በአቶ ጌታቸው የሚመራው ቡድን “ህወሓትን ማዳን” ያለውን ስብሰባ ማድረግ ጀመረ

አቶ ጌታቸው ረዳ

በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ምክትል ሊቀ-መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በአቶ ጌታቸው ረዳ የተጠራ “ህወሓትን የማዳን” የተባለ ስብሰባ በመቀለ ውስጥ መደረገ ጀመረ።

ዛሬ እሁድ ነሐሴ 12/2016 ዓ.ም. በከተማው በሚገኘው የክልሉ ምክር ቤት የስብሰባ አዳራሽ እየተደረገ ያለው ስብሰባ “ህወሓትን ለማዳን የሚመጥን ሥራ መሠራት አለበት” በሚል አጀንዳ መሆኑን የቢቢሲ የመቀለ ወኪል ዘግቧል።

በዚህ “ህወሓትን የማዳን” ሰብሰባ ላይ ወደ 17 የሚጠጉ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት ተሳታፊዎች ናቸው።

እነ አቶ ጌታቸው ረዳ ይህን ስብሰባ እያደረጉ ያሉት የህወሓት ሊቀ-መንበር በሆኑት በእነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራ ቡድን እያካሄደ ባለው ጉባኤ፤ አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ወደ 17 የሚጠጉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከፓርቲው ከፍተኛ አመራርነት ካገደ በኋላ ነው።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውስጥ ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት ጉልህ ሚና ሲጫወት በቆየው ህወሓት ውስጥ ባሉ አመራሮች መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንከር ያለ ክፍፍል ተፈጥሯል።

በአመራሮች መካከል ልዩነት ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል የፓርቲው ዳግም ምዝገባ እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየተካሄደ ያለው ጉባኤ ተጠቃሽ ናቸው።

በሊቀ-መንበሩ በእነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን ከእነ አቶ ጌታቸው ረዳ ፍላጎት እና ዕውቅና ውጪ የፓርቲውን 14ኛ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።

በዚህ ጉባኤው ላይ ሳይገኙ የቀሩ የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የፓርቲው ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት በተራ አባልነት ከመቀጠል ውጪ ሌላ ኃላፊነት እንደሌላቸው ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም. በወጣ መግለጫ ተገልጿል።

የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች የዚህ ጉባኤ ተሳታፊዎች አይደሉም።

በጉባኤው ተሳታፊ ያልሆኑ አባላት ከከፍተኛ የፓርቲ ኃላፊነታቸው ታግደዋል መባሉን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በድርጅቱ ሊቀ-መንበር (ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል) የሚመራው ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመንጠቅ ሙከራ ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።

አቶ ጌታቸው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫቸው “ከጀርባችን ደጀን ይሆነናል፣ ይደግፈናል በሚሉት ባልታወቀ የውጭ ኃይል ተማምነው” አራት የድርጅቱ አመራሮች እንዲካሄድ የወሰኑት ጉባኤ “ወዳልተፈለገ ችግር ሊያመራን ይችላል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

እነ አቶ ጌታቸው ረዳ እያካሄዱት ያለው ስብሰባ
የምስሉ መግለጫ, እነ አቶ ጌታቸው ረዳ እያካሄዱት ያለው ስብሰባ

“የፖለቲካውን ሁኔታ የሚመልስ ወሳኝ ሰብሰባ”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ እሁድ ነሔሰ 12/2016 ዓ.ም. የጠሩት ስብሰባ የህወሓትን እና የክልሉን ሁኔታ ወደነበረበት ለመመለስ “ጊዜውን የጠበቀ እና አስፈላጊ” ነው ብለዋል።

አቶ ጌታቸው “ሰላም የሕዝባችን ዋነኛ ጉዳይ ስለሆነ አማራጭ የሌላው አስፈላጊ ነገር ነው” ካሉ በኋላ፤ “ጠዋት ማት በትንሽ ትልቁ ‘መክት’ እያሉ ጦርነት መጎሰም ትክልል አይደለም። በእኛ ላይ ጦርነት የሚያውጅ ካለ መዘጋጀት እንችላለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

በእነ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ቡድን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ወግነዋል በሚል የሚተቹት የክልሉ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “እንንበርከክ ያለ ሰው የለም” ካሉ በኋላ፤ “ከሰላም ወጪ ሌላ አማራጭ ስላሌለ በተቻለ መጠን ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት አለብን” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው በጠሩት ሰበሰባ ላይ በህወሓት ጉባኤ ታግደዋል የተባሉት ወደ 17 የሚጠጉ የማዕከላዊ ኮሚቴ እና የፓርቲው የቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን ጨምሮ ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተወጣጡ የፓርቲው አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

እነ አቶ ጌታቸው ይህን ሰብሰባ በመቀለ በክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ እያደረጉ ያሉት የህወሓት ጉባኤ በሰማዕታት አዳራሽ ለስድስተኛ ቀን ቀጥሎ እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።

በህወሓት አመራሮች መካከል ልዩነት ከፈጠሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ አሁን እየተካሄደ ያለው የፓርቲው 14ኛ ጉባኤ ነው።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጉባኤ የህወሓትን ሕገ ደንብ እና ሌሎች የአገሪቱ ሕጐችን ያላከበረ እንዲሁም የትግራይ ክልል ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው በማለት ይተቻሉ።

በእነ ደብረጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን ግን በትግራይ እና በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውሶች ለመፍታት ጉባኤ ማካሄዱ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ይላል።