አንዱ የሰውነት አካል ከሌላው አንጻር በፍጥነት እያረጀ መሆኑን ማወቅ ይቻላል?

የደም ምርመራ የሚያደርግ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በተለምዶ ዕድሜ አንድ ሰው በሕይወት በኖረባቸው ዓመታት ብዛት የሚገለጽ ነው።

ሳይንቲስቶች ደግሞ የደም ምርመራ በማካሄድ የአንድን ሰው የውስጥ አካላት የእርጅና መጠን ለማወቅ እንደሚችሉ ያምናሉ።

ይህ ደግሞ የትኞቹ የአካል ክፍሎች ሥራ የማቆም አደጋ እንዳንዣበባቸው ለመተንበይ ሊረዳ ይችላል።

የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ያዋቀረው ቡድን ልብን፣ አንጎልን እና ሳንባን ጨምሮ 11 ዋና ዋና የሰውነት ክፍሎችን መከታተል እንደሚችል ተናግሯል።

የስታንፎርድ ቡድን በሺህዎች በሚቆጠሩ ጎልማሶች ጥናቱን ሞክሮታል። የጥናቱ ተሳታፊዎች በአብዛኛው መካከለኛ ወይም ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ናቸው።

ከ50 ዓመት በላይ ከሆናቸው አምስት ጤናማ ጎልማሶች ቢያንስ አንዱ በፍጥነት እያረጀ ያለ አንድ የአካል ሊኖራቸው እንደሚችል ውጤቶቹ ይጠቁማሉ።

ከ100 ሰዎች ደግሞ አንድ ወይም ሁለቱ ከዕድሜያቸው በላይ ያረጀ በርካታ የአካል ክፍሎች ሊኖራቸው ይችላል።

የምርመራው ሃሳብ አስፈሪ ቢመስልም በቶሎ እርምጃ ለመውሰድ እና እንደዚህ ያሉ ተጋላጭ የአካል ክፍሎችን የወደፊት ሁኔታ ለመለወጥ ዕድሉ ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።

የትኛዎቹ የአካል ክፍሎች በፍጥነት እደከሙ እንዳሉ ማወቁ ምን ዓይነት የጤና ችግሮች እያንዣበቡ እንደሆነ ለማወቅ ይረዳል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ኔቸር በተባለው መጽሔት ላይ አስፍረዋል።

የአካል ክፍሎች የዕድሜ ልዩነት

ለምሳሌ ልብ “ከዕድሜው አንጻር እያረጀ ከሆነ” ለልብ ድካም የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል። በፍጥነት ያረጀ አንጎል ደግሞ ለመርሳት በሽታ የተጋለጠ ሊሆን ይችላል።

በጥናቱ መሠረት አንድ ግለሰብ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የአካል ክፍሎቹ በፍጥነት እያረጁ ከሆነ በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ ለአንዳንድ በሽታዎች እና ለሞት የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል።

የመረመሯቸው የሰውነት ክፍሎች የሚከተሉትን ያካትታሉ:

• አንጎል

• ልብ

• ጉበት

• ሳንባ

• አንጀት

• ኩላሊት

• ስብ

• የደም ቧንቧዎች (ደም ቅዳ እና መልስ ቧንቧዎች)

• የበሽታ መከላከያ ቲሹ

• ጡንቻ

• ጣፍያ

ይህ የደም ምርመራ የየትኞቹ የአካል ክፍሎች በፍጥነት እያረጁ እንደሆነ ፍንጭ ለመስጠት በሺህዎች የሚቆጠሩ ፕሮቲኖችን በተለያየ ደረጃ ይመለከታል።

የተገኙት ፕሮቲኖች ንድፍ ለተወሰኑ የአካል ክፍሎች የተዘጋጀ ይመስላል።

ተመራማሪዎች ብዙ የደም ምርመራ ውጤቶችን እና የታካሚ መረጃዎችን በመጠቀም ትንበያውን ይሠራል። ስልተ ቀመርን ተጠቅሞ ትንበያውን የሚሰጥ ማሽን አዘጋጅተዋል።

ከመርማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ቶኒ ዋይስ-ኮራይ “እነዚህን የአካል ክፍሎች ያላቸውን አማካኝ ዕድሜ ለማወቅ ከባድ በሽታ ከሌላቸው በርካታ ሰዎች ናሙና ወስደናል። 50 ዓመት እና ከዚያ በላይ ከሆናቸው ሰዎች ውስጥ 18 በመቶዎቹ ቢያንስ አንዱ የሰውነት አካላቸው በፍጥነት እያረጀ መሆኑን አይተናል” ብለዋል።

"እነዚህ ግለሰቦች በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ውስጥ በዚያ አካል ለበሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን ደርሰንበታል።”

የተለያየ የአካል ክፍሎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናቱ ጥቅም ላይ ሊውል እና ሊሸጥ የሚችል ከሆነ በሚል ለምርምሩ የባለቤትነት መብት እንዲሰጠው አቅርቧል።

ሆኖም የሰውነት አካል ዕድሜን በማወቅ የጤና ሁኔታን መተንበይ ምን ያህል ጥሩ እንደሆነ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናቶች ያስፈልጋሉ።

አንዳንድ የዶ/ር ዋይስ-ኮራይ ቀደምት ጥናቶች ባዮሎጂካል የእርጅና ሂደት ወጥ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ። ነገር ግን የሰዎች የሰውነት አካል ማርጀት በ30ዎቹ አጋማሽ፣ በ60ዎቹ መጀመሪያ እና በ70ዎቹ መገባደጃ ላይ በጣም እንደሚፈጥን ያሳያሉ።

በለንደን ኩዊን ሜሪ ዩኒቨርሲቲ ከዕድሜ ጋር የተያያዙ የጤና እና በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ጀምስ ቲሞንስ የደም ናሙናን በመጠቀም ባዮሎጂካል የዕድሜ ለውጥ ምልክቶችን ሲያጠኑ ቆይተዋል። የእሳቸው ጥናት የሚያተኩረው ከፕሮቲኖች ይልቅ ሊታወቁ በሚችሉ የጂን ለውጦች ላይ ነው።

በዶ/ር ዊስ-ኮራይ ግኝቶች አስደናቂ እንደሆኑ ገልጸው፤ በርካታ ሰዎች በተለይም ከተለያየ ጎሳ የመጡ ወጣቶች ተሳትፈውበት ማረጋገጫ ያስፈልገዋል ብለዋል።

"ይህ እርጅና ነው ወይስ ከለጋ ዕድሜ ጋር የተያያዙ በሽታዎችን የሚለይ አዲስ መንገድ ነው? አጥኚዎቹ ቀዳሚውን ይደግፋሉ። የኋለኛውም ሊዘነጋ የሚገባ አይመስለኝም" ብለዋል።

ዶ/ር ዋይስ-ኮራይ “ይህን ግኝት በ50 ሺህ ወይም 100 ሺህ ግለሰቦች ላይ ማባዛት ከቻልን፤ ጤነኛ በሚመስሉ ሰዎች ላይ ያሉትን የአካል ክፍሎች ጤና በመከታተል በሰው አካል ውስጥ የተፋጠነ የእርጅና ሂደት ውስጥ ያሉ የሰውነት አካላትን ማግኘት እንችላለን ማለት ነው። በዚህም ሰዎች ከመታመማቸው በፊት ማከም እንችል ይሆናል” ብለዋል።

በግላስጎው ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ፖል ሼልስ በበኩላቸው ስለማንኛውም ሰው ጤንነት ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት፣ የተወሰኑ አካላትን ብቻ ሳይሆን መላውን ሰውነት መመልከት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የኤጅ ዩኬ የበጎ አድራጎት ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ካሮሊን አብርሀምስ ደግሞ በፍጥነት እያረጁ ያሉ የሰውነት ክፍሎችን ሳይንስ ቀደም ብሎ በማወቅ በሽታዎችን መለየቱ ጥሩ ቢሆንም ሰዎች ይህን በማወቃቸው ምን ሊሰማቸው እንደሚችል ግምት ውስጥ ሊገባ ያስፈልገዋል ብለዋል።

ጥናቱ እውን ከሆነ፣ ሰዎች ከውጤቶቹ መታወቅ ጎን ለጎን ስሜታዊ እና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል። ኤን ኤች ኤስም ዝግጁ መሆን እንዳለበት እና ይህንን ማቅረብ የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት እንዳለበት ተናግረዋል።