ሕጻናት ሳያቋርጡ እንዲተኙ ማሠልጠን ይጠቅማል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዌንዲ ሀል ካናዳዊ የእንቅልፍ አጥኚ ናቸው። ከስምንት ዓመት በፊት 235 ቤተሰቦችን ያማከለ ጥናት ሠርተዋል።
ጥናቱ ልጆችን መተኛት ማስተማር ላይ ያተኮረ ነበር። ከስድስት እስከ ስምንት ወር የሆናቸው ሕጻናትን አሳትፏል።
ቤተሰብ ልጆቹን ሳያባብል ልጆቹ በራሳቸው እንቅልፍ እንዲወስዳቸው ማድረግን ይዳስሳል።
ወላጆች የተለያየ መንገድ በመጠቀም ልጆቻቸውን ያስተኛሉ። ልጆቹን ሳያባብሉ ለማስተኛት የሚጠቀሟቸው መንገዶችም አሉ። ልጆች ከተኙ በኋላ ሲነቁ ሳያባብሏቸው ልጆቹ ተመልሰው እንዲተኙ ማድረግንም ያካትታል።
አንዳንድ ወላጆች ልጃቸውን የሚያባብሉበትን የጊዜ ክፍተት ይወስናሉ። ልጆች ሲያለቅሱ ሳያባብሉ የሚተዋቸውም አሉ።
ይህ በሁሉም አገር የሚዘወተር አይደለም። ለምሳሌ የአሜሪካ እናቶች ከልጃቸው በተለየ ክፍል ሲተኙ ለማያን እናቶች ይህ የሚታሰብ አይደለም።
ልጆች በአግባቡ ሳይተኙ መቅረታቸው ወይም ደጋግመው ከእንቅልፍ መነሳታቸውን እናቶች ከሚገጥማቸው ድብታ ጋር የሚያያይዙ አሉ።
ከአሥር የአሜሪካ መጻሕፍት ስድስቱ ልጆች ሲያለቅሱ አታባብሉ ይላሉ። በካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊዘርላንድ እና ጀርመን ያሉ ቤተሰቦችም ይህንን መንገድ ይከተላሉ።
ወላጆች ልጆቻቸውን መተኛት የሚያስተምሩበትን መንገድ የሚጠቁሙ መጻሕፍትና ጥናቶች በርካታ ናቸው።

የዌንዲ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ልጆቻቸውን እንዴት ማስተኛት እንደሚችሉ መመሪያ የተሰጣቸው ወላጆች በተሻለ ሁኔታ ልጆቻቸውን ያስተኛሉ።
ልጆቹ ዘለግ ላለ ጊዜ ይተኛሉ፤ ከእንቅልፍ የሚነሱበት ጊዜም ያጥራል።
የሕጻናት ሐኪሞች በተለይ በአሜሪካ እና አውስትራሊያ ልጆችን መተኛት ማሠልጠንን ሲደግፉ የሕጻናት አእምሮ ጤና ባለሙያዎች እምብዛም አይደግፉትም።
በጉዳዩ የሚሠሩ ጥናቶች በየጊዜው ውጤታቸው አዳዲስ ነገር ያሳያል። አንዳንድ ቤተሰብ ልጁ ከመተኛቱ በፊት ትንሽ እንደሚያለቅስ ወይም ከነጭራሹ እንደማያለቅስ በመግለጽ ልጁን መተኛት ማሠልጠን አስፈላጊነቱ አይታየውም።
ለዚህ ጥናት የሚመረጡ ቤተሰቦች ጥናቱ መሀል ላይ ማቋረጥና የእንቅልፍ ጉዳይ በቀላሉ ለመረዳት የተመቸ አለመሆኑ ምርምሩን ፈታኝ ያደርጉታል።
ልጆች ከእንቅልፋቸው ሲነቁ እንዳያለቅሱ ማስተማር ከተቻለ፣ ወላጆቻቸውን በለቅሶ አይቀሰቅሱም። ያ ማለት ደግሞ ወላጆች ልጆቹ ተኝተው እንዳደሩ ያስባሉ ማለት ነው።
እነዚህ ጥናቶች ወላጆች በሚሰጡት ምላሽ እና በወላጆች ምልከታ ላይ መመሥረታቸውም ጥናቱን ፈታኝ ያደርገዋል።
በዌንዲ ጥናት፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለተወሰነ ጊዜ አባብለው ለተወሰነ ጊዜ እንዲተዋቸው ይደረጋል። የሚያባብሉበትና የሚተውበት ሰዓት ተመጣጣኝ እንዲሆን ይነገራቸዋል።
ልጆች ሲያለቅሱ ልጆቹ ካሉበት ክፍል የሚወጡና እዛው ክፍል ውስጥ ሆነው ከማባበል የሚታቀቡም አሉ።
ይህንን ሥልጠና የወሰዱ ቤተሰቦች ልጆች ዘለግ ላለ ጊዜ እንደተኙ የዌንዲ ጥናት ይጠቁማል።
“ከሠለጠኑት ልጆች መካከል ከእንቅልፋቸው ቢነቁም ወላጆቻቸውን ያላነቁ ሕጻናት አሉ” ይላሉ አጥኚዋ።
የእንቅልፍ ቆይታን የሚመዘግብ መሣሪያ ተጠቅመው ባገኙት ውጤት፣ ሥልጠና የተሰጣቸው ልጆች እንቅልፍ ከ188 ደቂቃ ወደ 204 (በ8.5%) መሻሻሉን ደርሰውበታል።
ልጆቻቸው አልቅሰው ያልቀሰቀሷቸው ቤተሰቦች የተሻለ እንቅልፍ ማግኘታቸውንና አለመዳከማቸውን ገልጸዋል።
ሕጻናትን ማሠልጠን ይጠቅማል?
ከ19ኛው ክፍል ዘመን በፊት የልጆችን እንቅልፍ ማንም ጉዳይ አይለውም ነበር። የኢንዱስትሪ አብዮት ግን ይህን ለወጠ።
ወላጆች ዘለግ ላለ ጊዜ ከመሥራታቸወ ጋር በተያያዘ ነው ለውጡ የመጣው።
የሕጻናት ሕክምና ‘አባት’ የሚባሉት ኤሜት ሆልት፣ ልጆች ሲያለቅሱ ‘ሳንባቸው ስለሚሰፋ’ ማልቀሳቸውን ያበረታቱ ነበር።
ከአንድ እስከ ሦስት ሰዓት ሕጻናት ቢያለቅሱ እንደማይጎዳ ያምናሉ።
እአአ በ1985 ሪቻርድ ፌርበር የተባሉ ተመራማሪ ጉዳዩን ምሁራዊ ገጽታ ሰጡት።
ሕጻናት ስድስት ወር ሳይሞላቸው በፊት የእንቅልፍ ሥልጠና መስጠትን ዌንዲ አይደግፉም። አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ያለፉ ልጆች ላይም የሥነ ልቦና ጫና ሊያሳድር ይችላል ይላሉ።
በአነስተኛ ሁኔታ የሚያለቅሱ ልጆች ዕድሜያቸው ሲገፋ ድብታን ጨምሮ ሌሎችም እክሎች እንዳልገጠሟቸው የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ።
አንዳንድ ሕጻናት ብዙም ባያለቅሱም አንዳንድ ሕጻናት እስከሚያስመልሳቸው ድረስ ለሰዓታት ያለቅሳሉ። ለዚህ ነው ወላጆች ለልጆቻቸው የእንቅልፍ ሥልጠና መስጠት የሚመርጡት።
ከሚጠቀሱት መንገዶች መካከል ልጆች ሲያለቅሱ ከማባበል በፊት ዘለግ ያለ ጊዜ መቆየት፣ ልጆችን ሳያቅፉ አስተኝቶ ከተኙ በኋላ ክፍሉን ለቆ መውጣት ይጠቀሳሉ።

አንዳንድ እናቶች ልጆቻቸውን መተኛት ማሠልጠናቸው እንደረዳቸው ቢናገሩም፣ ሌሎች እናቶች ለውጡ ዘላቂ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።
ልጆቻቸው ስምንት ወር ሆኗቸው ይህንን መንገድ ከሞከሩ እናቶች 65% ልጆቻቸው አሥር ወር ሲሞላቸው እንቅልፍ እምቢ እንዳሉ ተናግረዋል። 39% ደግሞ ልጆቻቸው 12 ወር ሲሆናቸው እንቅልፍ በአግባቡ እንዳልተኙ ገልጸዋል።
ይህ ማለት ሥልጠናው አይሠራም ማለት ሳይሆን፣ ተከታታይነት ይሻል ማለት ነው።
የካናዳ አንድ ጥናት እንደሚለው፣ ወላጆች ልጆቻቸው አንድ ዓመት እስከሚሆቸው ሥልጠናውን እስከ አምስት ጊዜ ሞክረዋል።
የአውስትራሊያ ጥናት ደግሞ ሁለት ዓመት ድረስ ለውጡን ተከታትሏል።
ስድስት ዓመት የሞላቸውና ሥልጠናውን የወሰዱ እና ያልወሰዱ ልጆች መካከል የእንቅልፍ፣ የባህሪ፣ ከቤተሰብ ጋር ያላቸው ቁርኝት እና የኮሪስቶል (cortisol) መጠን ልዩነት አልታየም።
የአውስትራሊያ ብሔራዊ የሕክምና ጥናት ባለሙያ ሀሪየት ሂስኮክ እንደሚሉት፣ ልጆቹ ዕድሜያቸው ከፍ ሲል የባህሪ ለውጥ አላስተዋሉም።
246 እናቶችና ሕጻናት ያሳተፈ አንድ የካናዳ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ለልጆቻቸው ሥልጠና እንዲሰጡ በተመከሩ እና ባልተመከሩ እናቶችና ልጆቻቸው መካከል ልዩነት አልታየም። ሌላ 802 ቤተሰቦች ያማከለ ጥናትም ይህንኑ አረጋግጧል።
ጆዲ ሚንዲል በፊላደልፊያ የእንቅልፍ ተመራማሪ ናቸው።
ልጆችን የማሠልጠን ግብ ከእንቅልፍ እንዳይነቁ ወይም ብዙ እንዲተኙ ማድረግ ሳይሆን፣ ከእንቅልፍ ሲነቁ በራሳቸው ጥረት ተመልሰው እንዲተኙ ማድረግ ነው ይላሉ።
ልጆች ለመመገብ፣ ለመታቀፍ ወይም ከቤተሰቦቻው እንደተለዩ ተሰምቷቸው ከሚፈጠር የአእምሮ ጤና ቀውስ ለመውጣትም ከእንቅልፍ መንቃታቸው አይቀርም።
ዱርሀም የተባለ የሕጻናት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ሔለን ቤል እንደሚሉት፣ በእነዚህ ጥናቶች አማካይነት የሚገኙ ውጤቶች መሬት ላይ ያለውን እውነታ ላያሳዩ ይችላሉ።
ማባበል ጠቃሚ ነው?
ልጆች ሥልጠና ቢሰጣቸውም ከእንቅልፍ መንቃት አለማቆማቸው ሌላ ጥያቄ ያጭራል። ይህም ልጆች ከእንቅልፋቸው የሚነቁት ራሳቸውን ከጭንቀት ለማረጋጋት ነው? ወይስ እንክብካቤ አጥተው በመጨነቃው ነው? የሚለው ነው።
ይህንን ለመረዳት ኮሪስቶል የተባለውን ሆርሞን መለካት አንድ መንገድ ነው።
ይህ ሆርሞን ከጭንቀት ጋር የተያያዘ ነው። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ልጆች እንቅልፍ እንዲተኙ ለማድረግ ጣልቃ ከተገባ በኋላ የኮሪስቶል መጠን ጨምሮ ታይቷል። በሌሎች 43 ልጆች ላይ ደግሞ መጠኑ ቀንሷል።
ከአምስት ዓመት በኋላ በአውስትራሊያ በተሠራ ጥናት ግን ልዩነቱ ጠፍቶ ተመሳሳይ ነጥብ ላይ ደርሶ ነው የተገኘው።
ይህ ሆርሞን በቀን ውስጥ በተለያየ ምክንያት ስለሚለዋወጥ እንደ መለኪያ መጠቀም የለብንም ብለው የሚከራከሩ ምሁራንም አሉ።
ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው አባብለው ወደ እንቅልፍ የሚመለሱበት ሂደትን ዕውቅና የሰጡት ቶማስ አንደርስ የተባሉ ምሁር በ1970ዎቹ ነው።
ይህም ያለ ቤተሰብ ጣልቃ ገብነት ተመልሶ ከመተኛት ጋር ይገናኛል።
ልጆች እንዲተኙ ማሠልጠን በዘለቄታው አእምሯዊ ጤናቸው እና ከቤተሰባቸው ጋር ባላቸው ቁርኝት ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ጥናቶች ጠቁመዋል።

ከሌሎች አጥቢ እንስሳት አንጻር የልጆች አእምሮ ሳይበስል ነው የሚወለዱት፤ መጠኑም ከአዋቂዎች በአንድ ሦስተኛ ያንሳል። እስከ 20ዎቹ ዕድሜ ክልል ድረስ አእምሮ ቀስ እያለ ያድጋል።
ለዚህም ነው ልጆች ሲከፉ የሚያጽናናቸው የሚፈልጉት። ከስድስት ወር እስከ 12 ወር ባሉት ጊዜያት ስሜትን መቆጣጠር እየዳበረ ይሄዳል።
በካሊፎርንያ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት የሥነ ልቦና ምሁር ዳን ሲግል፣ የመጀመሪያው ዓመት ራስን መቆጣጠር ለመማር ቁልፍ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ቤተሰቦች ለሕጻናት የሚሰጡት ምላሽ፣ ከሕጻናቱ የቋንቋ ክህሎት፣ የሥነ ልቦና እድገት ጋርም ይገናኛል። በልጅነት ጭንቀት ሲበዛ ዕድሜ ከጨመረ በኋላም ለጭንቀት ይዳርጋል።
ልጆች በተደጋጋሚ ሲያለቅሱ አንዳች ሕመም እንደያዛቸው ጠቋሚ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም መተኛት ያልቻሉት በጤና እክል መሆን ወይም አለመሆኑ በግልጽ መለየት አለበት።
ልጆች እንዲተኙ ከማሠልጠን ጋር በተያያዘ የሚነሳው የልጆቹ ባህሪ ነው።
ቤተሰብ ልጆቹን ሁሌም ሲተኙ ድጋፍ የሚሰጥ ከሆነ በራሳቸው መተኛት ላይማሩ ይችላሉ።
ልጆቻቸው እንዳያለቅሱ ለመቆጣጠር ከሚሞክሩ ወላጆች የተወሰኑት ያሰቡትን ውጤት ሳያገኙ ሲቀሩ ፀፀት ይሰማቸዋል።
ልጆቻቸውን ካሠለጠኑ እናቶች መካከል ለድብታ የተጋለጡ ይገኙበታል።
የልጆች እንቅልፍ ሁኔታ የቤተሰቦች ጤና ላይ ተጽዕኖ ሲያሳድርም ታይቷል። የወላጆች አእምሯዊ ሁኔታም ለልጆች እንቅልፍ ማጣት ምክንያት ሲሆን ታይቷል።
የእናቶችና ሕጻናት እንቅልፍ ቤተ ሙከራ የፈጠሩት ቤል እና ጄምስ ማኬና እንደሚሉት፣ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር ሲተኙ የተሻለ እንቅልፍ እንደሚያገኙ ይናገራሉ።
ልጆች ለእንቅልፍ አንዳች መንገድን እንዲከተሉ ማድረግ ውጤታማ ሆኖ ያገኙበት ሁኔታም አለ። ለምሳሌ 405 ሕጻናትን ያሳተፈውን ጥናት እንመልከት።
ሕጻናቱን ከእንቅልፍ በፊት አጥቦ፣ ሎሽን ቀብቶ፣ ዝግ ባለ ሁኔታ ንባብ መስማትን በማስለመድ፣ ይህንንም በየቀኑ በመደጋገም የተሻለ ውጤት ያገኙ ወላጆች አሉ።
ከሰባት ወራት እስከ 36 ወራት ያሉ ሕጻናት በተሳተፉበት በዚህ ጥናት በድግምግሞሽ አንዳች መንገድ እንዲከተሉ ያልተደረጉት ሕጻናት ያነሰ እንቅልፍ ነው ያገኙት።

በተለያዩ አገራት በተሠሩ ጥናቶች እናቶች የሚያማክራቸው ሰው ሲያገኙ የተሻለ ስሜት እንደተሰማቸው ጠቁመዋል።
ብዙ ዘመነኛ ቤተሰቦች ውስጥ እናትም አባትም ሥራ ስላላቸው በቂ ጊዜ አያገኙም። ማታ ለመተኛት ሲሉ ልጆቻቸው እንዳይነቁ የተለያዩ መንገዶች ለመጠቀም የሚገደዱትም ለዚሁ ነው።
ልጆችን እንቅልፍ ማሠልጠን ውጤት ያሳያቸው ቢኖሩም፣ ልጆቻቸው በራሳቸው ጊዜ እንቅልፍን የተለማመዱላቸውም አሉ።
ከ4,000 በላይ ልጆችን ያሳተፈ ጥናት እንደሚያሳየው፣ 71% የሚሆኑ በየጊዜው ይነቁ የነበሩ የአምስት ወር ሕጻንት 20 ወር ሲሆናቸው ተሻሽለዋል። 89% የሚሆኑት ደግሞ 4.5 ዓመት ገደማ ሲሆናቸው ለውጥ አሳይተዋል።
አጥኚዎች እንደሚሉት፣ ወላጆች ሥልጠናውን መስጠት አስፈላጊ ነው ብለው ካመኑ ብቻ ነው ማከናወን ያለባቸው።
ችግሩ ባለበት ሁኔታ ብቻ የተሻለ ነው ተብሎ የታመነውን መንገድ ወላጆች እንዲከተሉም አጥኚዎች ይመክራሉ።












