ከ7 የእስራኤል የግድያ ሙከራዎች አምልጦ አሁን ተገድሏል የተባለው የሐማስ ጦር አዛዥ ዴይፍ ማን ነው?

መሐመድ ዴይፍ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, መሐመድ ዴይፍ

የእስራኤል ጦር ሠራዊት ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ባካሄደው የአየር ጥቃት የሐማስ ወታደራዊ መሪ የሆነውን መሐመድ ዴይፍን መግደሉን ይፋ አድርጓል።

ጦሩ እንዳለው ሐምሌ 6/2016 ዓ.ም. የጋዛ አንድ ክፍል በሆነችው ኻን ዩኒስ አካባቢ ዴይፍን ዒላማ አድርጎ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ነው የተገደለው። ነገር ግን ሐማስ ዴይፍ ስለመገደሉ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።

በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በወቅቱ ባወጣው መረጃ እስራኤል ዴይፍን ገደልኩበት ባለችው ጥቃት፣ የጦርነቱ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ካምፕ ውስጥ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ የእስራኤል ጦር ሠራዊት ጥቃቱ በተፈጸመበት ስፍራ “ሰላማዊ ሰዎች ሳይሆኑ የሐማስ ሽብርተኞች ብቻ ነበሩ” ማለቱን ዘግቧል።

በጥቃቱ ከዴይፍ በተጨማሪ ረዳቱ እና የመስከረም 26ቱን ጥቃት በማስተባበር አንዱ ነው የተባለው የኻን ዩኒስ ብርጌድ አዛዥ ራፋ ሳላማ ጭምር መገደሉን የእስራኤል መከላከያ ገልጿል።

ጥቃቱን በተመለከተ ሐማስ እስራኤል የፈጸመችውን “አሰቃቂ ጭፍጨፋ ለመሸፋፈን እየሞከረች ነው” በማለት ከስሶ ነበር።

ለአስርት ዓመታት የታደነው ዴይፍ

እስራኤል ለአስርት ዓመታት ስታድነው ቆይታለች፤ በጋዛ የሐማስ የጦር መሪ የሆነውን መሐመድ ዴይፍን።

አል-ቃሳም የተባለውን ብርጌድ የሚመራው ዴይፍ፣ እስራኤል ሲቪሎችን እና ወታደሮችን ገድሏል በማለት ነው ሌት ተቀን ስትፈልገው የቆየችው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሙሉ ስሙን ብዙ ሰው አያውቀውም። ይልቅ ቅጽል ስሙ ገናና ነው።

‘ዴይፍ’ ይባላል። ‘ዴይፍ’ ማለት ‘ጥቁር እንግዳ’ እንደማለት ነው፤ በአረብኛ።

ለምን ‘ዴይፍ’ ተባለ?

ምክንያቱም በነፍስ ከምትፈልገው ከእስራኤል ክትትል ለማምለጥ በየሰዉ ቤት እየሄደ ስለሚያድር ነው። አንድ ቤት ከአንድ ሌሊት በላይ አያሳልፍም። አንድ ቤት ሁለት ሌሊት ካደረ ከመልዓከ ሞት ጋር የማደር ያህል አደገኛ ነው - ለእሱ።

ሞሳድ ይደርስበታል። ስለዚህ ሁሌ እንግዳ ነው፤ ጥቁር እንግዳ።

ዴይፍ የድመት ነፍስ ነው ያለው የሚባለው ለምንድነው ካልን መልሱ ማንም የሚገምተው ነው። እስራኤል ገደልኩት ስትል እየተነሳ፣ ሞተ ሲባል እያንሰራራ ስላስቸገረ ነው።

ኮማንደር ዴይፍ ላይ እስራኤል ተደጋጋሚ እና ተከታታይ የግድያ ሙከራ ብታደርግበትም አልተሳካላትም። አራት ጊዜ ገደልኩት ብላ አራት ጊዜም ቆስሎ አምልጧል።

አንድ ጊዜ ዐይኑን አጥፍታዋለች። አንድ ጊዜ እግሩን አሳጥታዋለች። ሌላ ጊዜ መላ ቤተሰቡን በቦምብ ገድላለች።

ዴይፍ ግን ሞተ ሲባል የሆነ ቦታ ብቅ ይላል። “እስራኤል ወየውልሽ” እያለ መግለጫ ይሰጣል።

በአውሮፓውያኑ 2021 ለእስራኤል ማስጠንቀቂያ በድምጽ ላከ። በፍልስጤማውያን ሕይወት መቀለድ የማታቆም ከሆነ ቅጣት እንደሚጠብቃት የሚገልጽ መልዕክት።

በቀናት ውስጥ 13 እስራኤላዊያን ተገደሉ። እሰራኤል በበኩሏ 242 ሰዎችን ጋዛ ውስጥ ገደለች። ከእነዚህ መካከል 200 የሚሆኑት አሸባሪዎች ናቸው ብላ ነበር። እስራኤል ከእነዚህ አሸባሪዎች አንዱ መሐመድ ዴይፍ እንደሆነ ጭምር አምና ነበር።

ዴይፍ ግን ትንሽ ቆይቶ “አለሁ፤ አልሞትኩም” ብሎ መጣ።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የነበሩት ዲሰይ ዚልበርማን “በኦፕሬሽኑ ጊዜ በሙሉ መሐመደ ዴይፍን ለመግደል ሞክረናል፤ አልተሳካልንም እንጂ” ብለው ነበር ያኔ ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ።

ዴይፍ ለዓመታት አድፍጦ በድጋሚ የእስራኤል ራስ ምታት ሆነ።

መስከረም መጨረሻ ላይ ዓለምን ያነጋገረው እና በእስራኤል ላይ የደረሰውን ድንገተኛ ጥቃት ያቀነባበረው ይኽው መሐመድ ዴይፍ ሳይሆን እንዳልቀረ ይነገራል።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የተፈጸመውን መብረቃዊ ጥቃት ተከትሎ በሰዓታት ውስጥ በሐማስ ቴሌቪዥን መሐመድ ዴይፍ ደንገዝገዝ ባለ ብርሃን ውስጥ ሆኖ ብቅ በማለት “የእስራኤል ግፍ በቃን። የአል አቅሳው ጎርፍ ዘመቻ መብረቃዊ ጥቃትን ጀምረናል” ሲል አወጀ።

በዚህ መሐመድ ዴይፍ አቀነባበረው በተባለው የማይታመን ጥቃት፣ ከ1200 በላይ እስራኤላውያን ተገድለዋል። ከሟቾቹ ውስጥ ጥቂት የሌላ አገር ዜጎችም ይገኙበታል።

ከ150 በላይ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በሐማስ ታጣቂዎች ታግተው ወደ ጋዛ ሰርጥ ተወስደዋል።

መሐመድ ዴይፍ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, እምብዛም በአደባባይ የማይታየው ዴይፍ ይህ ቆየት ያለ ፎቶው በመገናኛ ብዙኃን በስፋት የሚታወቅበት ነው

መሐመድ ዴይፍ ማን ነው?

ስለዚህ ሰው ልጅነት ብዙም አይታወቅም። እውነተኛ ስሙ ግን ይታወቃል። ዲያብ ኢብራሒም አልማስሪ ነው።

አንዳንድ ሚዲያዎች ዴይፍ የተወለደው በጋዛ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ ነው ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ ሌላ ይላሉ።

ስለ ዴይፍ ልጅነት ከዚህ የዘለለ ብዙም አይታወቅም። ሐማስን የተቀላቀለው በወጣትነቱ ምናልባትም የመጀመሪያውን የፍልስጤማውያን አመጽ (ኢንቲፋዳ) ተከትሎ ነው።

እስራኤል ዴይፍን በ1989 (እአአ) በቁጥጥር ሥር አውላው ነበር። ሁለት ዓመት ግድም ታስሮ ተፈታ።

ከእስራኤል ስቃይ የበዛበት እስር በኋላ ግን ዴይፍ ሌላ ሰው ሆነ።

በሐማስ የውስጥ ሥልጣን መሰላል ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ላይ ወጣ። የሐማስ ወታደራዊ ክንፍን አጠናከረው።

ተከታታይ የሆኑ የሽብር ጥቃቶችን አቀነባብሯል ይላሉ ተንታኞች። ከአውሮፓውያኑ 1995 ወዲህ የተፈጸሙትን ብዙዎቹን የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች ያቀነባበረው እሱ ሳይሆን አይቀርም ይባላል።

በመጨረሻ ዴይፍ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ የሆነውን አልቃሳም ብርጌድን በአዛዥነት መምራት ጀመረ። ይህም በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 2002 የሆነ ነው።

ይህን ከፍተኛ ሥልጣን የተቀዳጀው እስራኤል ዕውቁን የቡድኑን አዛዥ ሳሊህ ሸሐዳን ከገደለች በኋላ ነው። ሳሊህ የአል ቃሳም ብርጌድ ዋና አዛዥ ነበር።

ዴይፍን ለመግደል የተደረጉ 7 ሙከራዎች

በአውሮፓውያኑ 2000 መባቻ ላይ ከአራት የእስራኤል ተከታታይ የግድያ ሙከራዎችን አምልጧል። በእነዚያ የግድያ ሙከራዎች ምክንያት ነው አንድ ዐይኑን ያጣው።

አንድ የእስራኤል የደኅንነት ሰው በ2006 (እአአ) ዴይፍ እንደተገደለ እምነት እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አምስተኛው የግድያ ሙከራ የተደረገበት በ2014 (እአአ) ነበር። እስራኤል እሱን ለመግደል በጋዛ ሼክ ሬድዋን በሚባለው ሰፈር ጅምላ የአየር ጥቃት መፈጸም ነበረባት።

ዴይፍ ከዚህ ጥቃትም በተአምር አመለጠ። ከጥቃቱ ማምለጥ ያልቻሉት ዊዳድ የተባለችው ባለቤቱ እና ሁለት ልጆቹ ተገደሉ።

አንዳንድ የእስራኤል የደኅንነት ሰዎች ቆስሎ ነው ያመለጠው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ጭራሽ በወቅቱ እዚያ አልነበረም ይላሉ።

ከዚያ በኋላ ሌሎች ሦስት የግድያ ሙከራዎችን አምልጧል።

ኔታንያሁ “ሁሉም የሐማስ አባል የሞት ጥላ እየተከተለው ነው” ሲሉ ጋዛ ውስጥ በሐማስ ላይ በከፈቱት ዘመቻ አንድም ሰው እንደማይተርፍ ዝተዋል።

ከዚህ ዛቻ የሚተርፍ አንድ የሐማስ አመራር ካለ ምናልባት ዴይፍ ሊሆን ይችላል ተብሎ ነበር።

ለመሆኑ በእስራኤል የደኅንነት ተቋማት እና ወታደራዊ ኃይሎች ከተቀነባበሩበት የግድያ ሙከራዎች እንዴት ሊያመልጥ ቻለ?

አንድ የደኅንነት ጉዳዮች አዋቂ ለቢቢሲ ሲናገሩ ዴይፍ ለእስራኤል አልጨበጥ ያለው ከማንኛውም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ራሱን ስላራቀ ነው ይላሉ።

“ስልክ ከሌለው፣ ኮምፒውተር ካልተጠቀመ፤ ዘመናዊ የስለላ መረብ እንዴት ሊያጠምደው ይችላል?” ብለው ይጠይቃሉ እኚህ የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ።

ሌላ የእሰራኤል የቀድሞ የደኅንነት ሰው ደግሞ ሐማስ ጥልቅ የመሬት ለመሬት ዋሻዎችን ቆፍሮ አዛዦቹን ስለሚያኖር፣ እንዲሁም ከሕዝብ ጋር ተቀላቅለው ንጹሐንን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ስለሚንቀሳቀሱ ዴይፍ ከተደገሰለት ሞት ሊያመልጥ ችሏል ብለው ያምናሉ።

እስራኤል በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ በዴይፍ ላይ ብቻ ሰባት ጊዜ የግድያ ሙከራ አድርጋለች። አካሉን ከማጉደል ውጪ አንዱም የሐማሱን ቁልፍ ሰው እስትንፋስ ሊቆርጥ አልቻለም ነበር።

ዴይፍ በጋዛ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ ዋና አዛዥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዴይፍ በጋዛ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አልቃሳም ብርጌድ ዋና አዛዥ ነው

ዴይፍ ለ8ኛ ጊዜ ከሞት ያመልጥ ይሆን?

ዴይፍ በአደባባይ አይታይም። ጋዛ ውስጥ ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው አይተው የሚለዩት። ነገር ግን “ጀግና” የሚሉት ልጃቸው ነው። ድል ባደረጉ ቁጥር ስሙን ከፍ አድርገው ያወድሱታል።

ከእስራኤል በተጨማሪ ወዳጇ አሜሪካም መሐመድ ዴይፍን በአደገኛ የአሸባሪዎች ዝርዝር መዝገብ ላይ ስሙን አስፍራው ቆይታለች።

እስራኤል በተለይ ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃት በኋላ ከማንም በላይ ዴይፍን አጥብቃ ስትፈልገው ቆይታለች።

በዓለም ቁጥር አንድ ከሚባሉት መካከል የሚመደቡትን የስለላ እና ወታደራዊ መኮንኖቿን አሰማርታ ከተቻለ በነፍስ ካልተቻለ ደግሞ የተረፈ ዐይኑን፣ የተረፈ እግሩን ልታሳጣው ስትጥር ቆይታለች።

ሐማስ በተቀናጀ ሁኔታ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ከባድ ጥቃት የተቆጡት እስራኤላውያን እና ባለሥልጣናቷ ቡድኑን እና መሪዎቹን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያለ እረፍት ጥረዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ዴይፍ ዋነኛው ዒላማዋ ነበረ። እስራኤል በስለላ እና በወታደራዊ ተቋሞቿ አማካይነት ከዚህ ቀደም ከሞከረችበት የግድያ ሙከራዎቿ የተረፈውን ዴይፍን ደግሞ በተለየ ስትፈልገው ቆይታለች።

እስራኤል ለወራት ሳይረጥ ዴይፍ እና የሚመራው ጦሩ ይገኙበታል የተባሉትን የጋዛ ጓዳ ጎድጓዳ በአውሮፕላን ቦምብ እና በከባድ መሳሪያ ስትደመስስ፣ በማስከተል ደግሞ እግረኛ ወታደሮቿን አሰማርታ ፍርስራሾችን ስታስስ ቆይታለች።

በዚህም ምክንያት ዴይፍ ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ካለቁበት የእስራኤል ያልተቋረጠ ወታደራዊ ዘመቻ በሕይወት ላይወጣ ይችላል ሲባል ቆይቷል።

በመጨረሻም ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በጋዛ ባለ የስደተኞች መጠለያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት እንደገደሉት ይፋ አድርገዋል።

ነገር ግን አሁን ዴይፍ እንደከዚህ ቀደሞቹ ሰባት የግድያ መከራዎች ጉዳት ደርሶበት አሊያም ምንም ሳይሆን አለሁ ሊል ይችላል። እስራኤሎች ግን በዴይፍ ላይ ያነጣጠሩት ዘመቻቸው ግዳዩን ጥሏል በማለት በእርግጠኝነት ለዓለም አሳውቀዋል።

ለዚህ ደግሞ በቀጣይ ቀናት የዴይፍ ቡድን ሐማስ የጦር አዛዡን ዕጣ ፈንታ በይፋ እስኪገልጽ መጠበቅ የግድ ነው።