በአሜሪካ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር መሪዎች እነማን ናቸው?

እስማኤል “ኤልማዮ” ዛምባዳ እና የኤልቻፖ የ38 ዓመት ልጅዮአኪን ጉዝማን ሎፔዝ
የምስሉ መግለጫ, እስማኤል “ኤልማዮ” ዛምባዳ እና የኤልቻፖ የ38 ዓመት ልጅ ዮአኪን ጉዝማን ሎፔዝ

በሜክሲኮ ውስጥ ስመ ገናና ነው - እስማኤል “ኤልማዮ” ዛምባዳ።

በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ንግድ ውስጥ ስሙ ለአምስት አስርት ዓመታት ገኗል።

“ሁሉም ቦታ ይፈልጉታል። ሰውየው እኮ አልተደበቀም” ይህንን ዘፈን የዘፈኑት የሜክሲኮው ታዋቂ ባንድ ሎስ ቱካንስ ደ ቲጁና ሲሆን መታሰቢያነቱም ለኤል ማዮ ነው።

አሜሪካን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ፖሊስ ግለሰቡን ለመያዝ ሲያድነው ነበር።

ኤልማዮ ዛምባዳ፣ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር እንዲሁም ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን የሚያካሂድ በተለምዶ ጉዝማን ዛምባዳ የሚባል በዓለም አቀፍ የተደራጁ ወንጀሎች ውስጥ ስመ ጥር የሆነውን ቡድን ከመሠረቱት አንዱ ነው።

ቡድኑ በሜክሲኮዋ ሲናሎዋ ግዛት መሠረቱን ያደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም “ኤልማዮ የሲናሎዋ ካርቴል” መሪ የሚል ስያሜንም አግኝቷል።

የ76 ዓመቱ ኤልማዮ ሐሙስ፣ ሐምሌ 18/ 2016 ዓ.ም. በአሜሪካ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ስር ውሏል።

ሌላኛው በቁጥጥር ስር የዋለው በአደንዛዥ ዕጽ ግዛት (ኢምፓየር) መሥርቷል የሚባለው እና ሌላኛው የዚህ ድርጅት መሥራች የሆነው የኤልቻፖ ልጅ የ38 ዓመቱ ዮአኪን ጉዝማን ሎፔዝ ነው።

ኤልቻፖ ወይም ዮአኪን ኤልቻፖ ጉዝማን በአሜሪካ ከአምስት ዓመት በፊት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት በእስር ላይ ይገኛል።

ኤልማዮን ወደ አሜሪካ ለማምጣት የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ምርመራ እና የፌደራሉ ምርመራ ቢሮ ለረዥም ወራት የቆየ ዘመቻ አካሂደዋል።

ከሜክሲኮ በአውሮፕላን እንዲሳፈር የተደረገውም በራሱ ቡድን ሲናሎዋ ከፍተኛ አመራሮች ተታልሎ እንደሆነ ዋል ስትሪት ጆርናል የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ሁለቱ ግለሰቦች በሙስና፣ በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር፣ በሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር እና በሌሎችም ወንጀሎች በዓለማችን ላይ ተፈላጊ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ መያዛቸው ያልተጠበቀ ነው ተብሏል።

ጥላው ብቻ የሚታየው የሚባለው ኤልማዮ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ውስጥ ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ በመንግሥት በጥብቅ ሲፈለግ ቆይቷል።

በዩቲዩብ ላይ 10 ሚሊዮን ሰዎች የተመለከቱን የሎስ ቱካንስ ደ ቲጁና ዘፈን ላይ “ሕግ ሊያቆመው ይፈልጋል። ጠላቶች ሊገድሉት ያድኑታል። ማናቸውም አልተሳካላቸውም፣ የሚገለጥላቸው ሰይጣን ነው” ሲሉ ኤልማዮን ይዘክሩታል።

እስማኤል “ኤልማዮ” ዛምባዳ
የምስሉ መግለጫ, እስማኤል “ኤልማዮ” ዛምባዳ

ከአዘዋዋሪነት ወደ መሪነት

ኤልማዮ በአንድ ወቅት ተራ አዘዋዋሪ ነበር። የተግባር ሰው መሆኑ፣ ሸረኝነቱ፣ ተንኮል እና ሙስና ተጨምረውበት “ካፖ ዴ ካ ፖስ” (የአለቃዎች አለቃ) ሊሆን ቻለ። ኤልማዮ በ1970ዎቹ ነው ወደ ድብቁ የአደንዛዠዥ ዕጽ ዝውውር ዓለም የገባው።

በመጀመሪያው በአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ፈር ቀዳጅ የሚባለው ጓዳላጃራ ካርቴል ውስጥ በአዘዋዋሪነት ይሠራ ነበር። ይህ ቡድን ኦፒየም፣ ዕጸ ፋርስ (ማሪዋና) እንዲሁም ኮኬይንን ያዘዋውር ነበር።

ከዚያም ጁዋሬዝ ካርቴል መካከለኛ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ሥራ አስኪያጅ የነበረ ሲሆን “የሰማዮቹ ጌታ” ከሚባለው ከመሪው አማዶ ካሪሎ ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበራቸው።

ከዚህም በኋላ ነው ኤልማዮ በኮሎምቢያ ውስጥ የግንኙነት መረቦችን በመዘርጋት ኮኬይን አምራች አጋሮችንም ፈጥሯል።

ሌሎች አለቆች ሲሞቱ ወይም ከሥልጣን ሲገለሉ የኤልማዮ ኃያልነትም እየጨመረ መጣ።

ኤልማዮ አጋሮቹን ለመክዳት ብዙም አያቅማማም።

ነገር ግን ከሌሎች የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር መሪዎች የሚለየው ነገር ቢኖር ልታይ ልታይ አይልም። ማንነቱ የተደበቀ ነው። የኤልማዮን ፎቶዎች ማግኘት ፈታኝ ነው። የለምም ማለት ይቻላል።

የፊቱን ገጽታ ለመቀየር ቀዶ ህክምና እንደተደረገለት ይነገራል። የሚያውቁት ሰዎች 1.8 ሜትር ቁመት እንዳለው፣ ሰውነቱ ግዙፍ የሚባል እና ጠንካራ እንደሆነ ይነገራል። በተጨማሪም በርካታ ሚስቶች እና ልጆች አሉትም ተብሏል።

አንድ ሚሊዮን ዶላር በጀት ለጉቦ

ከኤል ማዮ ልጆች አንዱ ቪሴንቴ ዛምባዳ ኒብላ በአውሮፓውያኑ 2009 በሜክሲኮ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።

ልጅየው የዚያን ጊዜ ለአሜሪካ ባለሥልጣናት በሰጠው ምስክርነት አባቱ ለጉቦ የሚሆን በወር አንድ ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚመድብ ይፋ አድርጓል። የአጋሮቹ የትስስር መረብም ኔትወርክ ባንኮችን እና መንግሥታትን እንደሚያጠቃልልም ተናግሯል።

ኤልማዮ ከሚኖርበት ማኅበረሰብ ጋር የጠነከረ ግንኙነት ካላቸው የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር መሪ አንዱ እንደነበረም ተዘግቧል።

የኤል አላሞ፣ የትውልድ ቀየው ራንቼሪያ እንዲሆም በሲናሎዋ ክልል ባሉ ከተሞች መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት እንዲሁም ክብረ በዓላትን ለማክበር የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ሰው ነበር።

የኤልቻፖ የ38 ዓመት ልጅ ዮአኪን ጉዝማን ሎፔዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኤልቻፖ የ38 ዓመት ልጅ ዮአኪን ጉዝማን ሎፔዝ

ከኤልቻፖ ወራሾች አንዱ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሐሙስ ዕለት ከኤልማዮ ጋር ስለታሰረው የኤልቻፖ ልጅ ዮአኪን ጉዝማን ሎፔዝ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም።

ኤልጉየሮ በመባል የሚታወቀው ይህ የ38 ዓመቱ ግለሰብ ኤልቻፖ ከሁለተኛዋ ሚስቱ የወለደው ነው።

ኤልቻፖ ከሦስት ሚስቶቹ አስር ልጆችን ወልዷል።

ኤልጉየሮ በኤልቻፖ ልጆች የተመሠረተው ሎስ ቻፒቶስ የተሰኘ ቡድን አባል ነው። በዚህ ቡድን ውስጥ ባለፈው ዓመት በሜክሲኮ በቁጥጥር ሥር ውሎ ለአሜሪካ ተላልፎ የተሰጠው የኤልጉየሮ ወንድም ኦቪዶም አባል ነው።

ኤልጉየሮ በዚህ የወንጀለኛ ቡድን የነበረው ሚና ከኦቪዲዮ በመቀጠል ሁለተኛ ሰው እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።

ሆኖም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኤልጉየሮ በሎስቻፒቶስ እንዲሁም በሲናሎዋ ካርቴል “በከፍተኛ ደረጃ የማዘዝ እና የቁጥጥር ተግባራትን የመፈጸም ሥልጣን አለው” ብሏል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት የኤልቻፖ የበኩር ልጅ ኤድጋር ከሞተ በኋላ ኤልጉየሮ እና ኦቪዶ የአደንዛዡን ዕጽ ዝውውር ንብረትን እንደወረሱ እና በሜክሲኮ ማሪዋና እንዲሁም በኮሎምቢያ ኮኬይን ግዢዎች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዳፈሰሱ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ኤልቻፖ በሜክሲኮ ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግለት እስር ቤት በአውሮፓውያኑ 2015 እንዲያመልጥ ሁለቱ ልጆቹ መሳተፋቸውም ተነግሯል።

በአደንዛዥ ዕዝ ዝውውር እና በግድያ ወንጀሎች ተከሶ እስር ቤት ወርዶ የነበረው ኤልቻፖ በሜክሲኮ ሁለት ጊዜ ከእስር ቤት አምልጧል።

ሁለቱ የኤልቻፖ ልጆች በሜክሲኮ ሲናሎዋ ግዛት ሜታአምፊታሚን የተባለውን አደንዛዥ ዕጽ የሚያመርቱ ቢያንስ 11 ላብራቶሪዎች እንደነበሯቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር የዋለው ኤልጉየሮ በአሜሪካ የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውር ክስ የተመሠረተበት በአውሮፓውያኑ 2018 ነበር።