በወጣት አሜሪካውያን ዘንድ ራስን ማጥፋት ለምን ጨመረ?

በ21 ዓመቱ ራሱን ያጠፋው ቤን

የፎቶው ባለመብት, BBC

የምስሉ መግለጫ, በ21 ዓመቱ ራሱን ያጠፋው ቤን

ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጹሑፍ አንባብያንን የሚረብሹ ይዘቶች አሉት

ካትሪን እና ቶኒ ሳላስ ልጃቸው ቤን ከእነሱ የተደበቀ ሕይወት እንደሚመራ ሃሳቡም አልነበራቸውም።

ከእነሱ በተደበቀው ሕይወቱ ልጃቸው “ራሱን ለማጥፋት እያቀደ ነበር” ይላሉ አባቱ ቶኒ።

ወላጆቹም ሆነ ሌሎች በሚያውቁት መንገድ ደግሞ ቤን ለእጮው የጋብቻ ቀለበትን እየገዛ ነበር።

ሆኖም ወላጆቹ ባልጠረጠሩት ሁኔታ ቤን ራሱን አጠፋ።

“እንድረዳው ዕድሉን ቢሰጠን ምኞቴ ነበር” ይላሉ እናቱ ካትሪን በሐዘን በተሰበረ ድምጽ።

“በጣም አስቸጋሪው ይህ ነበር። እሱን ለማነጋገር መንገድ አልነበረኝም” ብለዋል።

ገና ሃያ አንድ ዓመቱ የነበረው ቤን ሳላስ ሕይወቱን ያጠፋው ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ነበር።

ቤን ተስፋ ያለው ልጅ ነበር። በሰሜን ካሮላይና ስቴት ዩኒቨርስቲም የወንጀል ጥናት ተማሪ እንዲሁም አትሌት ነበር።

በርካታ ጓደኞች ነበሩት። የተረጋጋ ግንኙነት እንዲሁም አፍቃሪ ቤተሰብ ነበሩት።

ቤን ባለፈው ዓመት አሜሪካ በራስ ማጥፋት ካጣቻቸው 50 ሺህ አሜሪካውያን አንዱ ነው።

ይህ አሃዝ በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ ራስ ማጥፋት ተብሎ የተመዘገበ ሲሆን፣ ከዚያ ቀደም ብሎ ባለው በአውሮፓውያኑ 2022፣ 49 ሺህ 449 አሜሪካውያን ራሳቸውን አጥፍተዋል።

በሐዘን የተሰበሩት የቤን ወላጆችም በሳሎናቸው ለልጃቸው መታሰቢያ የሚሆን “የማስታወሻ ግድግዳም” አዘጋጅተዋል።

ከሞተ በኋላ የተሰጠው የዩኒቨርሰቲው ዲፕሎማም ከዚህ ግድግዳ ላይ ተሰቅሏል።

“ቤን ሁለገብ ልጅ ነበር” የሚሉት አባት ልጃቸውን ማጣታቸው “በሕይወታቸው ውስጥ አንድ ትልቅ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። የሆነ ነገር ጎድሎናል” ይላሉ።

ቤን ግን ለምን ራሱን አጠፋ? ቤተሰቦቹ እስካሁን ድረስ ምላሽ ያላገኙለት እና ለመመለስም እየጣሩበት ያለ ጥያቄ ነው።

ራሱን ያጠፋው ቤን ወላጆች
የምስሉ መግለጫ, ራሱን ያጠፋው ቤን ወላጆች
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ልጃቸው በአውሮፓውያኑ 2020 እምብዛም ለክፉ የማይሰጥ የመንፈስ ጭንቀት አጋጥሞት ለአጭር ጊዜ ህክምና ቢያገኝም፣ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ አገግሜያለሁ እንዳላቸው ወላጆቹ ያወሳሉ።

“ከአዕምሮ ጤና ጋር እየታገለ ያለ ሰው ላይ የሚጠበቁ የተለመዱ ጠቋሚ ነገሮች እየታዩበት አልነበረም። ራሱንም አላገለለም” ብለዋል አባቱ።

ቤን ከወላጆቹ ጋር በጣም የቀረበ ግንኙነት አለው። ብዙ ጊዜ ይገናኛሉ፤ ያወራሉም። ቤን ከመሞቱም ከጥቂት ሰዓታት በፊት አባትቱ ደውለውለት የነበረ ሲሆን፣ የመጨረሻ ንግግራቸው መሆኑን አላወቁም ነበር።

“ሳናግረው ደህና ነኝ። ሰላም ነኝ አለ። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይህችን ዓለም ትቷት ሄደ” ይላሉ።

ቤን ይማርበት የነበረው የሰሜን ካሮላይና ስቴት ዩኒቨርስቲ በቅርብ ጊዜ ራሳቸውን የሚያጠፉ ተማሪዎች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ እየተሸበረ ይገኛል።

ባለፈው የትምህርት ዘመን ቤንን ጨምሮ ሰባት ተማሪዎች ሕይወታቸውን አጥፍተዋል።

በዚህ ዓመት ደግሞ እስካሁን ባለው ጊዜ ሦስት ተማሪዎች ራሳቸውን አጥፍተዋል።

በዩኒቨርሰቲው ተማሪዎች ራሳቸውን ማጥፋታቸው ለተማሪዎቹም ሆነ ለዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ፈታኝ እንደሆነ የዩኒቨርስቲው ረዳት ምክትል ቻንስለር ጀስቲን ሆሊንግስሄድ ይናገራሉ።

በአሜሪካ ራስን ማጥፋት በኮሌጅ ካምፓሶች ብቻ የተገደበ ሳይሆን “ብሔራዊ ችግር” መሆኑንም ያስረዳሉ።

“ችግሩን ብናውቅ ኖሮ ለመፍታትም እንሞክራለን። ችግሩን ላለማየት ወይም ችላ እያልን አይደለም። ነገር ግን ምንም ዓይነት የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ላይኖሩ ይችላሉ።

“በችግር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ለቤተሰቦቻቸው ወይም ለጓደኞቻቸው አይናገሩም። እርዳታም ለማግኘት ሳይሹ እና ምንም ፍንጭ ሳናይ እዚህ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ። ለምን እንደሆነም በጭራሽ ልናውቅ አንችልም” ይላሉ ቻንስለር ጀስቲን።

ራሳቸውን የሚያጠፉ ተማሪዎች ቁጥር ከፍ ያለበት የሰሜን ካሮላይና ስቴት ዩኒቨርስቲም የአማካሪ ባለሙያዎች ቁጥርን ጨምሯል፤ እንዲሁም ተማሪዎች ድጋፍ የሚያገኙበትን ተንቃሳቃሽ ማዕከላትንም አቋቁሟል።

እንዲሁም ከአዕምሮ ጤና ጋር እየታገሉ ያሉ ተማሪዎች ሊያሳይዋቸው የሚችሉ ምልክቶችን ተረድተው ጓደኞቻቸው እያለፉበት ያለውን ነገር ሊያሳውቁበት የሚችሉበት ሥርዓትም ዘርግቷል።

በተጨማሪ ደግሞ በመማሪያ ክፍሎቻቸው በተደጋጋሚ የማይገኙ ተማሪዎችን እንዲሁም የቤት ሥራዎቻቸውን በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ማጠናቀቅ የማይችሉ እና እንዲራዘምላቸው የሚጠይቁ ተማሪዎችንም በተመለከተ መምህራን ሥልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው።

ምናልባትም እነዚህ ተማሪዎች እየገጠሟቸው ያሉ ችግሮች ምልክቶች ከሆኑ በሚል ነው ዩኒቨርስቲው መምህራኖቹ እንዲሠለጥኑ እያደረገ ያለው።

“በማናውቃቸው ሁኔታዎች ውስጥ የምንችለውን ያህል እየሠራን እንዳለን ይሰማኛል” ይላሉ ጀስቲን።

በተቻለ መጠን ድጋፍ በመስጠትም አንድን ሕይወትን እንኳን መታደግ ከተቻለ በሚል ዩኒቨርስቲው እየሠራ ይገኛል።

የሰሜን ካሮሊና ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ራሌይ ነው ዩኒቨርስቲው የሚገኘው።

ታሊ በመባል የሚታወቀው የተማሪዎች ኅብረት በርካታ ካፌዎችን፣ የማጥኚያ ስፍራዎች እና ሱቆችን የያዘ ባለ ብዙ ፎቅ ህንጻ ነው።

“የመጀመሪያው ራስ ማጥፋት ሲከሰት ዶርም ውስጥ ነበርኩ” ትላለች በዩኒቨርስቲው ተማሪ የሆነችው ሎሬላይ።

“በእኛ ዕድሜ ያሉ ብዙ ልጆች ስለ ዓለም ጭንቀት አለባቸው ብዬ አስባለሁ። በርካታ ነገሮች እየተሻሻሉ አይደለም። የኑሮ ውድነቱም እየከፋ ነው” ትላለች።

የሰሜን ካሮላይና ስቴት ዩኒቨርስቲ
የምስሉ መግለጫ, በርካታ ተማሪዎቹ ራሳቸውን ያጠፉበት የሰሜን ካሮላይና ስቴት ዩኒቨርስቲ

የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ የሆነው ብሮዲ ዩኒቨርስቲው በተደጋጋሚ በሚልካቸው ኢሜይሎች ምክንያት እየተሰጠ ያለውን እርዳታ እና እገዛ እንደሚያውቅ ያስረዳል።

ዩኒቨርስቲው “በአዕምሮ ጤና ችግሮች ላይ የበለጠ ትኩረት እየሰጠ ነው” ይላል።

በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ተመሳሳይ ችግር እያጋጠማቸው ይገኛሉ። ራስን ማጥፋት አንደኛው አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ራስን ማጥፋት ከ35 ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች መካከል ሁለተኛው የሞት መንስዔ እንደሆነ የአሜሪካ የጤና ተቋም የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል አስታውቋል።

የበርካቶችን ሕይወት ያናጋው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የበኩሉን አስተዋጽጾ ሊያደርግ እንደሚችልም የሥነ አዕምሮ ሐኪም እና የብሔራዊ የአዕምሮ ጤና ተባባሪ የህክምና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ክርስቲን ክራውፎርድ ያስረዳሉ።

“ወጣቶቻችን የሚያስፈልጋቸውን ማኅበራዊ ክህሎቶችን እና መንገዶችን ከማግኘት አንጻር ወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል” ይላሉ።

“በቤት ውስጥ ተወስነው ነበር። ከዕድሜ እኩዮቻቸው እና ለወጣቶች ጤናማ እድገት በጣም ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮችም ጋር ተለያይተዋል።”

አብዛኛውን ጊዜ በተንቃሳቃሽ ስልካቸው እና ላፕቶፓቸው ላይ ረዥም ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ወጣቶች ለጦርነት፣ ለጽንፈኛ መልዕክቶች የሚጋለጡ ሲሆን፣ ይህም ለጭንቀት እና ለድብርት እንደሚያጋልጣቸው ዶክተሯ ያስረዳሉ።

በአውሮፓውያኑ 2021 የአሜሪካ ከፍተኛው የጤና ባለሥልጣን ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በማስመልክት ብሔራዊ የጤና ምክር ማሳሰቢያ አስተላልፈዋል።

በዚህ ማሳሰቢያቸው ላይ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እና ወረርሽኙ “ወጣቶች እያጋጠሟቸው ያለውን ጭንቀት በማባበስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ” ተናግረዋል።

በመላው አሜሪካ ከ200 በላይ ማዕከላት ያሉት ብሔራዊ ራስን የማጥፋት የእርዳታ የስልክ መስመር፣ 988 ላይ የሚደረጉ ጥሪዎች ባለፈው ዓመት በአንድ ወር ብቻ በ100 ሺህ ጭማሪ አሳይተዋል።

በሜሪላንድ ግዛት ውስጥ የሚገኝ አንድ የእርዳታ ጥሪ ማዕከል ያሉትን 150 ኦፕሬተሮችን ቁጥር ለመጨመር በዕቅድ ላይ ነው።

ወደ ማዕከሉ የሚመጡ አብዛኞቹ ጥሪዎች ከ15 ዓመት ጀምሮ እስከ 35 እና 40 የሚደርሱ ወጣት ወንዶች እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደሆኑ የማዕከሉ ሠራተኛ ጆሴ ሜለንዴዝ ያስረዳሉ።

“ከዩኒቨርስቲ ትምህርታቸው ክፍያ ጋር በተያያዘ ጭንቀት እንዲሁም የምጣኔ ሃብቱ ሁኔታ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይከታቸዋል” ይላሉ።

“ያለፈው ትውልድ የነበረው እያንዳንዱ የማኅበራዊ ዋስትና ትስስር ብጥስጥሱ ወጥቷል። በርካታ ወጣቶች የወደፊት ሕይወታቸው ላይ ምን እንደሚጠብቃቸው በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስጨንቃቸው ይመስለኛል” በማለት እኚሁ ሠራተኛ ይናገራሉ።

ራሳቸውን ላጠፋው ልጃቸው መታሰቢያ የሆነው የማስታወሻ ግድግዳ
የምስሉ መግለጫ, ራሳቸውን ላጠፋው ልጃቸው መታሰቢያ የሆነው የማስታወሻ ግድግዳ

ልጃቸውን ባሳዛኝ ሁኔታ ያጡት ካትሪን ሐዘኑ የማይወጣላቸው ሆኗል።

ከቲሸርታቸው ላይ የልጃቸውን ምስል ያለበት “ጉዳያችን ነህ” የሚልም ጽሁፍ የያዘ ባጅ አድርገዋል።

“በየቀኑ ይህንን ቲሸርት እለብሰዋለሁ። ባጁን ልቤ ላይ አደርገዋለሁ። ምክንያቱም ቤን እዚያ ነው ያለው” ይላሉ እናት እንባቸውን እየታገሉ።

ወላጆቹ ቤን መቆጣጠር ያልቻለው እና ሕይወቱን ያሳጣውን የአእምሮ ጤና ችግር የሆነው ድብርት ላይ ግንዛቤን ለማሳደግም እየሠሩ ይገኛሉ።

የአዕምሮ ህመም በአሜሪካ ውስጥ መገለል እንደሚያመጣም ሁለቱ ወላጆች ያስረዳሉ።

“በርካታ ሰዎች ስለ ጉዳዩ እንዲናገሩ እንፈልጋለን። በእኛ ላይ ከደረሰ በሌላውም ላይ የማይደርስበት ምክንያት የለም” ይላሉ አባት ቶኒ።

እናት ካትሪንም በዚህ ይስማማሉ “ደህና ነኝ የሚሉትን ነገር ዝም ብላችሁ አትውሰዱት። ደህና ነኝ ካሉ አብዛኛውን ጊዜ በደኅንነት ላይ ላይሆኑ ይችላሉ” ይላሉ።