ለእንቅልፍ የሚውለውን ሜላቶኒን ከመጠን በላይ ሲወስዱ ምን ይገጥመዎታል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሜላቶኒን እንቅልፍ በሚያስቸግራቸው ሰዎች ተወዳጅነትን እያተረፈ ያለ አጋዥ ንጥረ ነገር ነው።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሜላቶኒንን ከመጠን በላይ መውሰድ በጣም እየጨመረ ይገኛል።
ንጥረ ነገሩን ከመጠን በላይ መውሰድ ምን ያህል ጉዳት ያደርሳል?
ዘመናዊ ስልካችሁን አልጋችሁ ላይ የምትጠቀሙ ሰዎች ምን ያህሎቹ ናችሁ?
ወቅታዊ ዜናዎችን ከማግኘት እስከ ማኅበራዊ የትስስር ገጾችን በምሽት መጎብኘት ድረስ ከስልኮች ሰማያዊ መብራት (ብሉ ላይት) ያን ያህል ሩቅ አይደለንም።
ነገር ግን ጥናቶች የመኝታ ጊዜን በስልክ ስክሪኖች መተካት በእንቅልፍ ላይ ከባድ ተጽዕኖ እንዳለው አረጋግጠዋል። ለዚህም ምክንያቱ በአንጎል የፒናል ዕጢ የሚመነጨው ሜላቶኒን የተባለው ሆርሞን ነው።
ሜላቶኒን በሰውነት ውስጥ የእንቅልፍ ዑደትን ለመቆጣጠር ቁልፍ ሚና አለው። አንዳንዴም “የጨለማው ሆርሞን” በመባል ይገለጻል።
በቀን መጠኑ ዝቅተኛ፤ በምሽት ጨለማው ጊዜውን ሲረከብ ደግሞ ከፍ ይላል።
በመኝታ ጊዜ እንደ ኤሌክትሮኒክስ ስክሪን ያሉ ብርሃንን የሚጨምሩ ማንኛውም ቁሶች የሰውነታችንን ተፈጥሯዊ የሜላቶኒንን ምርት ሂደትን ያደናቅፋሉ። እናም እንቅልፍ የማይጨበጥ ይሆናል።
ይህም በአሜሪካ ውስጥ ከሦስት አዋቂ ሰዎች በአንዱ ላይ ማግኘት ያለባቸውን ከሰባት እስከ ስምንት ሰዓት እንቅልፍ አለማግኘታቸውን ለማስረዳት አጋዥ ነው።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የእንቅልፍ እጦትን፣ የአውሮፕላን ጉዞ ድካምን ወይም ከምሽት ሥራ በኋላ የሚገጥምን የእንቅልፍ ችግርን ለመቅረፍ ፊታቸውን ወደ ሜላቶኒን አጋዦች ማዞራቸው አያስደንቅም።
ሜላቶኒን በዩናይትድ ኪንግደም በሐኪም ትዕዛዝ የሚሰጥ ቢሆንም፤ በአሜሪካ ግን በመደብሮች እና በፋርማሲዎች ውስጥ ካለሐኪም ትዕዛዝ ከቫይታሚን አጋዦች ቀጥሎ ይገኛል።
ሕጻናት እንኳ ምሽቱን በሙሉ እንዲተኙ ከልጅነታቸው ጀምሮ በማስቲካ መልክ ተሠርቶ ይሰጣቸዋል።
ሆኖም ሜላቶኒን እንደሚወራው ለደኅንነት የማያሰጋ ላይሆን ይችላል በሚል በህክምና ባለሞያዎች መካከል ሰፊ ክርክር አለ።
በቦስተን የህጻናት ሆስፒታል የልጆች ሐኪም የሆኑት ማይክል ቶሴ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ የሚያሳስብ አዝማሚያ አይተዋል። ሜላቶኒን ከመጠን በላይ ወስደው ሆስፒታል የሚገቡ ህጻናት ቁጥር እያሻቀበ መሆኑን ታዝበዋል።
“በድንገት ሜላቶኒን የወሰዱ ህጻናትን እና ራሳቸውን ለመጉዳት ሜላቶኒንን የወሰዱ ታዳጊዎችን እያየን ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቶሴ በጋራ ያጠኑት የአውሮፓውያኑ የ2022 ጥናት፤ ከ2012 እስከ 2021 ባሉት ጊዜያት ልጆች የሜላቶኒን ከመጠን በላይ የመውሰድ የአደጋ በ530 በመቶ ከፍ ብሏል።
የመመረዝ መቆጣጠሪያ አገልግሎት መሥሪያ ቤቶቸ 2020 ልጆች ከሌሎች ንጥረ ነገር በበለጠ ሜላቶኒንን ከመጠን በላይ በመውሰድ ከፍተኛ የስልክ ጥሪዎችን የተቀበለቡት ዓመት ነው።
የዚህ ጥናት ውጤት ሰኔ 2023 ከወጣ ሌላ ጥናት ጋር ተመሳሳይ ሆኗል። ጥናቱ ባለፉት አስር ዓመታት ከመጠን በላይ ሜላቶኒን በመውሰድ በሆስፒታሎች የድንገተኛ ክፍል የገቡ ህጻናት በ420 በመቶ መጨመሩን ጠቅሷል።
“የመመረዙ መጨመር የሜላቶኒን ጥቅም ላይ መዋል መጨመር ሁለተኛው ተጽዕኖ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው” ሲሉ ቶሴ ተናግረዋል።
በቅርብ ዓመታት ከሜላቶኒን ጋር በተያያዘ ለህክምና የሚመጡ ህጻናት አሃዝ እንደጨመረው ሁሉ፣ ሽያጩም ከፍ ብሏል።
ልጆች በአካባቢያቸው ባሉ ነገሮች ነው የሚመረዙት። ስለዚህም የሜላቶኒን አቅርቦት መጨመር ወደ መመረዝ መጨመር ይወስዳል።
በሁለቱም ጥናቶች የተካተቱ ህጻናት ምንም አይነት ምልክት አለማሳየታቸውን ማጤን አስፈላጊ ነው። ምልክት ካሳዩም እንደ ሆድ ህመም፣ ትውከት እና መጫጫን የመሳሰሉ አነስተኛ ምልክቶች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነገር ግን 260 ሺህ 435 የሜላቶኒን ተጠቃሚዎችን በተመለከተው የማይክል ቶሴ ሰፋ ያለ ጥናት፤ ወደ 300 የሚጠጉ ህጻናት ከፍተኛ ክትትል የሚሹ ሆነዋል።
አምስቱ ደግሞ የመተንፈሻ ማሽን (ቬንትሌተር) እንዲገጠምላቸው የግድ ብሏል። የሁለት ህጻናት ሕይወት ደግሞ አልፏል።
ሜላቶኒን ከሌሎች የጨቅላ ህጻናት የህልፈት ምክንያቶች ጋርም ግንኙነት አለው።
በ2019 (እአአ) የተካሄደ ጥናት ሁለት የዘጠኝ ወር እና የ13 ወር ልጆች ሕይወታቸው አልፎ ተገኝቷል።
የተደረገው የደም ምርመራ ውጤት በሁለቱም ህጻናት ላይ ሜላቶኒን እንደተገኘ አሳይቷል። በ13 ወር ዕድሜ ህጻኑ ላይ ሜላቶኒን በጡጦው ላይ ተገኝቷል።
ነገር ግን በሁለቱም ህጻናት ሞት ላይ ሌሎች እክሎች ሚና እንደነበራቸው ተነግሯል።
የመጀመሪያው ህጻን ከታላቅ ወንድሞ ጋር እንደተኛ ነበር የተገኘው። ሁለተኛው ልጅ ደግሞ ሞቃታማ በሆነ ክፍል ውስጥ ብቻውን የተገኘ ሲሆን፤ ሁለቱም ሁነቶች ለድንገተኛ የጨቅላ ልጆች ሞት አደጋ የሚሆኑ ናቸው።
ይህ ሁኔታም በአዋቂ ሰዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን እንደሚኖረው የሚያሳዩ ሪፖርቶችም አሉ።
ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ይፋ ሆነ ጥናት የ21 ዓመት ወጣት ከመጠን በላይ ሜላቶኒንን ለእንቅልፍ እጦት የጉንፋን መድኃኒት ከሆነው ዳይፈንሃይደረሚን ጋር በመውሰዷ ሕይወቷ ማለፉን ጠቅሷል።
ነገር ግን እነዚህ ሞቶች እና ከፍተኛ ተጽዕኖዎች በሜላቶኒን ምክንያት ላይከሰቱ የሚችሉበት ዕድል አለ። የችግሩ አንድ አካል ሜላቶኒን አጋዥ ንጥረ ነገር ተብሎ በመለየቱ በምግብ እና በመድኃኒት አስተዳደር ቁጥጥር አይደረግም። ጥብቅ የክሊኒካዊ ፍተሻም አልተካሄደበትም።
በመሆኑም ሆርሞኑ በሰውነታችን ውስጥ ምን ዓይነት ተጽዕኖ እንዳለው ሙሉ በሙሉ መረዳት አይቻልም። ከሌሎች መድኃኒቶች እና አጋዥ ንጥረ ነገሮች ጋር የሚኖረውን ግንኙነትም ማወቅ አይቻልም።
በተለያዩ ምርቶች ላይ የሜላቶኒን መጠን የተለያየ ነው።
በኦክስፈርድ ዩኒቨርስቲ የሰር ጁልስ ቶርን ኒዮሮሎጂካል ኢንስቲትዩት የጋራ ዳይሬክተር “ቀውስ ነው ያለው” ይላሉ።
“ሰዎች ሜላቶኒን ያለባቸውን ምርቶች ገዝተው መጠናቸውን በመለካት ጥናቶች ሰርተዋል፤ እናም መጠኑ በእሽጉ ላይ እንደሚለው ሆኖ አልተገኘም።”
ሜላቶኒን ሞቶችን እእና ከባድ እክሎችን እንደሚያስከትል የሚያሳይ የታወቀ ዘዴ የለም። በአይጦች ላይ የተካሄዱ ጥናቶች ሜላቶኒን በከፍተኛ መጠን (ከ400 ሚሊ ግራም በላይ) ሲሰጥ መርዛማ ተጽዕኖ እንዳለው አሳይተዋል።
ነገር ግን ይሄ መጠን ለእንቅልፍ እጦት ከሚሰጠው ከሁለት እስከ 10 ሚሊ ግራም በሺዎች እጥፍ የሚበልጥ ነው።
የሜላቶኒን ተቀባዮች በሥነ ተዋልዶ፣ በደም እና በልብ ዝውውር እንዲሁም በበሽታ መከላከያ ሥርዓቶች ጨምር በሁሉም የሰውነት ክፍሎች እንደሚገኙ እናውቃለን።
ነገር ግን ከአንጎል ውጪ ያለው ተጽዕኖ እምብዛም አይታወቅም። ይሁን አንጂ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጽዕኖውን ሳይገነዘቡ ሜላቶኒንን ይወስዳሉ።
“ሁሉም መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው፤ ስለዚህ የእንቅልፍ እጦትን ለማከም ከሌሎች መድኃኒቶች በደኅንነቱ በአንጻራዊነት የተሻለ ተደርጎ ይወሰደል” ሲሉ የቦስተን የህክምና ማዕከል የእንቅልፍ እጦት ክፍል ዳይሬክተር እና ተባባሪ ፕሮፌሰር ሳንፎርድ አሩባች ይናገራሉ።
“ሆኖም የማይታወቁ ጉዳዮች ናቸው የሚያሳስቡት ብዬ አስባለሁ። ይህ በማደግ ላይ ላለ ልጅ ከረሰጠ፤ ከ10 ዓመታት በኋላ የሚኖረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? አናውቅም። ምን ያህል መጠን ያለው ሜላቶኒን ነው በጣም ከፍተኛ የሚባለውን እንኳ አናውቅም። ምክንያቱም እነዚህ ጥናቶች ስላልተሰሩ” ይላሉ።















