የሱዳን መንግሥት በአሜሪካ ጥያቄ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ንግግር ለማድረግ ተስማማ

የሱዳን መሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሱዳን መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጦ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ጋር የሰላም ንግግር ለማድረግ ተስማማ።

የሰላም ንግግሩ የተዘጋጀው በአሜሪካ ሲሆን፣ በስዊትዘርላንድ የሚካሄድ ይሆናል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች ወደ ሰላም ንግግር ለመውሰድ የተደረጉ ጥረቶች ስኬታማ ሳይሆኑ ቆይተዋል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከተቆጣጠራቸው ከተሞች የማይወጣ ከሆነ የሰላም ንግግር እንደማይኖር የሱዳን መንግሥት ከዚህ ቀደም ገልጾ ነበር።

ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ለመነጋገር ስምምነት ላይ መድረሱን የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል። ለ15 ወራት የቀጠለው የእርስ በእርስ ጦርነት ማብቂያ ይሆናል የሚል ተስፋ አጭሯል።

ሐምሌ ላይ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተወካዮች ከተባበሩት መንግሥታት የሱዳን ልዩ ልዑክ ራምታኒ ላማራ ጋር ጄኔቫ ላይ ተገናኝተው ስለ ሰብአዊ እርዳታና ንጹኃን ዜጎችን ስለመጠበቅ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነበር።

ሆኖም ግን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪና የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ተወካዮች ወደ ጄኔቫም ይሁን ወደ ጅዳ፣ ሳዑዲ አረቢያ እንደማይሄዱ አስታውቀዋል።

በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፤ ሱዳን፣ ከአሜሪካ ባለሥልጣኖች ጋር የሰላም ድርድር ለማዘጋጀት ውይይት ለማካሄድ ጥያቄ አቅርባለች።

ሱዳን ትሪቢውን እንደዘገበው፣ የሱዳን መንግሥት ለሰላም ውይይቱ ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀመጠ ሲሆን ይህም ማን በውይይቱ ላይ መሳተፍ እንደሚችል ያካትታል።

ውይይቱ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነሐሴ 8/2016 ዓ.ም. እንደሚካሄድ በድረ ገጹ ያወጣው ዘገባ ይጠቁማል።

ሳዑዲ አረቢያ ከስዊትዘርላንድ ጋር የውይይቱ ተባባሪ አዘጋጅ እንደሆነችና፣ ውይይቱን የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና ግብፅ እንደሚታዘቡም አስታውቋል።