መድኃኒት የሚቋቋም የወባ በሽታ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ መስፋፋቱ ከፍተኛ ስጋት ፈጠረ

የወባ ትንኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአፍሪካ ዋነኛ የተበላውን መድኃኒት የሚቋቋም የወባ በሽታ በመስፋፋቱ በሕብረተሰብ ጤና ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጠረ።

ተመራማሪዎች መድኃኒትን የተላመደ የወባ በሽታ ሥርጭትን ለማስቆም አስቸኳይ እና ሥር ነቀል እርምጃ ካልተወሰደ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአደጋ ተጋልጠዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የወሳኙን የአርተማይዚኒን መድኃኒት ተፅዕኖ መቋቋም የሚችሉ የወባ በሽታ ተውሳኮች በምሥራቅ አፍሪካ ተስፋፍተዋል ተብሏል።

በአንዳንድ አካባቢዎች መድኃኒቱን የመላመድ ምጣኔው በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከአንድ በመቶ በታች ወደ 20 በመቶ በላይ ከፍ ብሏል።

በአፍሪካ ለመጨረሻ ጊዜ በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ የፀረ ወባ በሽታን መድኃኒትን የሚቋቋም ወባ በመከሰቱ ምክንያት በበሽታው የሚሞቱት ሕፃናት ቁጥር በሦስት እጥፍ እንዲጨምር አድርጎ ነበር።

በዚህም ምክንኣት ከ10 አገራት የተውጣጡ 28 ታዋቂ የወባ ሳይንቲስቶች በሳይንስ ጆርናል ላይ በፍጥነት እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።

አርተማይዚኒን የወባ በሽታን የሚያስከትል ተወሳክ የሚገድል ሲሆን፣ ይህም በበሽታው ሕክምና ውስጥ ወሳን ተደርጎ ይወሰዳል።

አርተማይሲኒንን የሚቋቋም ወባ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ በሩዋንዳ፣ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ በኡጋንዳ እና በኤርትራ መፈጠሩ ተነግሯል።

እነዚህ መድኃኒቱን የተላመዱ የወባ ተውሳኮች በአገራቱ እና ድንበር ዘለው በሌሎች አገራት ውስጥ ተሰራጭተዋል።

ወባ ይገድላል የሚል ጽሑፍ የያዘች ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሁን በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በሩዋንዳ፣ በኡጋንዳ እና በታንዛኒያ ውስጥ ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነው የወባ በሽታ የሚከሰተው መድኃኒቱን በተቋቋሙ ፓራሳይቶች ነው።

“በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ውጤታማ ባልሆኑ የፀረ ወባ ሕክምናዎች ከመሞታቸው በፊት እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ በናይጄሪያ የሚገኘው የኢሎሪን ዩኒቨርሲቲ የሕፃናት ሕክምና ክፍል ፕሮፌሰር የሆኑት ኦሉግቤንጋ ሞኩኦሉ ተናግረዋል።

እአአ በ2016 በሰሜን ኡጋንዳ መድኃኒቱን የሚቋቋም ወባ እምብዛም አልተገኘም ነበር። እአአ በ2019 ግን ከ20 በመቶ በላይ ደርሷል።

መድኃኒት የተላመደውን ዝርያ ይበልጥ ከተስፋፋ “ማስወገድ የማይቻል” ይሆናል ሲሉ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድኑ ተናግረዋል።

በታይላንድ የማሂዶል ኦክስፎርድ ትሮፒካል ሕክምና ምርምር ማዕከል ባልደረባ የሆኑት የሆኑት ዶ/ር መሁል ዶርዳ ይህ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚከሰት ለጊዜው እርግጠኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

ነገር ግን በደቡብ ምሥራቅ እስያም ተመሳሳይ የሆነ ነገር ታይቶ በአርተማይሲኒንን ላይ የተመሠረቱ ህክምናዎች ውጤታማ መሆን አቁመዋል።

ከታሪክ መማር

ተመሳሳይ ታሪክ ከዚህ በፊት ተከስቷል። በ1970ዎቹ በሽታው በምሥራቅ አፍሪካ ቀድሞ ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን ክሎሮኪን የተሰኘ መድኃኒት መቋቋም ጀመረ። በ1980ዎቹ ደግሞ ወደ ምዕራባዊ አፍሪካ ተስፋፋ።

በአህጉሪቱ በወባ ምክንያት የሚከሰት ሞት በሦስት እጥፍ ጨምሮ በ1980 ከነበረበት 493 ሺህ ገደማ በ2004 ወደ 1.6 ሚሊዮን አደገ።

“ይህ በድጋሚ አፍሪካ ውስጥ የምናየው ነገር እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ” የሚሉት ዶክተር ዶርዳ፣ “የአርተማይሲኒን ሕክምና አልሳካ ማለት ከጀመረ የሞት ቁጥር ይጨምራል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሊቃውንቱ በሽታውን የሚያሰራጩትን ተወሳኮች እና ትንኞቹ ላይ ያነጣጠሩ ምክረ ሃሳቦችን ሰጥተዋል።

ፓራሳይቱ ሕክምናውን የመቋቋም ችሎታ እንዳይኖረው ለማድረግ ሦስተኛውን መድኃኒት በአርተማይሲኒን ጥምር ሕክምና ላይ መጨመርን አንስተዋል።

ዶክተር ዶርዳ ይህ ገንዘብ ያስወጣል “ካልሆነ ግን እሳቱ ከመስፋፋቱ በፊት ከማጥፋት ይልቅ ለመቆጣጠር ብዙ ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ እናደርጋለን” ብለዋል።

ሌሎቹ ምክረ ሃሳቦች

  • ሰዎች በፀረ-ነፍሳት-የታከሙ የአልጋ አጎበሮችን እንዲጠቀሙ ማድረግ እና ለረጅም ጊዜ የሚሠሩ ፀረ-ተባይ መድኃኒቶችን የመርጨት ሽፋንን ማሳደግ
  • አርተማይሲኒንን የሚቋቋም ወባ ባለባቸው አካባቢዎች አዳዲስ የወባ ክትባቶችን ለሁሉም ማዳረስ
  • የማኅበረሰብ ጤና ሠራተኞችን በመደገፍ ሕክምናው በሁሉም ሰው ቤት ደጃፍ እንዲገኝ ማድረግ
  • ሥርጭቱን ለማወቅ እንዲረዳ የመረጃ ፍሰትን ማሳለጥ፤ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ መዘግየቶች ሊኖሩ ይችላሉ

“እርዳታ በአፍሪካ የአርተማይሲኒንን የሚቋቋም ወባ ሥርጭትን ለመግታት እና ለማጥፋት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን” ሲሉ በታንዛኒያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባልደረባ የሆኑት ዳይሬክተር ንቱሊ ካፖሎግዌ ተናግረዋል።