አይታከምም የተባለውን የካንሰር አይነት ያከመው አዲሱ መድሃኒት

አሊሳ

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኘው አሊሳ እንካሁን ድረስ ህክምና ያልተገኘለትን የደም ካንሰር አይነት ከሰውነቷ ውስጥ አብዮተኛ በተባለለት አንድ መድሃኒት ማከም ተቻለ።

ከዚህ ቀደም የአሊሳን ሕመም ለማከም የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ ቢቀሩም ይህ አዲሱ መድሃኒት ግን አንድ ግዜ ከተሰጣት በኋላ ውጤት ማየት መቻሉ በህክምናው አለም አስደናቂ ግኝት ተብሎለታል።

የግሬት ኦርመንድ ስትሪት ሆስፒታል ሃኪሞች 'ቤዝ ኤዲቲንግ' የተሰኘ አዲስ ቴክኒክን በመጠቀም በታካሚዋ ውስጥ የሚቆይ ህይወት ያለው መድሃኒት ለመገንባት የባዮሎጂካል ምህንድስና ሂደትን መጠቀማቸውም ታውቋል።

አሊሳ ህክምናውን ካገኘች ከስድስት ወራት በኋላ ካንሰሩ በምርመራ የማይገኝበት ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን መልሶ የሚያገረሽ ከሆነ በሚል ግን ሐኪሞች አሁንም ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ።

የ13 ዓመቷ አሊሳ ባለፈው አመት ግንቦት ወር ነበር በቲ-ሴል አኪዩት ሊምፎብላስቲክ ሉኪሚያ በተሰኘ ደም ካንሰር አይነት የተጠቃችው።

ይህ የካንሰር አይነት አጅግ የከፋ ሲሆን በኪሞቴራፒ ብሎም በአጥንት መቅኒ ንቅለ ተከላ ከሰውነቷ ውስጥ ማጥፋት ሳይቻል ቀርቶ ነበር።

አሊሳ አዲሱ መድሃኒት ለሙከራ ባይሰጣት ኖሮ ሃኪሞች ህመም እንዳይሰማት ከማድረግ በዘለለ የሚሰጧት የህክምና አማራጭ አልነበራቸውም።

"በመጨረሻ ህይወቴ ያልፍ ነበር" ስትል ታዳጊዋ ተናግራለች። ወላጅ እናቷ በበኩሏ ባለፈው አመት በዚህ ጊዜ የገናን በአል በስጋት ማሳፏን ተናግራለች።

“ይህ ገና ከእሷ ጋር የምናሳልፈው የመጨረሻው በአል እንደሆነ እያሰብኩ ነበር’’ ስትልም ተናግራለች። ነገር ግን ባለፈው አመት በጥር ወር የልጇን 13ኛ አመት ማክበሯን ተናግራለች።

የግሬት ኦርመንድ ስትሪት ሆስፒታል ባልደረቦች የተጠቀሙት ይህ አዲስ የህክምና ዘዴ በጥናት ከተለየ 6 ዓመቱ ነው።

ቲ-ሴል የተሰኙትን የነጭ የደም ሴሎች ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ እንዲባዙ ያደረገውን ይህንን የህመም አይነት የዘረመል ማሻሻል በማድረግ ለማከም ሃሳቡ ለአሊሳ እናት ሲቀርብ ‘’ይህንን ማድረግ ትችላላችሁ?’’ ስትል ጠይቃለች። አሊሳ ይህንን የሙከራ ህክምና ለመጀመሪያ ግዜ ለመውሰድ ውሳኔዋን ሰጥታለች።

ፕሮፌሰር ዋሴም ቃሲም የተሰኙት የሆስፒታሉ ባልደረባ እንዳሉት ይህ የዘረመልን ቅርጽ በመቀያየር የሚሰጥ ሕክምና ‘’በፍጥነት የሚለዋወጥ ብሎም ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት’’ ነው።

ከህክምናው በኋላ ለወራት በሽታ የመከላከል አቅሟ በመቀነሱ ወንድሟን ማየት ሳትችል የቆየችው ታዳጊ ‘’ትንንሿን ነገር እንኳን ማመስገን ተምሬአለሁ። አሁን እዚህ ስላለሁ በጣም ደስተኛ ነኝ’’ ስትል አሊሳ ተናግራለች።