በዓለም ራሳቸውን የሚያጠፉ በርካታ ሰዎች ያሉባት ትንሿ አፍሪካዊት አገር

ከዋናው መንገድ ፊት ለፊት የሚታየው ጉልበት የሚያዝል ተራራማ መንገድ ወደ 79 ዓመቷ አዛውንት ቤት ይወስዳል።
ማታሎሃንገ ሞሎኢ የተባሉት አዛውንት የዓለም ‘ከፍታ’ በምትባለው ሌሶቱ በተራራዎች በተከበባ መንደር ውስጥ ይኖራሉ።
ሞሎኢ 10 ልጆችን ወልደዋል። ትሎሃንግ ስለሚባለው የመጀመሪያ ልጃቸው ይናገራሉ።
የሞሎኢ የመጀመሪያ ልጅ በ38 ዓመቱ ልክ እንደ በርካታ የአገሩ ሰዎች የራሱን ሕይወት አጠፋ።
በከፍታዋ ምክንያት በሰማይ ላይ ያለችው አገር የሚል ስያሜ ያላት፤ በዓለም ላይ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያጠፉባት ቀዳሚ አገር ነች - ሌሶቱ።
“ትሎሃንግ በጣም ጥሩ ልጅ ነበር። ስለ አእምሮ ሕመሙ ይነግረኝ ነበር” ይላሉ ማታሎሃንግ በሞት ስላጡት ልጃቸው ሲናገሩ።
“ሕይወቱን ባጠፋበት ቀን ወደ እኔ መጥቶ ‘እናቴ አንድ ቀን እራሴን እንዳጠፋሁ ትሰሚያለሽ’ አለኝ። የልጄ ሞት በጣም ነው የጎዳኝ። ይረብሸው ስለነበረው ነገር በዝርዝር በነገረኝ እያልኩ እብሰለሰላለሁ” የሚሉት እናት ልጃቸው ስሜቱን ለሰዎች መግለጽ ያልፈለገው ሊደርስበት የሚችለውን ትችት በመፍራት እንደሆነ ይገልጻሉ።
“ስለ ህመሙ፤ ስለ ጭንቀቱ ብናገር ሰዎች የራሱን ችግር መፍታት እንደማይችል ሰው ይመለከቱኛል ብሎ ፍርቶ ነው” ይላሉ የ79 ዓመቷ እናት።
እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ከሆነ በሌሶቱ በየዓመቱ ከ100 ሺህ ሕዝብ 87 የሚሆኑት እራሳቸውን ያጠፋሉ።
ይህ አሃዝ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የምንረዳው በተቀረው ዓለም ከ100 ሺህ ሕዝብ እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ከሌሱቶ በ10 እጥፍ ዝቅ ማለቱን ስንመለከት ነው።

ሄልፕሌሶቱ የተባለው ዓይነት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የአገሪቱ ወጣቶች የአእምሮ ጤናቸውን መጠበቅ የሚያስችላቸውን ክኅሎት ለማስጨበጥ ጥረት እያደረጉ ነው።
ከመዲናዋ ማሴሩ የሁለት ሰዓት የመኪና መንገድ ርቃ በምትገኘው ሃሎትሴ ከተማ አንድ ባለሙያ ስለ አእምሮ ጤና ገለጻ እየሰጠ ነበር።
ከተሳታፊዎቹ መካከል አንዷ ሦስት ጓደኞቿ እራሳቸውን ማጥፋታቸውን እና እርሷም ብትሆን ሕይወቷን ለማጥፋት ሞክራ እንደነበረ ትናገራለች።
ወጣቷ ሁሉም ሰው እራስን ስለማጥፋት አስቧል ወይም እራሱን ያጠፋ ሰው ያውቃል፤ ነገር ግን ስለጉዳዩ በድፍራት ለመናገር እንፈራለን ትላለች።
ሌላኛዋ ተሳታፊ ለሕክምና በገባችበት ሆስፒታል እንዴት በአንድ ሐኪም እንደተደፈረች ስሜታዊ ሆና ለሌሎች ትናገራለች።
“ዶክተሩ ቆንጆ እንደሆንኩ ነገረኝ። ከዚያ ሸጉጥ አውጥቶ ከእኔ ጋር መተኛት እንደሚፈልግ ነገረኝ። እምቢ ካልኩት እንደሚገድለኝ አስፈራራኝ። ሁሌም እራሴን ማጥፋት ብቸኛው መፍትሄ አድርጌ እወስዳለሁ፤ ግን ይህን ማድረግ አልቻልኩም። እስካሁን በሕይወት እንድቆይ ያደረገኝ የወንድሞቼ ነገር ነው። ታናናሽ ወንድሞቼ ጠንካራ አድርገው ይመለከቱኛል፤ እኔ ግን በጣም ደካማ ሴት ነኝ።”

ተሳታፊዎች በእንደዚህ ዓይነት ስብስቦች ውስጥ ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጻቸው እረፍት እንደሚሰጣቸው እና ‘ብቻዬን አይደለሁም’ ብለው እንዲያስቡ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ።
ወጣቶች በአንድ ተሰብስበው ሐሳባቸውን እንዲለዋወጡ የሚያመቻቹት ሊኔኦ ራፎካ ሰዎች እራሳቸውን የሚያጠፉበት መንገድ በርካታ ቢሆንም፤ በሌሶቱ ብዙዎችን የሚያመሳስል ነገር ግን አለ ይላሉ።
“ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው፣ ሥራ አጥ መሆን፣ በሞት ምክንያት የቅርብ ሰው ማጣት፣ አልኮል እና አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም” እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች የሚያመሳስሏቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ያስረዳሉ።
እአአ 2022 የተከናወነ አንድ ጥናት 86 በመቶ የሌሶቱ ዜጎች ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ደርሶባቸዋል። የዓለም ባንክ አሃዝ ደግሞ ከአምስት የሌሶቱ ዜጎች ሁለቱ ሥራ አጥ ናቸው ወይም ተማሪ አይደሉም።
“ከቤተሰብ ወይም ከጓደኛ በቂ የሆነ ድጋፍ እያገኙ አይደለም” የሚሉት ራፎካ፤ ብዙዎች ሰው ምን ይለኛል በሚል ፍራቻ ስለ አእምሮ ጤናቸው በነጻነት ከመናገር ይቆጠባሉ።
ከማኅብረሰቡ ሊደርስባቸው የሚችለውን መገለል ተቋቋመው እንኳ እርዳታ ፍለጋ ወደፊት የሚመጡ ደረጃውን የጠበቀ የአእምሮ ጤና ሕክምና አያገኙም።
በአገሪቱ ያለው አንድ የአእምሮ ጤና ተቋም ብቻ ነው። ይህ ተቋም መልካም ስም የለውም። አንድ ጥናት ታካሚዎች በሆስፒታሉ የሚኖሩበት ሁኔታ ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ ነው ብሏል።
የሌሶቱ መንግሥት ይህን የማኅብረሰብ የአእምሮ ጤና ቀውስ መፍትሄ ለመስጠት ብሔራዊ የአእምሮ ጤና ፖሊሲ እያዘጋጀው ነው ይላል።
የፓርላማ አባል እና የጤና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሞክሆቱ ማክሃላኘኔ፤ “የአእምሮ ጤና ችግር በአገሪቱ በወረርሽኝ መልክ ተስፋፍቷል” ይላሉ።
የምክር ቤት አባሉ መንግሥት ወጣቶች ስለ አእምሮ ጤና ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና የጤና ቀውስ ካጋጠማቸው እርዳታ እንዲጠይቁ ለማበራታት በትምህርት ቤቶች እና ወጣቶች ይገኙበታል በሚባል ስፍራ የማንቃት ሥራ እየሠሩ መሆኑን ይናገራሉ።

በዚያች ተራራማ የሌሶቱ መንደር የ79 ዓመቷ አዛውንት ከመጀመሪያ ልጃቸው መቃርብ አጠገብ ተገኝተዋል።
እራስን በማጥፋት ምክንያት የቀርብ የሚሏቸውን ከተነጠቁ ሰዎች መካከል አንዷ የሆኑ አዛውንት፣ ሐዘናቸው ሁሌም ጥልቅ ሆኖ እንደቀረ ይናገራሉ።
“አንድ ነገር ግን ለሰዎች መናገር እፈልጋለሁ” ይላሉ ሞሎኢ።
“እራስን ማጥፋት ፈጽሞ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ሊረዷችሁ ለሚችሉ ሰዎች ህመማችሁን ተናገሩ” በማለት የልጃቸው ሞት የሚያንገበግባቸው እናት ይመክራሉ።















