ዓለም በጉጉት እየጠበቀው ያለው ወሳኙ የእንግሊዝ እና ፈረንሳይ ጨዋታ

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ውድድር በጉጉት ከሚጠበቁ ጨዋታዎች መካከል ቀዳሚ ሊሆን የሚችለው የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ወሳኝ ፍልሚያ ዛሬ ቅዳሜ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በአል ባይት ስታዲየም ይደረጋል።
ከዚህ ቀደም ብሎ 12 ሰዓት ላይ በአል ቱማማ ስታዲየም አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ከፖርቱጋል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ የእንግሊዝን እና የፈረንሳይን ያህል ባይሆንም የሚጠበቅ ነው።
ምንም እንኳን በዚህ ጨዋታ ፖርቱጋል በአሸናፊነት ወደ ቀጣዩ ዙር ታልፋለች የሚለው ግምት የበርካቶች ቢሆንም፣ ብዙ ያልተጠበቁ ክስተቶችን እያስተናገደ ባለው የዓለም ዋንጫ ምን ሊከሰት እንደሚችል በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
የዛሬ ምሽቱ የፈረንሳይና የእንግሊዝ ተጠባቂ ጨዋታ ለእንግሊዙ አሰልጣኝ ጋሪዝ ሳውዝጌት እስካሁን ካደረጋቸው ጨዋታዎች ሁሉ ከባዱ እና የሚፈተንበት ይሆናል እየተባለ ነው።
የቀደመው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ እና በዚህ ውድድርም ብቃታቸውን ካሳዩ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነውን የፈረንሳይን ቡድን ለማሸነፍ ከባድ ኃላፊነት ከፊቱ ተደቅኗል።
በፈረንሳይና በእንግሊዝ መካከል የሚደረገው ጨዋታ በመላው ዓለም የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በጉጉት ከመጠበቁ ባሻገር ታሪካዊም ነው።
የሁለቱ አገራት ብሔራዊ ቡድኖች በተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን ከዓለም ዋንጫ ውጪ በጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ሲገኛኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በዓለም ዋንጫም ከአውሮፓውያኑ 1982 ወዲህ በጥሎ ማለፍ ውድደር የሚገናኙት አሁን ነው።
በዚህ ውድድር እስካሁን እንግሊዝ 12 ግቦችን ስታስቆጥር ፈረንሳይ ደግሞ 9 አስመዝግባለች።
የዛሬው ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንደቀደሙት የጥሎ ማለፍ ፉክክሮች ሁሉ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት መለያ ይሸጋገራል ወይስ በመደበኛው ሰዓት ይጠናቀቃል? ሁሉም በጉጉት የሚጠበቀው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለቱ አሠልጣኞችና ቡድናቸው ይህንን ወሳኝ ደግሞም ከባድ ጨዋታ በድል ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ይናገራሉ።
የእግሊዙ አሠልጣኝ ሳውዝጌት ቡድኑ በቀድሞው የዓለም ዋንጫ እና የአውሮፓ ዋንጫ ወቅት የገጠማቸውን ሽንፈት እንደ ትምህርት በመያዝ በዚህ ጨዋታ አሸናፊ ለመሆን መዘጋጀቱን ገልጿል።
“ከልምድ አኳያ እነዚያ ታላላቅ ግጥሚያዎች ለቡድናችን ጠቃሚ የመነሻ ነጥቦች ናቸው” ብሏል ሳውዝጌት።
“ከፈረንሳይ ጋር ለምናደርገው ግጥሚያ ከሁሉ የበለጠ አቅማችንን እንድንጠቀም በማድረግ እንድንዘጋጅ ያደረጉ የቀደሙ ሽንፈቶች አሉን። በዚህም ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ተዘጋጅተናል።”
በፈረንሳይ በኩልም ይህንን ወሳኝ ጨዋታ ለማሸነፍ ጉጉቱ ከፍተኛ ነው።
የእንግሊዝ ቡድን ደካማ ጎን ምን እንደሆነ የተጠየቀው ዴሾ፣ “ሁሉም ቡድን ጠንካራ ጎኖች እንጂ የበዛ ድክመት አይኖራቸውም። ነገር ግን ብዙ ጠንካራ ያልሆኑባቸው ነጥቦች ይኖራሉ።
በመጨረሻ ግን መለየት ያለብን አንድን ቡድን ልናጠቃው የምንችልበትን ጎኑን ነው” በማለት የእንግሊዝ ቡድን በመልሶ ማጥቃት ግብ በማስቆጠር በኩል ጠንካራ መሆናቸውን መስክሯል።
ፈረንሳይ አንድ አንድ ቢጫ ካርድ ያለባቸውን ተከላካዩን ዩሌስ ኩንዴን እና የመሃል መስመር ተጫወቹን አውሬሊን ሹሜኒን የምታሰልፍ ይሆንል። በዚህ ጨዋታ ድል ከቀናትና ተጫዋቾቹ ተጨማሪ ቢጫ ካርድ ካዩ በቀታይ ጨዋታ የቡድኗ ጥንካሬ ሊሳሳ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ነገር ግን አሳልጣኝ ዲዲዬ ዱሾ እንደሚለው ቢጫ ካርድን በመፍራት ተጫዋቾቻቸው ለቡድናቸው አሸናፊነት ሊያደርጉት ከሚችሉት አስተዋጽኦ እንዲቆጠቡ አይፈልግም።
“በሙሉ አቅማቸው በመጫወት ያቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ” በማለት የተጫዋቾቹ ዋነኛ ግብ እንግሊዝን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፍ መሆኑን አመለክቷል።
ከዚህ ውድድር በኋላ የፈረንሳይን ብሔራዊ ቡድን ለማሠልጣን የገባው ኮንትራት የሚያበቃው ዴሾ፣ ቡድኑ “በጣም የተረጋጋ” መሆኑን ገልጿል።
“ዋናው ትኩረታችንን የምናደርገው በእያንዳንዱ ግጥሚያ ላይ ነው። ምክንያቱም ስለቀጣዩ በማሰብ እራስን ጭንቀትና ጫና ውስጥ መክተት ምንም ውጤት የለመውም” በማለት የቡድኑ ሙሉ ትኩረት በዛሬው ጨዋታ ላይ ነው ብሏል።
ትናንት አርብ ምሽት ለዋንጫው ስትጠበቅ የነበረችው ብራዚል በመደበኛው ሰዓት ከክሮሺያ ጋር አንድ አቻ በመለያየታቸው በመለያ ምቶች 4 ለ 2 ተሸንፋ ከውድድሩ ተሰናብታለች።
እንዲሁም ከባድ ከተባሉት ጨዋታዎች መካከል የሚመደበው የአርጀንቲና እና የኔዘርላንድስ ግጥሚያ ከፍተኛ ፉክክር ታይቶበት መደበኛው ሰዓት ሁለት አቻ በሆነ ውጤት በመጠናቀቁ፣ በመለያ ምቶች አርጀንቲና 4 ለ 3 አሸንፋለች።
በዚህም በቀጣይ የግማሽ ፍጻሜ ክሮሺያ እና አርጀንቲና የሚገጥሙ ሲሆን፣ ዛሬ የሚደረጉት ጨዋታዎች አሸናፊዎችም ለዋንጫ ለመቅረብ ከቀናት በኋላ ይፋለማሉ።












