ቋንቋቸውን የሚናገር ባለመኖሩ ለ12 ዓመታት በአሜሪካ ሆስፒታል ለመቆየት የተገደዱት ሜክሲኳዊት

ሪታ ፓቲኖ

የፎቶው ባለመብት, PIANO PRODUCTIONS

የምስሉ መግለጫ, ሪታ ፓቲኖ

እአአ ሰኔ 8/1983 የካንሳስ ፖሊስ በዕድሜ የገፉ ሴት በቤተክርስቲያን ውስጥ ያገኛል። ግራ ከመጋባታቸው በተጨማሪ የቆሸሸ ልብስ ለብሰዋል።

ሴትየዋ ማንም የማያውቃቸውን ጥቂት ቃላት ተናገሩ። ፖሊስ በእንግሊዝኛ ይጠይቃል እሳቸው በማይታወቅ ቋንቋ ይመልሳሉ። የሚናገሩትን ማንም ባለመረዳቱ ለ12 ዓመታት ነጻነታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ተገደዋል።

ሪታ ፓቲኖ ኩዊንቴሮ ይባላሉ። የሜክሲኮው ራራሙሪ (ታራሁማራ) ማኅበረሰብ ተወላጅ ናቸው።

በተያዙበት ቀን በምዕራብ ካንሳስ ማንተር ከተማ በሚገኘው የሜቶዲስት ቤተክርስቲያን ምድር ቤት ውስጥ ተጠልለው ነበር።

ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ። በኋላም ሊያጥባቸው የሞከረውን የፖሊስ መኮንን ደብደቡ ሲል የሜክሲኮ ፊልም አዘጋጅ ሳንቲያጎ ስታይንዩ ተናግሯል።

ሳንቲያጎ በ2024 ለዕይታ የበቃውን “የከዋክብት እና የተራራዋ ሴት” የተሰኘውን በሪታ ዙሪያ የሚያጠነጥን ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅቷል።

“በተፈጥሮ ውስጥ መኖር”

ዳይሬክተሩ ቀረጻ የጀመረው በ2016 ቢሆንም ፕሮጀክቱ ተጠናቀቀው በ2022 ነው።

“አልታመምኩም። ከተፈጥሮ ጋር በመኖሬ በጣም ጥሩ ስሜት ይሰማኛል” ሲሉ ሪታ ዘጋቢ ፊልሙ ላይ ይደመጣሉ።

ይህንን የተናገሩት ሰሜናዊ ሜክሲኮ የራራሙሪ ተወላጆች በሚኖሩባት የትውልድ ግዛታቸው ቺዋዋ ሲሆን፣ የሚናገሩት ደግሞ በአፍ መፍቻ ራራሙሪ ቋንቋ ነው።

ራራሙሪ ማለት “የብርሃን ሯጮች” እንደማለት ነው። “ራራ” እግር ማለት ሲሆን “ሙሪ” ደግሞ ብርሃን እንደማለት ነው።

ለራራሙሪዎች ሩጫ ጠቃሚ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ጠቀሜታ አለው። በሴራ ታራሁማራ ተዳፋት አካባቢ ይኖራሉ። በውስብስብ መልክዓ ምድራቸው ምክንያት ጅረቶችን እንዲያቋርጡ እና ተራራዎችን እንዲወጡ ያስገድዳቸዋል።

ሪታ በካንሳስ ውስጥ የገጠማቸው ግን ከትውልድ አገራቸው በተቃራኒ የሆነ የአየር ንብረት ነው።

ይህም ለ12 ዓመታት በአሜሪካ የአእምሮ ህክምና ማዕከል እንዲታሰሩ አድርጓቸዋል።

በቋንቋ አለመግባባት

ሪታ ራራሙሪ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገራሉ።

በካንሳስ ፍርድ ቤት እና በሆስፒታል ውስጥ ግን አስተርጓሚ አላገኙም። ሪታ ምን እየሆነ እንደሆነ እና ለምን እንደታሰሩም አያውቁም።

ባለሙያ ነው የተባለ ተርጓሚም እንኳን ቋንቋቸውን አልተረዳም።

“ፍርድ ቤት ሲወሰዱ ዳኛው አእምሯቸው ትክክል እንዳልሆነ እና ለራሳቸው ጭምር አደገኛ እንደሆኑ በመግለጽ ወደ አእምሮ ህክምና ሆስፒታል ይወሰዱ” ብለዋል ሲል ሳንቲያጎ ለቢቢሲ ሙንዶ ገልጿል።

ቀሪው ሕይወታቸው በገለልተኝነት፣ በህክምና፣ በተቋማዊ ቢሮክራሲ እና በብቸኝነት የተሞላ ነበር።

ሪታ ፓቲኖ ከማኅበራሰባቸው አባላት ጋር

የፎቶው ባለመብት, PIANO PRODUCTIONS

የምስሉ መግለጫ, ሪታ ፓቲኖ ከማኅበራሰባቸው አባላት ጋር

ለመሆኑ ሪታ ማን ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሪታ በአፈ ታሪክ እና በምሥጢራዊ ጉዳዮች የተከበቡ ሴት ናቸው።

የበግ እረኛ፣ አዋላጅ፣ የእጸዋት ባለሙያ፣ የእጅ ባለሙያ እና ልብስ አጣቢ ነበሩ።

እንደሳንቲያጎ ዘጋቢ ፊልም ከሆነ ሪታ ብዙ ነገሮችን መሥራታቸውን የተለያዩ ዘመዶቻቸውን እና ጎረቤቶቻቸውን ቃለ መጠይቅ አድርጎ ገልጿል።

ሪታ በ1930 እንደተወለዱ ይታመናል። የትውልድ ቀያቸው በቺዋዋ የምትገኘው ፒድራስ ቨርዴስ ናት። በኋላም በኡሪክ ማዘጋጃ ቤት ስር ባለችው በሴሮካሁይ አቅራቢያ ይኖሩ ነበር።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ከሆነ ባል እና ወንድ ልጅ ነበራቸው።

ብዙ በግ ስለነበራቸውም በማኅበረሰባቸው ደረጃ “ሃብታም” የሚባሉ ናቸው።

አንድ ቀን ግን ሁሉም ነገር ተለወጠ። ሪታ “የሚፈሩ እና የማይፈለጉ” ሆኑ።

በጎቻቸው ተዘረፉ። ጎረቤቶቻቸው ደግሞ ባላቸውን ገድለዋል ብለው ያሟቸው ጀመር። ይህ ስለመሆኑ ግን እስካሁን ድረስ ማረጋገጫ አልተገኘም።

የሪታ ጎረቤት የነበረው እና በዘጋቢ ፊልሙ ላይ የተሳተፈው ፕሮሶፒዮ ማንሲናስ “የታየችበት መንገድ አስከፊ ነው። ከባለቤቷ ጋር ተጣልታ፤ ደበድባ እንደገደለችው ተነግሯል።”

“ሪታ ባሏ ፓቲኖ ጄሮኒሞ ሬንቴሪያስን አልገደለችውም። ሪታ ፓቲኖ ፍየሎቿን ተዘርፋለች። ብርድ ልብሶቿ እና በጎቿ ተሰርቀዋል” ሲል አክሏል።

እንደሳንቲያጎ ጥናት ከሆነ ባላቸው ቺዋዋ ውስጥ ስለመሞታቸው ምንም ዓይነት የተመዘገበ መረጃ አልተገኘም።

እሳቸው አንድ ዓይነት “አስማታዊ ኃይል” እንዳላቸውም እምነት ነበረው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሪታ የተወሰነ የአካል ጉዳት ነበራቸው ይላል ሳንቲያጎ።

ሪታ የመናገር ችግር የነበረባቸው ሲሆን፣ ከልጃቸው ጋርም መንከራተት ጀመሩ። ማኅበረሰቡ ደግሞ በፍርሃት ይመለከታቸው ጀመር። የትም ጥሩ አቀባበል እንዳልተደረገላት ጎረቤቶቻቸው ይናገራሉ።

“አንዳንድ ሰዎች አልፈለጓቸውም፤ በራቸውንም ዘጉባቸው። ሊገድሏቸው እንደሚፈልጉም ይገልጻሉ። እሳቸው ግን ተርበው ምግብ ፍለጋ ነበር ከቤት ቤት የሚንከራተቱት” ሲል ማንሲናስ አክሎ ተናግሯል።

“ባጋጠማቸው እና ስለእሳቸው በተነገረው ነገር ምክንያት ባለሥልጣናት ልጃቸውን ነጠቋቸው” ይላል የፊልም ሠሪው።

ለምን ሜክሲኮን ለቀው እንደወጡ እና ወደ ካንሳስ እንዴት እንደደረሱ አሁንም እንቆቅልሽ እንደሆነ መቅረቱን ሳንቲያጎ ጠቁሟል።

የእግር ጉዞ

የፎቶው ባለመብት, PIANO PRODUCTIONS

ነፃነት

ፍርድ ቤቱ መጀመሪያ ላይ ሴትየዋ የአእምሮ ህክምና ሆስፒታል ለሦስት ወራት እንዲቆዩ ይወስናል።

ከሦስት ወራት በኋላ ጤንነታቸው በድጋሚ ይገመገማል በሚል ሃሳብ ነው።

በፍርድ ቤት የቆመላቸው ጠበቃ ግን ፍርድ ቤት አልቆመላቸውም።

በአስተርጓሚ አለመኖር ምክንያት ከእርሳቸው ጋር መግባባትም አልቻለም።

የህክምና ባለሙያዎችም ስለእሳቸው ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው በመግለጽ የትኛውንም የቤተሰብ አባላቸውን ማግኘት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ገልጸዋል።

ወራት አለፈው፣ ዓመታት ነጎዱ።

ሪታ መናገር አልቻሉም። ብቻቸውን ከቤታቸው ርቀው ነበር።

በቋንቋ ችግር ምክንያት ተጨባጭ ምርመራ ሳይደረግላቸው መድኃኒት እየወሰዱ ቆዩ።

“ብዙ ዓይነት አድሎአዊነት እና ጫናዎችን አይቻለሁ። በሪታ ጉዳይ ብዙ አካላት ነበሩበት። እሳቸው እንግሊዝኛ የማይናገሩ፣ ድሃ እና ስደተኛ የሆኑ፣ ምናልባትም የአካል ጉዳተኛ ናቸው” ይላል ሳንቲያጎ።

ሁኔታው ​​እስኪሻሻል አሥር ዓመታት ፈጅቷል።

የካንሳስ የአካል ጉዳተኞች መብት ተቋም በ1994 በሆስፒታል ውስጥ ከአምስት ዓመታት በላይ የቆዩ ታካሚዎችን ጉዳይ ለመገምገም ወሰነ።

ድርጅቱ ቶሪያ ምሮዝን የተባለ ጠበቃ ለሪታ አቆመላቸው።

“ካከናወናቸው የመጀመሪያዎቹ ነገሮች መካከል አንደኛው የህክምና መዝገቦቻቸውን መመልከት ነበር። ከቺዋዋ የመጡ እና የታራሁማራ ተወላጅ መሆናቸውን የሚያመለክት መረጃ ነበር” ሲል ምሮዝ ተናግረዋል።

“አሥር ዓመታት አልፈውም እዚያው ነበሩ። ሁሌም ‘ከየት እንደመጡ ወይም የሚናገሩትን ቋንቋ አናውቅም’ ይሉ ነበር” ሲሉ አክለዋል።

የአካል ጉዳተኞች ድርጅቱ ሆስፒታሉን እና ከ30 በላይ ሠራተኞቹን ከሰሰ። ለደረሰው ጉዳት 10 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ጠየቁ።

ሪታ ፍርድ ቤት ቀርበው መመስከር ስለማይችሉ የሕግ ሂደቱ የራሱ ተግዳሮቶች ነበሩት።

በዚያን ውቅት ራራሙሪን (ታራሁማራን) የመረዳት ችሎታ ያለው አንድ የሥነ-አእምሮ ሐኪም ብቻ ነበር ይላል ሳንቲያጎ።

ሪታ ከሆስፒታል ወጥተው በ1995 ሜክሲኮ ደረሱ። የፍርድ ቤቱ ጉዳይ ግን እስከ 2001 ድረስ ቀጠለ። በመጨረሻም በድርድር ተፈታ።

ሪታ 90 ሺህ ዶላር ካሳ ተከፈላቸው። ከዚህ ውስጥ 32 ሺህ 641 ዶላር ደግሞ ለረዳቸው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ተሰጠ።

የተቀረው ገንዘብ ሪታን በአገራቸው ለመርዳት የሚውል ሆነ።

ሪታ ፓቲኖ

የፎቶው ባለመብት, PIANO PRODUCTIONS

የምስሉ መግለጫ, ሪታ ፓቲኖ

ድሃ ግን “ደስተኛ”

ሪታ በድህነት ውስጥ መኖራቸውን ቀጥለዋል።

“ፍርድ ቤቱ አመኔታ ለመፍጠር እና በመንግሥታዊ ባልሆነው ድርጅት የተመረጠችውን ቤያትሪዝ ዛፓታ የሚባሉ መነኩሴ የሪታ ንብረት እንዲያስተዳድሩ ተሾሙ። ለሁለት ዓመታት ያህል በወር 300 ዶላር ያህል ይሰጣቸው ጀመር። ከዚያም በአንድ ጊዜ ስድስት ሺህ ተሰጣቸው። በኋላም መነኩሴዋ ቀሪውን ገንዘብ ይዘው ጠፋች” ይላል ፊልም ሠሪው ሳንቲኣጎ።

ለበርካታ ዓመታትም መነኩሴዋ ገንዘቡን ለራሳቸው ተጠቀሙበት። በኋላም ፍርድ ቤቱ ከመነኩሴዋ እጅ 10 ሺህ ዶላር ብቻ ማስመለስ ቻለ።

ሌሎች ሁለት አዳዲስ ሞግዚቶች ተቀጠሩላቸው። ሞግዚቶቹ በየዓመቱ አንድ ሺህ ዶላር ይከፈላቸው ነበር። ሁለቱም ግን ሪታን ልናገኛት አልቻልንም ብለው ነበር።

ከአሥር ዓመታት በኋላ ገንዘቡ አለቀ።

ከላቲን አሜሪካ በቋንቋ እጦት የተነሳ በህክምና ቸልተኝነት ከተጎዱ እና በይፋ የሚታወቁት ሪታ ብቻ ነበሩ። ከሰሜን አሜሪካ የመጡ ሌሎች በርካታ ሴቶች ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸዋል።

ሪታ ፓቲኖ እአአ በ2018 ሕይወታቸው አለፈ። ቤተሰቦቻቸው እና ማኅበረሰቡ ህልፈታቸውን ደግሰው “አከበሩ።”

የራራሙሪ ሰዎች ሙታንን ደግሶ መሸኘት ወደ ቀጣዩ ሕይወት እንዲሸጋገሩ እንደሚረዳቸው ያምናሉ።

ሪታ ሜክሲኮ በነበሩበት ጊዜ መዝፈን እና መጨፈር ይወዱ ነበር።

“እዚህ [በትውልድ አገሬ] በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲሉ ሪታ በአንድ ወቅት ለሳንቲያጎ ነግረውት ነበር።