ለሕጻናት በጣም አስፈላጊ በሆነው ጡት ማጥባት ዙሪያ ያሉ 7 የተዛቡ አመለካከቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መርጃ ተቋም ዩኒሴፍ በቅርቡ ባወጣው ጥናት እንደጠቆመው በበቂ ሁኔታ የእናት ጡት አለመጥባት በዓመት 16 በመቶ የልጆች ሞትን ያስከትላል።
የዓለም ጤና ድርጅት ለሚያጠቡ እናቶች ማኅበረሰቡ እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ያበረታታል።
ለሚያጠቡ እናቶች ምቹ የጤና ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም ሴቶች በማንኛውም ቦታ እና ሁኔታ ውስጥ ሆነው የማጥባት መብታቸውን ማክበር የዚህ እንቅስቃሴ አካል ናቸው።
የነሐሴ የመጀመሪያው ሳምንት የዓለም ጡት የማጥባት ሳምንት ነው።
የዘንድሮው መሪ ቃል “ክፍተቱን ማጥበብ፡ የሚያጠቡ እናቶችን መደገፍ” ወይም 'Closing the gap: Breastfeeding support for all' ይሰኛል።
ጡት ስለማጥባት የተዛቡ አመለካከቶች ሴቶች ላይ ጫና ያሳድራሉ። ከተዛቡት አመለካከቶች መካከል የተወሰኑትን እንመለከታለን።
በሊቨርፑል ዩኒቨርስቲ የክሊኒካል ፋርማኮሎጂ እና ግሎባል ኸልዝ ፕሮፌሰር እንዲሁም በዩጋንዳ ማኬሬሬ ዩኒቨርስቲ የጥናት ባለሙያ ካትሪዮና ዌይት እንዲሁም በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለንደን ፕሮፌሰር አላስተር ሱትክሊፍ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
1. ጡት ማጥባት ያማል
ፕሮፌሰር ዌይት እንደሚሉት፣ መጀመሪያ አካባቢ ምቾት የሚነሳ ስሜት ቢኖርም የተለመደ ነው። የጡት ጫፍ አካባቢ ህመም ቢሰማም ይህ የሚለመድ ነው።
ሆኖም ጡት ማጥባት ከፍተኛ ህመም የሚያስከትል አይደለም። የጡት ጫፍ አካባቢ ያለ ሕመም የኢንፌክሽን ምልክት ወይም የልጅ በአግባቡ አለመጥባት ሊሆን ይችላል።
የተወሰነ ምቾት ማጣት የተለመደ ነው። በተለይ የመጀመሪያ ልጅ ለወለዱ እናቶች ለመልመድ ውስን ጊዜ ይወስዳል።

2. ቶሎ ልጅ ማጥባት ካልተጀመረ ማጥባት አይቻልም
ፕሮፌሰር ሱትክሊፍ እንደሚሉት፣ እናቶች ልጆቻቸውን እንዲያጠቡ ማበረታታት ከጤና እና ከሌሎችም ነገሮች አንጻር መልካም ነው።
ሆኖም በዚህ ተፈጥሯዊ ሂደት ላይ ሰው ሠራሽ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ ሳይንሳዊ መሠረት የለውም።
ልጆችን በፍጥነት ጡት እንዲጠቡ ማስጀመር ጠቀሜታ አለው።
አንደኛው ጨቅላዎቹ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘታቸው ነው። በተጨማሪም የማሕጸን የመኮማተር ሂደትን ያፋጥናል። ይህም ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የማሕጸን መድማትን የሚከላከል ነው።
ልጆች በተወለዱ በጥቂት ቀናት የእናት ሰውነት በፕሮቲን የበለጸገ ኮሎስትረም የተባለ ንጥረ ነገር ያመነጫል። ይህም ልጆች የመጥባት ሂደታቸውን የሚጀምሩበት ንጥረ ነገር ነው።
3. እያጠቡ መድኃኒት መውሰድ አይቻልም
ፕሮፌሰር ዌይት እንደሚሉት፣ ሁሉም እናቶች የሚወስዱት መድኃኒት ልጃቸውን ይጎዳ ይሆን ብላ ስጋት ያድርባቸዋዋል።
እውነታው ግን መድኃኒቶች በጡት ወተት በኩል ወደ ልጆች የሚደርሱት በውስን መጠን ነው። ሐኪሞች መድኃኒት መውሰድ ያስፈልጋል ካሉ መድኃኒቱን መውሰድ አደጋ አይሆንም ማለት ነው።
ልጆች በዋነኛነት የሚያስፈልጋቸው ጤናማ እናት ነው። አብዛኞቹ ለኢንፌክሽን፣ ድባቴ እና አጠቃላይ ህመም የሚሰጡ መድኃኒቶች አስጊ አይደሉም።
ጡት እያጠቡ የማይወሰዱ መድኃኒቶች ውስን ናቸው። እንደ ካንሰር ያሉ በጣም ከባድ ህመምን ለማከም የሚውሉትን ያካትታል።
ጥቅም እና ጉዳታቸው ከግምት መግባት ያለባቸው መድኃኒቶችም አሉ። ጡት እያጠቡ መድኃኒት የታዘዘላቸው እናቶች ሐኪማቸውን ማማከር አለባቸው።
ለጉንፋን እና ለብርድ ያለ ሐኪም ማዘዣ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ያላቸው ንጥረ ነገር የጡት ወተት መጠንን ሊቀንስ ይችላል።
በቅጠላ ቅጠል እና በሥራ ሥር ላይ የተመሠረቱ መድኃኒቶች በአግባቡ ስላልተጠኑ ውስጣቸው ምን እንዳለ ማወቅ ይከብዳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
4. ከማጥባት በፊት ቅመም የበዛበት ምግብ መብላት አይቻልም
ፕሮፌሰር ዌይት እንደሚሉት፣ ጡት እያጠቡ መመገብ የማይገባ ምግብ የለም። ሆኖም ግን አመጋገብ የጡት ወተት ይዘት ላይ ተጽዕኖ አለው።
የትኛው ምግብ ምን ውጤት እንዳለው መከታተል ያስፈልጋል። ፕ/ር ዌይት የራሳቸውን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ ይሰጣሉ።
ከልጆቻቸው አንደኛው የብርቱኳን ጭማቂን የመሰሉ ጭማቂዎች ጠጥተው ሲያጠቡ ልጃቸው ምቾች ያጣ ነበር።
ጎጂ የሚባል ወይም በሕክምና ስህተት ነው የሚባል እና መበላት የሌለበት ነገር ባይኖርም አመጋገብ የሚያመጣውን ለውጥ በቅርበት መከታተል ይቻል።

5. ፎርሙላ ተጠቅሞ ጡት ማጥባት አይቻልም
ፕሮፌሰር ዌይት እንደሚሉት፣ ጡት ማጥባት ከተፈለገ ፎርሙላ (የሕጻነት የዱቄት ወተት) መጠቀም አይቻልም የሚለው ነገር ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም።
ሆኖም የጡት ወተት በፍላጎትና አቅርቦት ላይ የተመሠረተ ነው። የእናቶች ሰውነት ለልጆች አስፈላጊ የሆነ የወተት መጠን ማምረት ይችላል።
ልጅ ጡት ሲጠባ በሰውነት ውስጥ የሚመነጭ ሆርሞን አስፈላጊውን የወተት መጠን ያመነጫል። የእናት ጡት ወተት የሚጠቡት ጨቅላዎች አንድም ይሁኑ መንታ ልጆች፣ ሰውነት አስፈላጊውን መጠን ወተት ያመነጫል።
ፎርሙላ ለልጆች መስጠት ከተጀመረ ወደ ሰውነት የሚተላለፈውን መልዕክት ያዛባል። ሰውነት ማምረት ስለሚገባው የወተት መጠን የሚተላለፍለት መልዕክት ይቋረጣል ማለት ነው።
የጡት ወተት አስቸጋሪ ሆኖ ፎርሙላ መጠቀም የተወሰነ እፎይታ ቢሰጥም ችግሩን ያባብሰዋል።
እናት በቂ እንቅልፍ ካላገኘች፣ ከታመመች ወይም ከደከማት የተወሰነ ለልጆች ፎርሙላ መስጠት ይቻላል። ይህ ማለት ግን ጡት ማጥባት ይቀራል ማለት አይደለም።
ሊጠቅም የሚችል ቢሆንም የጡት ወተትን አፍራሽ አይደለም።
6. ከታመሙ ማጥባት አይቻልም
ፕሮፌሰር ሱትክሊፍ እንደሚሉት፣ ይሄ የተዛባ አመለካከት ነው።
እናት ማጥባት የማትችለው ኤችአይቪ ወይም ሄፒታይተስ ካለባት ብቻ ነው። እነዚህ ሕመሞች ጡት በማጥባት ይተላለፋሉ።
በአብዛኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ እናት ታማም ጡት ማጥባት መቀጠል ይቻላል። የእናት ሰውነት ፀረ ቫይረስ ተከላካይ የሚያመርት ሲሆን፣ ጨቅላ ሕጻናትንም ይጠብቃል።
ጡት በማጥባት ከእናት ወደ ልጅ ህመም የመተላለፉ ነገር እምብዛም ነው።

7. ከዓመት በላይ ካጠቡ ልጅን ጡት ማስጣል ይከብዳል
ፕሮፌሰር ዌይት እንደሚሉት፣ የዓለም ጤና ድርጅት ምክር ለስድስት ወራት ልጅን ጡት ማጥባት ነው። ከዚያም አብረው የሚሄዱ ምግቦችን ጀምሮ እስከተፈለገው ጊዜ ጡት ማጥባት መቀጠል ይቻላል።
ጡት ማጥባት መቆም አለበት በሚል የተቀመጠ ጊዜ የለም።
እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ባሉ የበለጸጉ አገራት ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ልጆችን ጡት ማስጣል ይቻላል።
አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት እስከ ሦስት ዓመት ድረስ እናት ጡት ማጥባቷን ልተቀጥል ትችላለች።
ዓለም አቀፍ ችግር የሆነው ብዙ አገራት በቂ የወሊድ ፈቃድ አለመስጠታቸው ነው። በዚህም ምክንያት እናቶች የዓለም ጤና ድርጅትን መርኅን ተከትለው ብቻ ያጠባሉ።












