቶን ወርቅ ያስገኙ አትሌቶች ነበሩ። ሁለት ብር እና 3 ነሐስም በዚሁ በለንደን ኦሊምፒክ ተገኝቷል።
በቀጣዩ የ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ አልማዝ አያና ብቸኛውን ወርቅ በ10 ሺህ ሜትር አሳክታለች። በሪዮው ኦሊምፒክ 2 ብር እና 5 ነሐስ ማሳካት ተችሏል።
የ2020ው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ደግሞ ሰለሞን ባረጋ ብቸኛውን ወርቅ በ10 ሺህ ሜትር አግኝቷል። በዚህ ውድድር የሜዳሊያውም ቁጥር ቀንሶ አንድ ብር እና ሁለት ነሐስ ብቻ ነው የተገኘው።
ይህ ደግሞ ስጋት ፈጥሯል።
የወንዶች 5 ሺህ እና 10 ሺህ ውድድር ላይ ከሌሎች አገራት ጠንካራ ተፎካካሪዎች አሉብን ለሚለው ታምሩ በተለይም በ5 ሺህ “ከሐጎስ ውጪ ልምድ ስለሌላቸውም ይበልጥ ይፈተናሉ የሚል ስጋት አለኝ” ይላል።
ወጥ አቋም ያለው አትሌት ማግኘት ከባድ መሆኑን በማንሳትም በእርግጠኝነት አትሌቶቹ ሜዳሊያ ያስገኛሉ ብሎ ለመናገር እንደሚከብደው ገልጿል።
“ወቅታዊ ብቃት እና የዓለም ክብረ ወሰን የያዙ አትሌቶች አሉን፤ እነሱ በአቋማቸው ከቀጠሉ ሜዳሊያ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ” ሲልም ታምሩ ግምቱን ያስቀምጣል።
ጉዳፍ በ1500፣ 5 ሺህ እና 10 ሺህ ትሳተፋለች። ከዚህ ቀደምም በሦስቱም የተወዳደሩ አትሌቶች አሉ።
ነገር ግን ታምሩ “ከሦስቱ ይልቅ በሁለቱ ወይም በአንዱ ትኩረት ሰጥታ ብትዘጋጅ መልካም ነበር” ይላል።
ሦስቱም የየራሳቸው ‘የልምምድ እና የዝግጅት ሥርዓት’ ያላቸው ከመሆኑም በላይ በ1500 እንዲሁም በ5 ሺህ ሜትር ማጣሪያዎች መኖራቸው “ዕቅዷን ሊያጨናግፍባት ይችላል” የሚል ስጋት አለው።
በጉዳፍ ተሳትፎ ምክንያት ፍሬወይኒ ኃይሉ እና ሂሩት መሸሻ ከተሳትፎ ውጪ ሆነዋል።
ጉዳፍ በአንድ ወይም በሁለት ውድድሮች ላይ አተኩራ ለሌሎቹ አትሌቶች ዕድሉ ቢሰጥ የተሻለ ይሆን ነበር የሚል ሐሳብ ነው ያለው።
ውድድሩ ከሜዳ ውጪ ያለ ውዝግብም ጥላውን አጥልቶበታል። የዛሬ አራት ዓመት በኦሊምፒክ ኮሚቴ እና በአትሌቲክስ ፌደሬሽን መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ዘንድሮም ከኦሊምፒኩ በፊትም ተደግሟል።
ይህም “አንዳንዶች [ከኦሊምፒክ] ተሳትፎ ውጪ ችግር ውስጥ እንገኛለን ብለው እንዲገምቱም አድርጓቸዋል” ይላል ተሾመ።
በሀሉቱ ተቋማት መካከል ያለው ችግር መልኩን እየቀያየረ አሁን ድረስ ዘልቋል።
“ችግሩ እያለ ነው አትሌቶቹ ሄዱት። ለዚህ ነው አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡ ተስፋ የሚቆርጠው። ምክንያቱም ትርምሱ እና አለመግባበቱ አትሌቶቻችን ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል” በማለት በውጤት ላይ ጫና ሊኖረው እንደሚችል ተሾመ ይጠቅሳል።
“የአትሌቶች ምርጫ ውዝግብ በውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ያመጣል። እስካሁን ያኮረፉ ብቻቸውን የሚሠሩ ቅሬታ ያላቸው አትሌቶች አሉ” የሚለው ታምሩ “በግልፅ ለመናገር በተለይ ጉዳፍ በሦስት ርቀቶች መሮጧ እንዲሁም በሁለት ርቀቶች የመሮጥ ፍላጎት ያላቸው ዮሚፍ እና ፅጌ ገ/ሰላማ መከልከላቸው ቅሬታን ፈጥሯል” ብሏል።
“አትሌቲክስ ላይ አደጋ እያንዣበበ ነው የሚሉ አሉ። ይህ በግልጽ የሚታይ ነው። ኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና በመጣ ቁጥር መጠላለፉ ከቀጠለ አትሌቲክሱ አደጋ ላይ ነው” ብሎ ተሾመ ያምናል።
ነገር ግን ታምሩም ሆነ ተሾመ በዚህ ሁሉ ቅሬታ እና አለመግባባት ውስጥ በማለፍ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ይመኛሉ።












