በህወሓት መካከል ከተፈጠረው ክፍፍል የትግራይ ኃይሎች ገለልተኛ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ

አቶ ጌታቸው ረዳ

የፎቶው ባለመብት, tplf/fb

የምስሉ መግለጫ, አቶ ጌታቸው ረዳ፡ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዝዳንት

የትግራይ ኃይሎች ክልሉን እያስተዳደረ ባለው ፓርቲ ውስጥ መከፋፈል ቢፈጠርም የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች ገለልተኛ ሆነው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ።

ይህ ጥሪ የቀረበው በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ለአንድ ቀን ያካሄደውን “ህወሓትን ማዳን” ያለውን ስብሰባ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው የአቋም መግለጫ ነው።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ምክትል ሊቀ-መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በሆኑት በአቶ ጌታቸው ረዳ የተጠራው “ህወሓትን የማዳን” ስብሰባ ሲጠናቀቅ ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

በአቋም መግለጫው እየተካሄደ ያለው የህወሓት ጉባኤ ሕጋዊ አይደለም፣ በጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎች ሕጋዊ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፣ ህወሓት ዳግም እንዲመዘገብ መደረጉ ‘ቅርቃር ውስጥ’ ከትቶታል የሚሉ እና የትግራይ ሕዝብ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆም የሚጠይቁ ነጥቦች ተካተዋል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውስጥ ለበርካታ አስርት ዓመታት ጉልህ ሚና ሲጫወት በቆየው ህወሓት ውስጥ ባሉ አመራሮች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንከር ያለ ክፍፍል መፈጠሩ ይታወቃል።

በአመራሮች መካከል ልዩነት ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል የፓርቲው ዳግም ምዝገባ እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየተካሄደ ያለው ጉባኤ ተጠቃሽ ናቸው።

በሊቀ-መንበሩ በእነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን ከእነ አቶ ጌታቸው ረዳ ፍላጎት እና ዕውቅና ውጪ የፓርቲውን 14ኛ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።

በአንጻሩ ትናንት እሑድ ነሐሴ 12 በፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ የተጠራ ስብሰባ በመቀለ ከተማ በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ ተካሂዷል።

በስበሰባው ላይ እነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በጠሩት የህወሓት ጉባኤ ላይ ታግደዋል የተባሉት ወደ 17 የሚጠጉ የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን ጨምሮ ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተወጣጡ የፓርቲው አባላት ተሳትፈዋል።

ለአንድ ቀን የቆየው ስብሰባ ሲጠናቀቅ በወጣው የአቋም መግለጫ ላይ ምንም እንኳ ክልሉን እያስተዳደረ ባለው ፓርቲ ውስጥ መከፋፈል ቢኖርም የትግራይ ኃይሎች ግን ገለልተኛ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።

በዚህም የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች አባላት “በፓርቲያችን ውስጥ ያለውን የሃሳብ ልዩነት ወደ ጎን በመተው የሕዝባችንን ደኅንነት እና ሰላም ለማረጋገጥ በገለልተኝነት እንድትቆዩ” በማለት ከየትኛውም ወገን ጎን እንዳይ ቆሙ ጠይቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ከሰብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ባወጣው መግለጫ በክልሉ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ከፍተኛው የክልሉ አስተዳር የሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ያለው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር ነው በማለት ክልሉን መልሶ በመገንባት ሂደት ሕዝቡ ከጎኑ እንዲቆም ጠይቋል።

በህወሓት አመራሮች መካከል ለተፈጠረው ልዩነት አንዱ ምክንያት የሆነው የፓርቲው ዳግም ምዝገባ እንዲሁ በአቋም መግለጫው ተጠቅሷል።

በእነ ጌታቸው የሚራው ቡድን ህወሓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዳግም እንደ አዲስ ፓርቲ መዝገቡ “ቅርቃር ውስጥ” እንዲገባ አድርጎታል ብሏል።

“ህወሓት ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝቶ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በዓለም ፊት ቢፈራረምም በግለሰቦች ኃላፊነት የጎደለው ተግባር በአዲስ ፓርቲነት እንዲመዘገብ በመደረጉ ቅርቃር ውስጥ ገብቷል” ይላል የአቋም መግለጫው።

በእነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እና ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር የሚመራው ቡድን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ የተሰረዘው የፓርቲው ሕጋዊ እውቅና እንዲመለስለት ሲጠይቅ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ በጸደቀው ማሻሻያ መሠረት ፓርቲውን የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነቱን መመለስ ስለማያስችል የህወሓት ጥያቄ ውድቅ ሆኖ ፓርቲውን “በልዩ ሁኔታ” ዳግም መመዝገቡ ይታወሳል።

ምርጫ ቦርድ እና የእነ አቶ ጌታቸው ስብስብ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው 14ኛው ጉባኤ ሕጋዊ አይደለም ያሉ ሲሆን፣ በጉባኤው የሚተላለፍ ውሳኔም ተፈጻሚ አይሆንም ሲል በአቋም መግለጫው አስታውቋል።

የእነ አቶ ጌታቸው ስብስብ ይህን ያለው ጉባኤው በ14ኛ ጌባኤ ያልተሳተፉ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በፓርቲው ውስጥ ከተራ አባልነት ያልዘለለ ኃላፊነት አይኖራቸውም ካለ በኋላ ነው።

“እየተካሄደ ያለው ጉባኤ ሕጋዊ አይደለም። . . . በጉባኤው የሚተላለፈው ውሳኔም ተፈጻሚ አይሆንም። . . . ጉባኤው ለአንድ ቡድን ጥቅም ሲባል እየተደረገ ያለ ነው። ሕገ-ወጥ ጉባኤውን ተከትሎ ለሚፈጠር ማንኛውም አደጋ ቡድኑ ኃላፊነቱን ይወስዳል” ይላል የአቋም መግለጫው።

ከዚህ በተጨማሪ በአቋም መግለጫው “ሰላም የፓርቲያችን እና የሕዝባችን ስትራቴጂያዊ ምርጫ ነው። ሕዝባችንን ወደ ጦርነት ለመመለስ ሴራ የሚፈጥር ማንኛውንም የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይል አጥብቀን እንቃወማለን። ሰላማችንን የሚያውኩትን ለመታገል ከመንግሥት፣ ከሕዝባችን እና ከፀጥታ ኃይላችን ጎን ለመቆም ተስማምተናል” ይላል።

ከዚህ ቀደም የእነ አቶ ጌታቸው ቡድን በእነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድንን ጦርነት ይጎስማል በሚል ይወቅሳል።

አቶ ጌታቸው ትናንት እሁድ ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባ ላይ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ “ጠዋት ማት በትንሽ በትልቁ ‘መክት’ እያሉ ጦርነት መጎሰም ትክልል አይደለም። በእኛ ላይ ጦርነት የሚያውጅ ካለ መዘጋጀት እንችላለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

በህወሓት ውስጥ የተከሰተውን ክፍፍል ተከትሎ በሕዝቡ ውስጥ ስጋት የተፈጠረ ሲሆን፣ በክልሉ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሁሉን አቀፍ ክልላዊ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠይቀዋል።