ሞሮኮ ለዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ በመድረስ ታሪክ ሰራች

የሞሮኮ ተጨዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሞሮኮ ፖርቹጋልን በመርታት ለዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰች የመጀመሪያዊት አፍሪካዊት ጋር በመሆን ታሪክ ሰራች።

ሰሜናዊ አፍሪካዊቷ ሃገር ሞሮኮ ትናንት ታህሳስ 1፣ 2015 ዓ.ም ፖርቹጋልን በኳታር የዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ 1ለ0ም በመርታት ነው ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈችው።

በዚህም ጨዋታ ከፍተኛ ስፍራ ተሰጥቷት የነበረውን ፖርቹጋልን እንዲሁም መሪ ተጨዋቿን ክርስቲያኖ ሮናልዶን ግስጋሴ ገትታለች።

የሞሮኮው አጥቂ ዩሴፍ ኤን ኔሲሪ በመጀመሪያው አጋማሽ የማሸነፊያውን ጎል በማስቆጠር የአል ቱማማ ስታዲየምን ታዳሚዎች እንዲሁም የአረቡን አለምና አፍሪካውያንን አስፈንጥዟል።

የአትላስ አናብስቱ ደጋፊዎች ስታዲየሙን ሞልተውት የነበረ ሲሆን በዓለም አቀፉ የስፖርት መድረክ ሞሮኮን ከፍ ያደረጋትንም ድል በከፍተኛ ደስታ ገልጸውታል።

በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ጨዋታዎች 196 ጊዜ በመጫወት ክብረ ወሰኑን የተቆጣጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ50ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ቢገባም ጎል ሊቀናው አልቻለም። አገሩንም ወደ ግማሽ ፍጻሜ ሊያሳልፋት አልቻለም።

 በግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ፈረንሳይን የምትፋለመው ሞሮኮ ከእረፍት በፊት ኤን ኔሲሪ፣ ያህያ አቲያት አላህ ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ጎል አስቆጥሯል።

የፖርቹጋሉ አጥቂ ብሩኖ ፈርናዴዝ ከደቂቃዎች በኋላ አስደናቂ ጎል ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም የጎሉ ብረት መልሶበት አገሩን እኩል የማድረግ እድሉ ለጥቂት ከሽፏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ሞሮኮ ተጨዋቾች ቢጎዱባትም እንዲሁም እንዲሁም አጥቂዋ ዋሊድ ቼዲራ በስምንት ደቂቃ ተጨማሪ ጊዜ ውስጥ ሁለተኛውን ቢጫ ካርድ በማየቱ ከጨዋታው ቢሰናበትም ፖርቹጋል ጎል ማስቆጠር አልቻለችም።

ሶስት የአፍሪካ ሃገራት ከዚህ ቀደም በነበሩ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ሩብ ፍጻሜ ደረጃ ላይ ቢደርሱም አንዳቸውም ቢሆን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፍ አልቻሉም ነበር።

ድንቅ ጨዋታን ላሳዩት የሞሮኮ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ኤን ኔሲሪ በቴስታ ያስቆጠራት ግብ ሃገሪቱን በታሪክ መዝገብ እንድትሰፍር በማድረግ ደስታቸውን ሌላ ደረጃ ላይ አድርሶታል።