የብራዚል ሻርኮች ሰውነት ውስጥ ኮኬይን የተባለው አደገኛ ዕፅ እንዴት ሊገኝ ቻለ?

አንድ ሻርክ ቤተ-ሙከራ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Oswaldo Cruz Foundation

የምስሉ መግለጫ, ሳይንቲስቶቹ ቤተ-ሙከራ ውስጥ ሻርኮች ላይ ምርመራ አድርገው ዕፅ አግኝተውባቸዋል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ሳይንቲስቶች በብራዚል ጠረፍ አካባቢ የሚገኙ ሻርኮች እንዴት ኮኬይን የተሰኘው ዕፅ ሊገኝባቸው እንደቻለ ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የኦስዋልዶ ክሩዝ ፋውንዴሽን የባሕር ምርምር ባለሙያዎች 13 ሻርኮችን መርምረው ጡንቻቸው እና ጉበታቸው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው አደገኛ ዕፅ አግኝተዋል።

ብራዚሊያን ሻርፕኖዝ ተብለው የሚጠሩት ሻርኮች በአብዛኛው ሪዮ ዴ ጄኔሪዮ ጠረፍ ላይ በሚገኘው ውቅያኖስ የሚንሸራሸሩ ናቸው።

ሻርኮች ውስጥ ኮኬይን ሲገኝ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ሻርኮቹ ውስጥ የተገኘው የኮኬይን መጠን ከሌሎች የውቅያኖስ እንስሳት ጋር ሲነፃፀር በ100 እጥፍ ከፍ የሚል ነው።

እኒህ ሻርኮች ሰውነታቸው ውስጥ እንዴት ኮኬይን ሊገኝ እንደቻለ ለሚለው የተለያዩ መላ ምቶች እየተሰነዘሩ ነው።

አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚያምኑት ኮኬይኑ ወደ ውሃ እየሄደ ያለው ሕጋዊ ያልሆኑ ቤተ-ሙራዎች ዕፁን ሲያመርቱ አሊያም ደግሞ ከዕፁ ተጠቃሚዎች ዐይነ-ምድር አሊያም ከሽንት ነው።

አንዲት ሴት ሻርክ በእጇ ይዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አጥኚዎች 13 ሻርኮችን መርምረው ኮኬይን እንዳለባቸው ማወቅ ችለዋል

የጥናቱ አዘጋጅ የሆኑት ባዮሎጂስት እና የጥናት ባለሙያ የሆኑት ሬቸል ዴቪስ ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ምክንያቶች በሻርኮች ደም ውስጥ ኮኬይን ሊገኝ እንዳስቻሉ ግምት አላቸው።

በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ምክንያት ውቅያኖስ ውስጥ የተጣለ ጥቅል ኮኬይን ምናልባት ወደ ሻርኮች ሰውነት ተሻግሮ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ቢኖርም አጥኚዎቹ ግን ይህ ግምት ውሃ የሚያነሳ አይደለም ይላሉ።

“በብራዚል ልክ እንደ ፍሎሪዳ እና ሜክሲኮ ይህ የሚያክል መጠን ያለው ኮኬይን ውሃ ውስጥ አይጣልም። ለዚህ ነው እኛ በጥናታችን መሠረት ሁለቱን ምክንያቶች ብቻ ከግምት የምናስገባው” ይላሉ ሬቸል።

ጓንት ያጠለቀ እጅ የቤተ-ሙከራ ቁሳቁስ ይዞ

የፎቶው ባለመብት, Oswaldo Cruz Foundation

የምስሉ መግለጫ, ሻርኮቹ ውስጥ የተገኘው የኮኬይን መጠን ከሌሎች የውቅያኖስ እንስሳት ሲነፃፀር በ100 እጥፍ ከፍ የሚል ነው

'አስጊ ግኝት'

ፖርቹጋል በሚገኘው የሌይሪያ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ እና የባሕር ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት ሳራ ኖቫይስ ግኝቱ “በጣም አስፈላጊ ቢሆንም በተመሳሳይ ደግሞ እጅግ አስጊ ነው” ይላሉ።

በጥናቱ የተካተቱ ሁሉም ሴት ሻርኮች ነብሰ-ጡሮች ነበሩ። ነገር ግን ኮኬይን የተባለው አደገኛ ዕፅ ፅንሱ ላይ ምን ዓይነት አደጋ ሊያመጣ እንደሚችል እስካሁን የሚታወቅ ነገር የለም።

ይህ ዕፅ ሻርኮች ላይ የፀባይ ለውጥ እያመጣ ይሆን የሚለውን ለማየት ቀጣይነት ያለው ጥናት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎቹ ያምናሉ።

ከዚህ ቀደም የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አደገኛ ዕፆች ሰዎች ላይ የሚያመጡት ለውጥ እና እንሰሳት ላይ የሚያስከትሉት ተፅዕኖ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይነት አለው።

እርግጥ ነው አጥኚዎች በሠሩት ጥናት ያካተቱት አንድ የሻርክ ዘር ብቻ ቢሆንም ሌሎችም የሻርክ ዓይነቶች ቢመረመሩ ኮኬይን ሊገኝባቸው እንደሚችል ይገምታሉ።

“ሻርኮች ሥጋ በል ናቸው። የተበከሉ ነገሮች የሚገቡት ምግብ በሚያስገቡበት መንገድ በኩል ነው። ጥናት ያደረግንባቸው ሻርኮች የሚበሏቸው ዓሣዎች ተበክለው ሊሆን እንደሚችል እርግጥ ነው” ይላሉ ሬቸል ዴቪስ።

ሻርፕኖዝ የተሰኘው የሻርክ ዝርያ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮኬይን መተላለፊያ መንገድ

ብራዚል ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የኮኬይን መጠን አለ። ይህ የሆነበት ምክንያት አደገኛውን ዕፅ ለማዘዋወር ብራዚል አመቺ ስለሆነች ነው።

ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ወደ አውሮፓ እና አፍሪካ የሚልኩትን ኮኬይን የሚያስተላልፉት በብራዚል በኩል ነው የሚሉት የሳኦ ፖሎ ዩኒቨርሲቲዋ ሶሲዮሎጂስት ካሚላ ኑኔዝ ዲያዝ ናቸው።

ባለሙያዋ አክለው እንደሚሉት ብራዚል ወሳኝ ሥፍራ ላይ ስለምትገኝ የአደገኛ ዕፅ አከፋፋዮች መከማቻ ሆናለች።

“ሥነ-ምድራዊ ጠቀሜታው የሚመጣው ብራዚል ማዕከል ላይ በመገኘቷ ነው። ምክንያቱም የኮኬይን አምራች የሆኑት ፔሩ፣ ኮለምቢያ እና ቦሊቪያ በምዕራብ ይገኛሉ፤ የአትላንቲክ ውቅያኖስን ለመድረስ ደግሞ የተለያዩ አማራጮች አሉ።”

“መቼም ይህ ለምንም አብዛኛው ወደ አውሮፓ እና አፍሪካ የሚጋዝ አደገኛ ዕፅ በብራዚል በኩል እንደሚጓዝ ለማስረዳት ቀላል ይመስለኛል። አገሪቱ አህጉራትን የምታማክል እና ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ ያለች ናት።”

አንድ ሰማጭ ውቅያኖስ ውስጥ ሲዋኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የባሕር ጠላቂዎች ዕፁን አሰራጭተውት ይሆን?

የጥናቱ ባለሙያዎች ዕፁ ወደ ውቅያኖስ የተሠራጨው ከቤተ-ሙከራዎች ወጥቶ ነው ብለው ባስቀመጡት መላ ምት ኑኔዝ ዲያዝ አይስማሙም።

እሳቸው የሚያምኑት ዕፁን ወደ መርከቦች የሚያጓጓዙ ባሕር ጠላቂዎች (ውስጥ ለውስጥ የሚዋኙ) ውሃውን በክለውታል ብለው ነው።

“እኔ ከሩቅ ሆኜ እንደተመለከትኩት ከሆነ ዕፁን ወደ መርከብ የሚያሳፍሩ ጠላቂዎች ናቸው ሻርኮቹ የሚኖሩበትን ውሃ የበከሉት” ይላሉ በዘርፉ ብዙ ልምድና ዕውቀት ያዳበሩት ባለሙያ።

ኮኬይን የተባለው አደገኛ ዕፅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኮኬይን በበርካታ ሀገራት የታገደ ዕፅ ሲሆን አብዝቶ መጠቀም ለሞት ሊያጋልጥ ይችላል

ሶሲዮሎጂስቷ እንደሚሉት ኮኬይን ወደ ብራዚል የሚመጣው በወንዞች እና በመንገድ አማካይነት ሲሆን፣ ወደ አውሮፓ ደግሞ የሚላከው በመርከብ እና በአውሮፕላን ነው።

ኑኔዝ ዲያዝ እንደሚያብራሩት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የሚጓዘው ኮኬይን በዋናነት በሜክሲኮ እና ኮሎምቢያ አጓጓዦች በኩል የሚጋዝ ቢሆንም ብራዚልም አንዷ መንገድ አድራሻ ናት።

“ሁሉም የብራዚል ድንበሮች መውጫ መንገድ ናቸው። እኒህ የድንበር መውጫዎች በወንጀለኛ ቡድኖች ቁጥጥር ሥር ናቸው።”

የሻርክ ፊን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሻርክ 'ፊን' የተባለው ከውሀ ወጣ ብሎ የሚታየው አካሉ ለገበያ ይቀርባል

ኮኬይኑ ሻርክ የሚበሉ ሰዎችን ሊበክል ይችላል?

ሻርኮችን የበከለው ኮኬይን በምግብ ሰንሰለት በኩል ወደ ሰዎች ሊዛመት ይችላል።

የጥናት ባለሙያዋ ሬቸል ዴቪስ እንደሚሉት ዕፁ ወደ ሰው ልጅ ሊዛመት የሚችለው ብራዚል ውስጥ ዶግፊሽ ሻርክ ተብሎ በሚታወቀው ምግብ አማካይነት ነው።

“ሻርኮች ብራዚል ውስጥ ለምግብነት ይውላሉ። ብራዚል ብቻ ሳይሆን ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሜክሲኮ እና ሌሎች በርካታ አገራት ሻርክ ይመገባሉ።”

“ምግቡ አብዛኛውን ጊዜ ፍሌክ፣ ዓሳ፣ ጥብስ፣ ዶግፊሽ እና ሌሎች ስሞች እየተሰጡት ለገበያ ይቀርባል” ይላሉ ሬቸል።

ከሻርክ ፊን የሚሠራው ሾርባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከሻርክ ፊን የሚሠራ ሾርብ ብራዚል ውስጥ ተወዳጅ ምግብ ነው

ነገር ግን ሻርኮች ሰውነት ውስጥ የተገኘው ኮኬይን ወደ ሰዎች ሲዘዋወር ምን ያህል ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል እስካሁን ግልፅ አይደለም።

ዴቪስ እንደሚሉት “እስካሁን ባለው ሁኔታ በሻርክ ሥጋ ምክንያት የሰው ልጅ ጤና ሊቃወስ ይችላል የሚለው ፅንሰ-ሐሳብ የሚያሳስብ ሆኖ አልተገኘም።”

ሻርኮች እና ሌሎች የዓሳ ዓይነቶች በቆዳቸው በኩል እንዲሁም በጊላቸው ነው ውሃ የሚያስገቡት የሚሉት ዴቪስ አደገኛው ዕፅ ውቅያኖስ ውስጥ የሚዋኙ ሰዎችን የመበከል አቅሙ ይህን ያክል ነው ሲሉ ያስረዳሉ።