ስምንት ቡድኖች ከዋክብቶቻቸውን አሰልፈው የሚፋለሙባቸው ታላላቆቹ ጨዋታዎች

በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ቀሪዎቹ ስምንት ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለመድረስ የሚያደርጉትን ትንቅንቅ ዛሬ ይጀምራሉ።
ለዋንጫ ጨዋታው ለመቅረብ ከሚፋለሙት የመጨረሻ አራት ቡድኖች ውስጥ ለመካተት በሚደረገው ጨዋታ ክሮሺያ ከብራዚል ጋር ቀድመው ይጫወታሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ሲል የ2018 የሩሲያ ዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረችው ክሮሺያ ለዋንጫው ከተገመተችው ብራዚል ፈተና ይጠብቃታል።
ምሽት አራት ሰዓት ሲል ደግሞ ድንቅ ጨዋታ ይታይበታል የተባለው ግጥሚያ ይከናወናል። ይህ ጨዋታ የአውሮፓውያኑን 1978 የዋንጫ ተፋላሚዎች ኔዘርላንደስ እና አርጀንቲናን ያገናኛል።
ክሮሺያ ብራዚልን መቋቋም ይቻላታል?
ጃፓንን በመለያ ምት በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው የደረሱት ክሮሺያዎች የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ግስጋሴያቸው ዛሬ በብራዚል ሊገታ እንደሚችል የበርካቶች ግምት ነው።
ይሁን እንጂ በሉካ ሞድሪች አጋፋሪነት የሚመሩት ክሮሺያዎች ከቤልጂየም ጋር የነበራቸውን አይበገሬነት እንዲሁም ከካናዳ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ያሳዩትን ድንቅ አቋም ዛሬም ከደገሙት ብራዚልን ሊገዳደሩ ይችላሉ።
ለዋንጫው ትልቅ ግምት የተሰጣት ብራዚል በበኩሏ እስካሁን ይህ ነው የሚባል ብርቱ ተቀናቃኝ ሳይገጥማት እዚህ ደርሳለች።
ደቡብ ኮሪያን 4 ለ 1 በሆነ ውጤት ድል አድርገው ወደ ሩብ ፍጻሜ ስለደረሱት ቢጫ ለባሾቹ የክሮሺያው አሰልጣኝ ድላትኮ ዳሊች አስተያየት ሲሰጡ፤ “እስካሁን ባየሁት፤ ያላቸውን የተጫዋቾች ጥራት እና ክህሎት ስለመለከት እውነትም አስፈሪ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ወጣት የክሮሺያ ቡድን አባላት ግን እንዲሁ በቀላሉ ለብራዚል እንደማይንበረከኩ እየገለጹ ነው። የቀኝ ተመላላሹ ጆሲፕ ጁራኖቪች፤ “እንደ ሉካ ሞድሪች ያሉ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ እየተሯሯጡ የተቻላቸውን ሲያደርጉ ለእንደኛ አይነት ወጣት ተጫዋቾች ተጨማሪ ኃይል ነው” በማለት ብራዚላውያኑን ለማሸነፍ እንደሚፋሉ ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሜሲ ወይስ ብርትካናማዎቹ?
ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሊዮኔል ሜሲዋ አርጀንቲና ከኔዘርላንድስ የምታደርገው ጨዋታ በመላው ዓለም በጉጉት ይጠበቃል።
ለሜሲ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ይህ የዓለም ዋንጫ የመጨረሻው ለሆነው ለምን ግዜም ምርጡ ሜሲ፤ ድንቅ የእግር ኳስ ሕይወቱ ሙሉ የሚሆነው የዓለም ዋንጫን ሲያነሳ ይሆናል።
የ71 ዓመቱ የኔዘርላንድስ አሰልጣኝ ቫን ሃል ሦስት ጊዜ የዋንጫ ተፋላሚ ለነበሩት ሆላንዶች በመጨረሻ ስኬት መስጠትን ያልማሉ።
አሰልጣኙ ምናልባት በዛሬው ጨዋታ ሜሲን ማስቆም እና በመልሶ ማጥቃት ጎል ለማስቆጠር አልመው ሊገቡ ይችላሉ።
ነገ ቅዳሜ ደግሞ ስፔንን በመርታት ሩብ ፍጻሜውን የተቀለቀለችው አፍሪካዊቷ ሞሮኮ ከክርስቲያኖ ሮናልዶው ፖርቹጋል ጋር ትገጥማለች።
ምሽት 4 ሰዓት ላይ ደግሞ በድንቅ አቋም ተጋጣሚዎቻቸውን እየረቱ ያሉት ፍረንሳያውያን ከእንግሊዝ ይጫወታሉ።
ሁሉም ቡድኖች ያላቸውን አቅም እና ክህሎት ሁሉ አሟጠው በታላቁ ዓለም እግር ኳስ መድረክ ላይ ለመዝለቅ የሚያደርጉት ፍልሚያ በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
እነማን ወደ ቀጣዩ ዙር ያልፉ ይሆን? ምንስ ያለተጠበቀ ነገር ይከሰት ይሆን?












