ልጃቸው እንዲገደል ለፍርድ ቤት ያመለከቱት ምስኪን እናት

የፎቶው ባለመብት, BBC/Rana family
እንዴት የወለደ አንጀት “ልጄ ይገደልልኝ” ትላለች?
እናት ኒርማላ ራና ግን አድርገውታል። ምን ያድርጉ። የልጃቸው ስቃይ ማብቂያ አጣ።
እናት 60 ዓመት ደፍነዋል። ይገደልልኝ የሚሉት ልጃቸው አልጋ ላይ ተኝቷል። በዕድሜ የእሳቸውን ግማሽ ነው።
ሮጦም ኖሮም ሳይጠግብ ከዕለታት አንድ ቀን ሕይወቱ ጨለመ።
የኢንጂነሪንግ የኮሌጅ ተማሪ ነበር። ኮሌጅ ውስጥ ከ4ኛ ፎቅ ወደቀ። ጭንቅላቱ ክፉኛ ተጎዳ። ነፍሱ ግን ተረፈች።
ምናለ ነፍሱ ባልተረፈች በሚያስብል ደረጃ ነበር የተጎዳው።
የዚህ የ30 ዓመት ወጣት ስም ሐሪሽ ይባላል።
እናት፣ አባት እና ልጅ በሰሜን ሕንድ ቻንዲጋር ግዛት ነበር የሚኖሩት። በአውሮፓውያኑ 2013 በቤተሰቡ ላይ መቅሰፍት ወረደ።
ልጃቸው ሐሪሽ ላለፉት 11 ዓመታት አልጋ ላይ ነው። አይናገር-አይጋገር።
እሱ ያለበትን ሁኔታ ሐኪሞች በእንግሊዝኛው ቬጀቴቲቭ ስቴት (vegetative state) ይሉታል። ከሞት በላይ ከመኖር በታች ያለ ሁኔታ ነው። ሞቶ በሕይወት እንደመቆየት ያለ ስሜት ነው። ሰመመን አይደለም። ይለያል።
ለምሳሌ ሐሪሽ መናገር አይችልም። ሰውነቱ ደቋል። ፊቱ ጉድጉዷል። በአንጥንት ነው የቀረው። ሲያዩት የጣዕረ ሞትን ያህል ያስደነግጣል።
ግን ደግሞ ነፍሱ አለች። ከእናቱ ጋር በዐይን- ጥቅሻ ይግባባሉ። ለ11 ዓመታት ከሆስፒታል አልወጣም።
አባቱ አሾክ፣ “ያልወሰድነው ሆስፒታል የለም። ወላ የግል፣ ወላ የመንግሥት፤ አንዱም አልሠራልንም” ይላሉ።
“በተአምር እናምናለን። በመድኃኒትም እናምናለን። በጸሎትም እናምናለን። ጸሎትም፣ ተአምርም፣ መድኃኒትም ግን አልሠራልንም።”
ወጣቱ ሐሪሽ ከተኛበት የሆስፒታል አልጋ በላይ አንድ የግድግዳ ሰዓት ይታያል። የደቂቃው ቀስት ቋ-ቋ እያለ ይቆጥራል።
ከአልጋው በጎን በኩል ደግሞ የመንፈሳዊ ቀናትን የሚያመላክት ካሌንደር ተሰቅሏል። እሱም ቀናት ይቆጥራል። ለሐሪሽ እናቱ እና አባቱ ግን ቀንም ሰዓትም ከቆመ 11 ዓመት ሆኗል።
በዚህ በሕክምና ‘ቬጄቴቲቭ’ ተብሎ በሚጠራ ደረጃ ያሉ ተማሚዎች ጥልቅ ሰመመን (ኮማ) ውስጥ አይደሉም። ነቅተው ነው ያሉት። አካባቢያቸው ምን እንደሚከናወን ግን አያውቁም። ግራ የሆነ ነገር ነው።
እናት እና አባቱ ላለፉት 11 ዓመታት ሐሪሽን ሲንከባከቡት ነበር።
እናት ሌላ ሕይወት የላቸውም። ልጃቸውን ሲያጸዳድዱት፣ ልብስ ሲቀይሩለት፣ ዐይን ዐይኑን ሲመለከቱት ነው መሽቶ የሚነጋው።
ላለፉት 11 ዓመታት ይህንኑ ተደጋጋሚ ነገር እያደረጉ አሉ።
የሚደንቀው ደግሞ የአልጋ ቁራኛው ሐሪሽ ይህ አደጋ ሳይደርስበት የክብደት አንሺ ስፖርተኛ ነበር። ጡንቻው የፈረጠመ ንቁ ልጅ።
ምህንድስና ተማሪም ነበር። አሁን የ30 ዓመት ወጣት ሳይሆን አንድ ሐሙስ የቀረው ሽማግሌ መስሏል። ሥጋው አልቆ በአጥንት ቀርቷል።
ታዲያ ለምን ይኖራል? የእናቱም የሰሞኑ ጥያቄ ይኸው ነው። ልጄን ግደሉልኝ የሚሉት ወደው አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, BBC/Rana family
“ልጄን ገድላችሁ ከስቃዩ ገላግሉልኝ” እናት
እናት ኒርማላ የዕንባ ከረጢታቸው ደርቋል። “ማልቀስ ከረሳሁ ዘመን የለውም” ይላሉ።
የነበራቸውን ጥሪት ልጃቸውን በመንከባከብ ጨረሱት። የሚላስ የሚቀመስ ሲጠፋ በመጨረሻ ቤተሰቡ ተማከረ።
ተስፋ ከሌለው ልጃችን በከንቱ ለምን ይሰቃያል? ቢሞትና ቢገላገልስ? ብለው ተማከሩ። ወሰኑ። ቀላል ውሳኔ አልነበረም።
የአልጋ ቁራኛው ሐሪሽ፣ ዩታኔዣ (euthanasia) ለሚባለውና ስቃይ ላይ ያሉ ሰዎችን በስምምነት እስትንፋሳቸውን ማቆም የሚቻልበትን ዕድል የሚሰጠውን “የርህራሄ ግድያ” እንዲያገኝ ጠየቁ።
በዩታኔዣ ታማሚዎች የሚገደሉት በስቃይ የለሽ መርፌ ተወግተው ነው።
ቤተሰባቸውን ተሰናብተው ወደው እና ፈቅደው ይሸኛሉ። ወይም ደግሞ ቤተሰብ ለእነርሱ መልካሙ ነገር ይህ ሆኖ ሲሰማው ይወስናል።
መርፌውን በተወጉ በሰከንዶች ውስጥ ያሸልባሉ።
በዕድሜ ዘመን ስቃይ የሚቃትቱ ሰዎች ይህን የርህራሄ ግድያን ይመርጣሉ። መድኃኒት ባልተፈጠረለት በሽታ የታመሙ ሰዎችም እንዲህ ያደርጋሉ።
ጥቂት የአውሮፓ አገራት ይህን “የርህራሄ ግድያ” ተግባር ሕጋዊ አድርገውታል።
በሌሎች በበርካታ አገራት ግን ወንጀል ነው።
ስለዚህ የሐሪሽ እናት ፍርድ ቤት ማመልከት ነበረባቸው። ልጄ በርህራሄ ግድያ እስትንፋሱን አቁሙልኝ ብለው አመለከቱ።
“በቃኝ፤ አለቅኩ-ደቀቅኩ፤ እኔ ብሞት ማን ይንከባከበዋል? አንድኛውን ይረፍና የሰውነት አካሉን በሕይወት መቆየት ለሚፈልጉ በችሮታ እንሰጣለን። እሱም ሰላም ያገኛል፣ እኛም የእሱ አካል በተለገሳቸው ሰዎች ውስጥ እሱን እያየን እንጽናናለን” ብለዋል እናት።
እናት በማይጨከነው ቢጨክኑም የደልሒ ፍርድ ቤት ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል።
ፍርድ ቤት “ታማሚው ወጣት በሕይወት ያለው በመካኒካል መንገድ ብቻ ቢሆን የእናቱን የልጄን ግደሉልኝ ጥያቄ እንቀበል ነበር። ነገር ግን ያለ ውጫዊ ድጋፍ በሕይወት መቆየት ስለሚችል ጥያቄውን ውድቅ አድርገናል” ብሏል።
“ምንም እንኳ “የርህራሄ በጎ ፈቃድ ግድያ” ዓላማው ታማሚውን ከስቃይ ለመታደግ ቢሆንም በሕይወት መቆየት እየቻለ ነፍሱን ማጥፋት ወንጀል ነው” ሲል ይነበባል፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ።
ይህን የፍርድ ቤት ውሳኔ የተቃወሙት ቤተሰቦች በተለይም እናቱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት ብለዋል።
በሕንድ የርህራሄ ግድያ (ዩታኔዣ) አይፈቀድም። ሆኖም ግን የተዘዋዋሪ የርህራሄ ግድያ ሊፈቀድ ይችላል።
ይህም ማለት ለምሳሌ ታማሚውን ምግብ በመከልከል ሊሆን ይችላል። ፍርድ ቤት የሚለው “በውጫዊ ሜካኒካዊ እርዳታ ስላልሆነ ወጣቱ በሕይወት የቆየው፣ እስትንፋሱ ሊቆም አይገባም” ነው።
ነገር ግን እናት አቤት ብለዋል። “ልጄ ምግብ የሚወስደው በሆዱ በኩል በተቀበረ ቱቦ ነው። ይሄ ማለት ሜካኒካዊ ነው። የተቀበረው ቱቦ ከእርሱ ጋር የተወለደ አይደለም” ሲሉ ተከራክረዋል።

የፎቶው ባለመብት, BBC/Rana family
ነሐሴ ያቺን ሰዓት
ዕለቱ ነሐሴ 5/2013 (እአአ) ነበር። የአባቱ አሾክ ራና ስልክ ጠራ።
“ልጅዎ መጠነኛ አደጋ ደርሶበታልና ቶሎ ይድረሱ” ተባሉ።
ወደ ሆስፒታል በረሩ።
“ስንደርስ ሐኪሙ የልጃችሁ የጭንቅላቱ ነርቮች ጨርሶ ደርቀዋል አለን” ይላሉ ከ11 ዓመት በፊት ያቺን የተረገመች ቀን በማስታወስ።
ሐሪሽ ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ምግብ አያላምጥም። በሆዱ በኩል በተቀበረ ቱቦ ነው ምግብ በፈሳሽ መልክ የሚደርሰው።
ይህ ደግሞ ቤተሰቡን በወር 15 ሺህ ሩፒ ያስወጣል። አሁን ወርሃዊ የሆስፒታል ወጪ ቤተሰቡን ፈትኖታል። 30 ሺህ ሩፒ በወር ያወጣል።
ቤተሰቡ እሱን ለማዳን ሲል ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። መኖሪያ ቤታቸውን ሽጠዋል። ከደልሂ ከተማ ወጥተው ወደ ትንሽዬ ገጠር ገብተው አንድ ክፍል ተከራይተው ለመኖር ተገደዋል።
አሁን ግን ባዶ እጃቸውን እየቀሩ ነው።
የአባት ወርሃዊ የጡረታ ብር 3600 ሩፒ ነው። ይህ ደግሞ እንኳን የሆስፒታል ወጪ ሊሸፍን፣ አስቤዛ አይገዛም።
ስለዚህ እናት ጎዳና መውጣት ነበረባቸው። ሳንድዊች እና በርገር ለመሸጥ። ቅዳሜ እና እሑድ ይህንኑ ያደርጋሉ።
አሁን ጥያቄው ያቀረቡት ይግባኝ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ከተደረገ ወላጆቹ ልጃቸውን ምን ሊያደርጉት ይችላሉ?
አባት፣ “መንግሥት በራሱ ሆስፒታል ልጃችንን ይንከባከብልን” እያሉ ነው። ለጊዜው ያላቸው አማራጭ ያ ብቻ ነው።
በአሜሪካ 11 ግዛቶች ዩቴኔዣ (የርህራሄ ግድያ) ይፈቀዳል። በአውሮፓ ደግሞ ስዊትዘርላንድ እና ስፔን ፈቅደዋል።
አውስትራሊያም ከእነዚህ አገራት ትመደባለች።
ከዚያ ባሻገር ባሉ አገራት ግን ድርጊቱ ሕገ ወጥ ነው።
ኒርማና ራና ልጄ አንድ ቀን ይድናል ብለው ከአንጀታቸው ያምኑ ነበር።
ቀኑ ሳምንት ሆነ። ሳምንቱ ወር ሆነ። ወሩ ዓመት ሆነ። ዓመቱ ዓመታትን ወለደ። ምንም አዲስ ነገር የለም። እምነታቸው ተሸረሸረ። ስቃያቸው በዛ።
እናት የልጃቸው ትዝታ አሁንም በዐይናቸው ላይ ይዞራል፤ “ትዝ ይለኛል ቤት ውስጥ ሲሯሯጥ፣ ክብደት ሲያነሳ - ‘እማዬ፣ እማዬ ጡንቻዬን እይውማ እንዴት እንደፈረጠመልኝ’ ሲለኝ” ይላሉ ኩርምት ብለው።
አያነቡም። የእንባ ከረጢታቸው ደርቋል። አሁን እናት ጸሎታቸው አንድ እና አንድ ብቻ ነው።
“አምላኬ ሆይ! በቃኝ! ልጄን ውሰድልኝ።”












