የእናት ጡት ወተት ‘ባንክ’ ለምን ከእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ተቃውሞ ገጠመው?

የፎቶው ባለመብት, THINKSTOCK
በፓኪስታን ሥራ ሊጀምር የነበረ ግዙፍ የእናት ጡት ወተት ‘ባንክ’ በአገሪቱ ባሉ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ተቃውሞ ከገጠመው በኋላ እንዲዘጋ ተደረገ።
የሃይማኖት መሪዎቹ ቀደም ሲል ለእናት ጡት ወተት ባንክ ፕሮጀክት ይሁንታን ሰጥተው የነበረ ቢሆንም፣ ተቋሙ ተገንብቶ ሊመረቅ ቀናት ሲቀሩት እንዲዘጋ ተወስኗል።
እንደ የተባበሩት መንግሥት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) አሃዝ ከሆነ በደቡብ እሲያ ከፍተኛ የሕጻናት ሞት መጠን ያለባት አገር ፓኪስታን ነች።
እናት አዲስ ለተወለደ ልጇ ጡት ማጥባት የማትችልበት ሁኔታ ሲፈጠር የእናት ጡት ወተት ማቅረብ የሚችሉ ተቋማት አዲስ ለተወለደ ሕጻናት የሕይወት እና ሞት ጉዳይ ይሆናሉ።
ለዚህ ደግሞ ማያሳያ የባሺራ ታሪክ ነው።
ባሺራ የመጀመሪያ ልጇን እንደ ወለደችው ነበር በሞት ያጣችው።
ከአንድ ዓመት በፊት ባሺራ ዳግም ከጸነሰች በኋላ በመጀመሪያ እርግዝናዋ ያጋጠማት ክፉ ነገር ዳግም እንዳያጋጥማት ከባለቤቷ ራሂም ጋር ወደ ካራቺ አቀናች።

የፎቶው ባለመብት, Rahim Shah
በሁለተኛ እርግዝናዋ ሴት ልጅ ተገላገለች። ልጇ ግን ካለጊዜዋ በሰባት ወሯ ነበር የተወለደችው። “ዶክተሮች ጡት እንድሰጣት ነገሩኝ። ጡቴ ግን ምንም ወተት የለውም” በማለት የነበራትን ጨንቀት ታስታውሳለች።
ራሂም “በሰባት ወሯ የተወለደችው ልጄ ማሞቂያ ክፍል ነበረች። ፎርሙላ [የዱቄት] ወተት አይሰጣትም ተባለ። የባሺራ ጡት ደግሞ እምቢ አለ። ልጄን ለማዳን ያላደረግኩት ጥረት አልነበረም” ይላል።
ባሺራ ልጇ በረሃብ ስትሞት ማየትን ጨርሶ ማሰብ አትፈልግም። በፓኪስታን የእናት ጡት ወተት የሚያቀርብ ተቋም ባለመኖሩ፤ የልጇን ሕይወት ለመታደርግ በየሆስፒታሉ እየዞረች ልጇን የምታጠባ እናት መፈለግን አማራጭ አደረገች።
“ከአንድ ሆስፒታል ወደ ሌላኛው እየተዘዋወርኩ በመጨረሻ በቅርቡ ወልዳ ልጇ የሞተባት እናት አገኘሁ። ልጄን ጡት እንድታጠባ ጠየቅኋት። እርሷም ፍቃደኛ ሆነች” ትላለች።
ራሂም ይህች እናት ልጃቸውን ለማጥባት ፍቃደኛ ባትሆን ኖሮ ልጇ በሕይወት የመትረፍ ዕድል እንደሌላት ትናገራለች።
የእናት ጡት ወተት ባንክ
በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች ከእናቶች የጡት ወተት ተሰብስቦ የጥራት ደረጃው ተመርምሮ ለጨቅላ ሕጻናት ይሰጣል።
እንደ ማሌዢያ እና ኢራን ያሉ ሙስሊም የሚበዛባቸው አገራት ጨምር የእናት ጡት ወተት ሰብስበው ለጨቅላ ሕጻናት የሚያቀርቡ የእናት ጡት ወተት ባንክ ተቋማት አሉ።
ብዙ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ግን መስል ተግባር እስላማዊ ሕግ ጡት ስለማጥባት ከሚፈቅደው ጋር ይቃረናል ይላሉ።
በእስልምና አንዲት እናት ያልወለደችውን ልጅ ብታጠባ ከልጁ ጋር “የወተት ዝምድና” ይፈጠራል። የአንድ እናት ጡት የጠቡ ልጆች በሙሉ ወንድም እና እህት ተደርገው ይታያሉ።
በዚህም ምክንያት አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች በፓኪስታን የተከፈው የእናት ጡት ወተት ባንክ “ሃራም ነው” ሲሉ አውጀዋል።

የፓኪስታን ባለሥልጣናት የእናት ጡት ወተት ከእስልምና አስተምህሮ ጋር እንዳይቃረን ብዙ መጣራቸውን ይገልጻሉ።
የግዛቲቱ የጤና ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር አዝራ ፔቹሆ ለቢቢሲ ሲናገሩ ለተቋሙ የጡት ወተት የሚለግሱ እናቶች ማንነት ይመዘገብ እና የጡት ወተቱን ለሚጠቡ ልጆች ወላጆች ይገለጻል ይላሉ።
ዶ/ር አዝራ የጡት ወተት የሰጠችውን እናት ማንነት መለየታች የአንድ እናት ጡት የጠቡ ልጆች ወደፊት ትዳር እንዳይመስረቱ ማረጋገጫ ነው ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ለሙስሊም ሕጻን የሚሰጠው የጡት ወተት ሙስሊም ከሆነች እናት የተገኘ ብቻ ስለመሆኑም ዶ/ር አዝራ ለእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ የአገሪቱ የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች የጡት ወተት ባንክ ሃራም ነው በማለት የቀረበውን ሃሳብ አልተቀበሉትም።
የፓኪስታ ሕገ-መንግሥት የትኛውም የአገሪቱ ሕግ የሸሪያ ሕግን መጻረር የለበትም ይላል።

የጡት ወተት
የእናት ጡት ወተት የጨቅላዎችን በሽታ የመከላከል አቅምን ከማሳደጉ በላይ ለልጆች ዕድገት ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ይዟል።
የዓለም ጤና ድርጅት ጨቅላዎች ከውልደት እስከ ሁለት ዓመታቸው “በበቂ ሁኔታ” ጡት ቢጠቡ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ የ820 ሺህ ልጆችን ሕይወት መታደግ ይቻላል ይላል።
የዓለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ ጨቅላዎች የእናታቸውን ጡት መጥባት ካልቻሉ የሌላ እናት ጡት ወተት እንዲጠቡ ምክር ይሰጣሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት የጡት ወተት ለጨቅላዎች የሚያቀርቡ ተቋማት በ60 አገራት ቢኖሩም፣ ተቋማቱ ከእስልምና የሃይማኖት አስተማሪዎች ጠንካራ ተቃውሞ ይገጥማቸዋል ይላል።
ከዚህ በተጨማሪም ጥናቶች በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ሙስሊም ወላጆች ለልጆቻቸው የሌላ ሰው የጡት ወተት ለመስጠት እንደሚያመነቱ ያሳያሉ።
ካራቺ የምትገኘው የባሺራ ልጅ ግን ጤና እና ደስተኛ ልጅ ሆና እያደገች ነው።
“ልጄን ያጠባችውን እናት በጣም አመሰግናታለሁ። ወደፊት ዕድሉን ካገኘሁ እና ከቻልኩ ለእኔ የተደረገውን በማድረግ የሕጻን ልጅን ሕይወት መታደግ እፈልጋለሁ” ስትል ባሺራ ለቢቢሲ ተናግራለች።












