የሐማስ መሪ ኢስማኢል ሃኒያ ኢራን ውስጥ ተገደሉ

የሐማስ የፖለቲካ ኃላፊ ኢስማኢል ሃኒያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሐማስ የፖለቲካ ኃላፊ ኢስማኢል ሃኒያ

የፍልስጤሙ ቡድን ሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኢል ሃኒያ በኢራን መዲና ቴህራን ውስጥ በሚገኘው መኖሪያቸው ቤታቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት ተገደሉ።

ሐማስ የቁጥር አንድ የመሪውን ግድያ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በእስራኤል በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸውን አስታውቋል።

ኢስማኢል ሃኒያ የተገደሉት የአዲሱን የኢራን ፕሬዝዳንት ባዕለ ሲመት ላይ ማክሰኞ ዕለት ከተሳተፉ በኋላ ነው።

የኢራን መንግሥት እንዲሁ ኢስማኢል ሃኒያ በአንድ ጥበቃቸው ጋር እንዲሁ መገደላቸውን አረጋግጧል።

አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የመሪውን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን በመግለጽ ለዚህም ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ባለፉት 10 ወራት ጋዛ ውስጥ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኘው የሐማስ አመራሮች እና ቤተሰቦቻቸው በእስራኤል ወታደራዊ እና የስለላ ተቋማት እየታደኑ ይገኛሉ።

ትናንት ማክሰኞ የተገደሉት የሐማስ ፖለቲካዊ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ልጆች እና የልጅ ልጆች ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ጦር በተፈጸመባቸው ጥቃት ተገድለዋል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር የእስራኤል አየር ኃይል ጋዛ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት እስማኤል ሃኒያን ሦስት ልጆች እና አራት የልጅ ልጆቻቸው ተገድለዋል።

ሐማስ ምን አለ?

የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ የሃኒያ ግድያ “ምላሽ ሳያገኝ አያልፍም” ብለዋል።

የኢስማኢል ሃኒያ ግድያ “በጣም ግብዝና የተሞላበት ድርጊት ነው። ለግድያው ምላሽ እንሰጣለን” ሲሉ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ሙሳ አቡ ማርዙክ ተናግረዋል ሲል በሐማስ የሚመራው አል-አስቃ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

የሐማስ ነባር ቃል-አቀባይ የሆኑት ሳሚ አቡ ዙሪ የመሪው ሃኒያን ግድያ “ግቡን ያልመታ ግድያ ነው። እንደውም ግጭቱን ሊያባብሰው የሚችል ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል አስነብቧል።

ዙሪ አክለው “እየሩሳሌምን ነፃ ለማውጣት ጦርነት እናውጃለን” ብለዋል ሲሉ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የዘገቡ ሲሆን ቡድኑ ይህን ለማድረግ “የትኛውንም ዋጋ ለመከፍል ዝግጁ ነው” ማለታቸው ተሰምቷል።

በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማዊያን በሐማሱ መሪ ግድያ ምክንያት ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የሰላም ድርድር ይመክናል የሚል ስጋት ይዟቸዋል።

በፍልስጤማዊያን ዘንድ ከፖለቲካ መሪነት ባለፈ የሰላም ድርድር ተወካይ ተደርገው የሚቆጠሩት ሃኒያ መገደላቸው ጋዛ ላሉ ፍልስጤማዊያን ከፍተኛ አንድምታ አለው።

የሐማስን ወታደራዊ ክንፍ ከሚመሩ ሌሎች መሪዎች በተነፃፃሪ ለዘብተኛ ናቸው የሚባሉት ሃኒያ ጋዛ በሚገኙ ፍልስጤማዊያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው መሪ ናቸው።

በስደተኛ ካምፕ ያደረጉት ሂኒዬህ በአውሮፓውያኑ 1948 ከፍልስጤም ግዛት የተፈናቀሉ በርካታ ፍልስጤማዊያንን የሚወክሉ ተደርገው ይቆጠራሉ።

በሰውዬው ግድያ ምክንያት በጋዛ ያለው ጦርነት የበለጥ ሊባባለስ የሚል ስጋት ጭሯል። ጦርነቱ ጋብ ሊል ይችላል የሚል ተስፋ የነበራቸው ሰዎችም ይህ ተስፋቸው የተሟጠጠ ይመስላል ሲል አል-ጀዚራ ዘግቧል።

የኢራኑ አቢዮታዊ ዘብ የሂኒዬህን ግድያ በተመለከተ “ምርመራ” መጀመሩን አስታውቋል።

አገዛዙ ባወጣው መግለጫ የሐማሱ መሪ ኢስማኢል ሃኒያ በኢራኗ ዋና ከተማ ቴህራን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሳሉ መገደላቸውን ተከትሎ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ኢስማኤል ሃኒዬህ ማን ናቸው?

በቅጽል ስማቸው አቡ አል-አቢድ የሚታወቁት ኢስማኢል ሃኒያ የሐማስ የፖለቲካ መሪ ናቸው።

ኢስማኢል አብደል ሳላም ሃኒያ የተወለዱት በፍልስጥኤማውያን የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው።

የሐማስ ፖሊት ቢሮ ኃላፊው ከ2006 (እአአ) ጀምሮ የአስረኛው የፍልስጥኤም መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።

ቀደም ሲል በእስራኤል ለሦስት ዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል።

ኢስማኢል ሃኒያ ወደ ጋዛ ተመልሰው የሐማስ መንፈሳዊ መሪ የሼክ አህመድ ያሲን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የፍልስጥኤም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ነበር።

ነገር ግን የሐማስ ቃሳም ብርጌድ በርካታ ሰዎች ከሞቱበት የአንድ ሳምንት ግጭት በኋላ የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት የማህሙድ አባስ ፓርቲ የሆነው ፋታህ ተወካዮችን ከጋዛ ሰርጥ በማባረሩ ፕሬዝዳንቱ በአጸፋው ለአንድ ዓመት ከቆዩበት የጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር ሃኒያን አባረሩ።

ኢስማኢል ሃኒያ ከሥልጣን መወገዳቸውን ተቃውመው ነበር። ከዚያም በኋላ ከፋታህ ጋር እርቅ እንዲወርድ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2017 ደግሞ የሐማስ ፖሊት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተመረጡ።

ሃኒያ በአሜሪካ መንግሥት ሽብርተኛ ተብለው ተፈርጀዋል።