ስዊትዘርላንድ ከሐይቆቿ የጥይት ክምችት ለሚያወጣላት ከፍተኛ የዶላር ሽልማት ያዘጋጀችው ለምንድነው?

በውብ ሐይቆቿ ውስጥ ጥይቶች አሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ስዊዘርላንድ በውብ ሐይቆቿ ውስጥ ብዙ ሺህ ቶን ጥይቶች አሉ

ስዊትዘርላንድ ፖስትካርድ ፎቶ ነው የምትመስለው። ዉብ ሐይቆቿ የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው።

ይሁንና በነዚህ ሐይቆች ሥር የማይጠበቅ ነገር ተከማችቷል፤ ጥይቶች፤ ሙሉ በሙሉ ያልመከኑ ተተኳሾች።

ከነዚህ የሚያማምሩ ሐይቆቿ መካከል ሉሰርን፣ ኒውቻቴል ወይም ተን በውስጣቸው ጥይቶችን መያዛቸው ተደርሶበታል።

ለዓመታት የስዊዝ መከላከያ ያረጁ ጥይቶችን ወደ ሐይቆቹ ነበር የሚደፋቸው። ይህን የሚያደርገው ከክፋት አልነበረም። በዚያው ይበሰብሳሉ፤ ለአካባቢ ጥበቃም ጥሩ ነው ብሎ ያምን ስለነበረ ነው።

በኃላ ላይ የተደረጉ ምርምሮች ግን ነገሩ አደጋ እንዳለው ደረሱበት።

በሉሰርን ሐይቅ ብቻ 3ሺህ 300 ቶን (3.3 ሚሊዮን ኪሎ ግራም) የሚመዝን ጥይት ክምችት እንዳለ ይገመታል። በኒውቻቴል ደግሞ ከ4500 በላይ ቶን ይኖራል።

ጥይቶቹ የሚገኙበት ጥልቀት ከ150 እስከ 220 ሜትር ይዘልቃል። በአንዳንድ ኃይቆች ደግሞ በ6 እና 7 ሜትር ጥልቀት ሊገኝ ይችላል።

አሁን የስዊዝ መከላከያ ሚኒስቴር እነዚህን ጥይቶች ከሐይቆቹ ለማውጣት ሁነኛ መላ ለሚያመጣ 50ሺህ የስዊዝ ፍራንክ ( 57ሺህ ዶላር ይጠጋል ) እሸልማለሁ ብሏል።

ጥይቶቹን ከሐይቁ ለማውጣት ለሚያስችሉ ሦስት ምርጥ ሐሳቦች ነው ይህ ሽልማት የተዘጋጀው። ነገር ግን ጥይቶቹን የማውጣቱ ተግባራዊ ሂደት ቢሊዯን ዶላሮችን ሊፈጅ ይችላል።

ምናልባት ስዊትዘርላንድ ወደ ኖርዌይ፣ ዴንማርክና ዩናይትድ ኪንግደም በመጠጋት ልምድ አካፍሉኝ ማለት ይጠበቅባታል። ነገሩ እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም።

በቀድሞ ጊዜ ጊዜ ያለፈባቸውን ጥይቶች ወደ ሐይቅ መጣል እንደ ጥሩ ተግባር ይታይ ነበር

የፎቶው ባለመብት, vbs

የምስሉ መግለጫ, በቀድሞ ጊዜ ጊዜ ያለፈባቸውን ጥይቶች ወደ ሐይቅ መጣል እንደ ጥሩ ተግባር ይታይ ነበር

ሌላው ሐይቅ ብሪያንዝ ነው። በዚያም እንዲሁ ብዙ ክምችት እንዳለ ተደርሶበታል።

በነዚህ ሐይቆች እስከዛሬ የጥይት ክምችቶች እንዳሉ ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም። ነገር ግን አደጋ ናቸው ተብሎ መታሰብ የተጀመረው በቅርቡ ነው።

ይበሰብሱና ከሐይቁ ጥልቅ መክነው ወደ ምንምነት ይቀየራሉ የሚል እሳቤ ነው የነበረው-ለረዥም ዘመን።

አንድ ማርቆስ ቡሰር የተባሉና ጡረታ ከወጡ ዘለግ ያለ ጊዜ የሆናቸው የስዊዝ ጂኦሎጂስት ይህ መላምት ሐቅ እንዳልሆነ ደረሱበት። እሳቸው ናቸው አደጋውን የተመለከተ ጥናት ለመጀመርያ ጊዜ ያሳተሙት።

ይህን ተከትሎ ጉዳዩ የሕዝብ መነጋገሪያ ለመሆን በቃ።

መንግሥትን የሚያማክሩት የከርሰ ምድር ባለሙያው ማርቆስ ቡሰር ይህን ጥናት ካሳተሙ 10 ዓመት አልፏቸዋል።

ለዚህ ሁሉ ጊዜ መንግሥት ምን ይሻላል ሲል ቆዝሞ ነው የቆየው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እሳቸው እንደሚሉት ጥይቶቹ ሁለት አደጋ አላቸው። አንዱ ምንም እንኳ ውሃ ውስጥ ቢሆኑም ሊፈነዱ የሚችሉበት ዕድል አለ። ምክንያቱም መከላከያ ወደ ኃይቆቹ ሲደፋቸው አንዳንዶቹ አልመከኑም።

ሌላው አደጋ የአፈርና የዉሃ ብክለትን ያስከትላሉ። የሐይቁን ዉሃና የሐይቁን ወለል ቲኤንቲ የተባለ ከፍተኛ መርዛማነት ያለው የጥይቱ አካል ሊበክለው ይችላል።

የስዊዝ መከላከያ እንዲህ ዓይነት ቸልተኝነት የተሞላበት ድርጊት እንዴት ሊፈጽም ቻለ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ቢሆንም ይህ ዓይነቱ ድርጊት ግን የመጀመርያው አይደለም።

ሚቶሎዝ የተባለው አካባቢ ለምሳሌ በፈረንጆቹ በ1947 ከፍተኛ ፍንዳታ ተከስቷል። በዚያ አካባቢ በሚገኝ ተራራ የተከማቸው 3ሺህ ቶን የሚመዝን ጥይት ፈንድቶ ነው ይህ ፍንዳታ የተከሰተው።

ፍንዳታው የ9 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን ያቺ የገጠር መንደር ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወድማለች። ፍንዳታው ከዙሪክ ርቆ 160 ኪሎ ሜትር ድረስ ይሰማ ነበር።

የሚቶልዝ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ታዲያ ፍንዳታውን ተከትሎ አካባቢው እስኪጸዳ ለ10 ዓመት ሌላ ቦታ ሄዶ ለመስፈር ተገደዋል።

ከሦስት ዓመት በፊትም እንዲሁ መከላከያ ከ3500 ቶን በላይ የሚመዝን ያልፈነዳ የጦር መሣሪያ ክምችት በተራራ ሥር ተቀብሮ ማግኘቱና ይህም አደጋ ደቅኖ እንደነበር አምኗል።

በብዙ ጦርነቶች ገለልተኛ አቋም በመውሰድ የምትታወቀው ስዊትዘርላንድ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አደጋ ከመጣ ራሷን ለመከላከል አንዳንድ ድልድዮቿን እና መሻለኪያዎችን ቦምብ አጥምዳባቸው እንደነበር ታውቋል።

እነዚህ ድልድዮችና መሿለኪያዎች በፍጥነት የተጠመዱባቸው ቦምቦች በጥንቃቄ መምከን ነበረባቸው፤ ምክንያቱም በአካባቢያቸው ከፍተኛ ተሽከርካሪ ሲያልፍ ሊፈነዱ የሚችሉበት አጋጣሚ ስለነበረ ነው።

በእአአ 2011 ለምሳሌ በጉታርድ መሿለኪያ ሁለት ከባድ ተሽከርካሪዎች ተጋጭተው በተፈጠረ እሳት 11 ሰዎች ሞተዋል።

በዚያ አቅራቢያ ታዲያ የጥይት ማከማቻ ነበር። የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን ለማጥፋት ባይችሉ አደጋው የከፋ ይሆን እንደነበር ይነገራል።

አንዱ ፈተና የሆነው ስዊትዘርላንድ በጦርነቶች ገለልተኛ ሆኖ የሚቆይ መከላከያ ቢኖራትም ባሕር በር በሌላት አገር እና በርካታ ሠራዊት ኖሯት በስልጠናዎች ጊዜ ጥይቶችን የማስወገጃ ብዙ አማራጭ የላት ይሆናል።

ስዊትዘርላንድ ሁሉም ዕድሜያቸው 18 የደረሱ ወንዶች የወታደራዊ ስልጠናና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለባቸው። ሁሉም ሰው የሚሰለጥነው ደግሞ በዚያው ብዙ ሕዝብ በሚኖርበት ቦታ ነው።

አሁን እነዚህን ጥይቶች ከውብ ሐይቆቿ የማስወገዱ ተግባር ተጀምሯል። ይሁንና ረዥም ጊዜ፣ ብዙ ገንዘብና ውስብስብ ሂደትን የሚፈልግ እንደሆነ ይጠበቃል።

አሁን የሚጠበቀው አንድ ባለ ብሩህ አእምሮ ሰው በሆነ ተአምር ብቅ ብሎ ይህን የጥይት ክምችቱን የማስወገድ ተግባርን ጥበብ በተሞላበት መንገድ እንዴት መፈጸም ይቻላል የሚለውን ሐሳብ ይዞ እንዲመጣ ነው።

ድንቅ ሐሳብ አለኝ የሚል ዜጋ እስከሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት የካቲት ወር ሐሳቡን ያቅርብ ተብሏል። በሚያዝያ ወር ደግሞ የሦስቱ አሸናፊ የሚባሉ ሐሳቦች ለሕዝብ ይፋ ይሆናሉ።

የስዊዝ ፍራንክ ሽልማቱም ያኔ ይበረከትላቸዋል።