ሴራሊዮን ከሰው አጥንት በሚቀመም የአደንዛዥ እፅ መስፋፋት ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ አወጀች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሴራሊዮኑ ፕሬዚደንት በአገሪቷ በተንሰራፋው ‘ኩሽ’ እየተባለ በሚጠራው የአደንዛዥ እፅ ምክንያት ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ።
ኩሽ የተለያዩ ሱስ የሚያስይዙ ግብዓቶችን በመደባለቅ የሚሰራ እፅ ሲሆን ለዓመታት በአገሪቷ ተንሰራፍቶ ይገኛል።
በዚህ አደንዛዥ እፅ ውስጥ ከሚጨመሩ ግብዓቶች መካከል አንዱ የተፈጨ የሰው አጥንት ነው።
በዚህም ምክንያት ከመቃብር ውስጥ አፅም ለማውጣት የሚቆፍሩ ሱሰኞችን ለማስቆም የጸጥታ አካላት በመካነ መቃብር ሥፍራዎች የሚያደርጉትን ጥበቃዎች አጠክረው ቆይተዋል።
ፕሬዚደንት ጁሊየን ማዳ ባዮ አስተዳደራቸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ ያስገደደውን ይህንን እፅ “የሞት ወጥመድ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን በአገሪቷ ላይም የህልውና ቀውስ ፈጥሯል ብለዋል።
በኩሽ እፅ የናወዙና እግራቸው ያበጠ በአብዛኛው ወንድ ወጣቶችን በሴራሊዮን ጎዳናዎች ጥጋ ጥግ ላይ ተቀምጠው ማየት የተለመደ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገረው አንድ ወጣት ከተዘፈቀበት ሱስ ለመውጣት እንዳዳገተው ተናግሯል።
እስካሁን በዚህ እፅ ምክንያት የምን ያህል ሰዎች ሕይወት እንደተቀጠፈ በይፋ የተገለጸ ቁጥር የለም።
ሆኖም አንድ ሐኪም ለቢቢሲ እንደተናገሩት በዋና መዲናዋ ፍሪታውን በቅርብ ወራት ውስጥ ኩሽ በተባለው እፅ ምክንያት ባጋጠማቸው ውስጣዊ የሰውነት አካል ጉዳት ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት ወንዶች ሞተዋል።
አደንዛዥ እፁ በአዕምሮ ጤና ላይም ከፍተኛ ቀውስ አስከትሏል።
በአገሪቷ ውስጥ ያለው ብቸኛው የሥነ አዕምሮ ሆስፒታል እንደገለጸው በአውሮፓውያኑ 2020 እና 2023 መካከል ባሉት ዓመታት ውስጥ ከእፁ ጋር በተገናኘ ወደ ሆስፒታሉ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በ4 ሺህ በመቶ ገደማ ጨምሮ ቁጥራቸው 1 ሺህ 865 ደርሶ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ኩሽ የተባለውን እፅ የሚጠቀሙ ሰዎች በመበራከታቸው ምክንያት በፍሪታውን ከተማ የሚገኘው ዋና መካነ መቃብር አፅም ለማውጣት መቃብር የሚቆፍሩ ወጣት ወንዶችን ለመከላከል የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግለት ለመጠየቅ ተገዷል።
ምክንያቱ ግልጽ ባይሆንም የኩሽን እፅ ለመስራት ጥቅም ላይ ከሚውሉ በርካታ ግብዓቶች መካከል የተፈጨ የሰው አጥንት አንዱ ነው።
ፕሬዚደንት ባዮ ሐሙስ ምሽት በአገሪቷ ብሔራዊ ጣቢያ ባስተላለፉት መልዕክትም “ በአደንዛዥ እፅ በተለይም ሰው ሰራሽ በሆነው የኩሽ እፅ ምክንያት አገራችን የሕልውና ስጋት ተደቅኖባታል” ብለዋል።
ፕሬዚደንቱ ጨምረውም በእፁ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እንዳሻቀበ ተናግረዋል።
በመሆኑም ባለሥልጣናት በአደንዛዥ እፆች በተለይም በኩሽ ምክንያት የሚደርሰውን ቀውስ ለመከላከል ብሔራዊ ግብረ ኃይል እንዲያቋቁሙ መመሪያ ሰጥተዋል።
በዚህ እፅ ሱስ ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች እንዲያገግሙ እንክብካቤና ድጋፍ ለማድረግ በየወረዳው ማዕከላት እንዲቋቋሙ እና የሰለጠኑ ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ እንዲመደቡ እንደሚደረግም ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል።
አሁን ላይ አገልግሎት የሚሰጥ የአደንዛዥ ዕፅ ማገገሚያ ማዕከል ያለው በመዲናዋ ፍሪታውን ከተማ ብቻ ነው። ይህም ማስተናገድ ባለመቻሉ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በጦሩ ማሰልጠኛ ማዕከል ውስጥ 100 አልጋዎች ያሉት ማገገሚያ በአፋጣኝ ተዘጋጅቶ ነበር።
ሆኖም በቂ ባለሙያዎች እና ቁሳቁሶች የተሟሉለት አልነበረም። በዚህም ምክንያት ባለሙያዎች ከማገገሚያነቱ ይልቅ “ማከማቻ ቦታ” ሲሉ ነበር የሚገልጹት።
በሱሱ ለተዘፈቁ ሰዎች ከሚደረገው እንክብካቤ ባሻገርም ፕሬዚደንቱ ሕግ አስፈጻሚ አካላት ምርመራ በማድረግ፣ በማሰር እና ፍርድ በመስጠት የአደንዛዥ እፅ ዝውውር ሰንሰለቱን መበጠስ ይገባቸዋል ብለዋል።
የፍሪታውን ከተማ ምክትል ከንቲባ ክዌኩ ሊስክ በበኩላቸው መቃብር ቆፋሪዎችን ለመከላከል ቢሯቸው ከፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግለት መጠየቁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በኪሲ ጎዳና የሚገኘውንና አጥር የሌለውን ትልቁን መካነ መቃብር ለመጠበቅ ምሽት ላይ የፖሊስ ስምሪት ይደረጋል።
የባዮ አስተዳደር የኩሽ እፅን በተመለከተ ምላሽ ለመስጠት ተነሳሽነት የላቸውም በሚል በበርካቶች ዘንድ ሲተች ቆይቷል።
የሴራሊዮን ሥነ አዕምሮ ሆስፒታል ኃላፊ ኦክተር አብዱል ጃሎህ አሁን ላይ ፕሬዚደንቱ ያወጁት አስቸኳይ ጊዜ ትክክለኛ እና ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል።
ዶክተር አብዱል ጃሎህ እንዳሉት በሆስፒታሉ ውስጥ ተኝተው ከሚታከሙ ህሙማን መካከል 63 በመቶ የሚሆኑት ከኩሽ እፅ ጋር በተያያዘ የገቡ ናቸው።












