የሲንጋፖር ታዳጊዎች በሒሳብ ትምህርት ለምን ጎበዝ ሆኑ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሲንጋፖር በተማሪዎች መካከል በተደረገው በዓለም አቀፉ የ2022 የፒሳ ፈተና በሂሳብ፣ በንባብ እና በሳይንስ ቀዳሚ ለመሆን በቅታለች።
አገሪቱ በሂሳብ ትምህርት በተደጋጋሚ ውጤታማ ሆናለች። ለስኬቱ የተሞገሰው ደግሞ ትምህርቱ የሚሰጥበት ልዩ መንገድ ነው።
የሲንጋፖር ሒሳብ ምንድን ነው? ለምንስ በጣም ስኬታማ ሆነ?
ፒሳ (ዓለም አቀፍ የተማሪ ምዘና ፕሮግራም) በኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት (OECD) የተዋወቀ ሲሆን ለ15 ዓመት ታዳጊዎች የትምህርት ደረጃዎችን የሚሰጥ ስርዓት ነው።
በፒሳ 2022 ከሦስቱ ዋና ዋና መመዘኛዎች አንዱ የሂሳብ ትምህርት ነው። የሲንጋፖር የ15 ዓመት ታዳጊዎች 575 ነጥብ አስመዝግበዋል። የ81 ተሳታፊ አገራት በአማካይ ውጤት 472 ነጥብ ነው።
የሲንጋፖር ባለስልጣናት ሰዎች አመክንዮአዊ እና ትንተናዊ በሆነ መንገድ እንዲያስቡ በማድርግ ረገድ የሒሳብ ትምህርት ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለው ያምናሉ።
በዚህ ምክንያት የሲንጋፖር ታዳጊዎች ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ወሳኝ የሒሳብ ሂደቶችን ማመዛዘን እንዴት ማዳበር እንደሚችሉ ይማራሉ።
የአገሪቷ ሒሳብ ለማስተማር የምትጠቀምበት አቀራረብ በተለምዶ የሲንጋፖር ሒሳብ በመባል ይታወቃል።
ይህ ዘዴ ለሕዝብ ትምህርት ቤቶች ተብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው በ1980ዎቹ በሲንጋፖር የትምህርት ሚኒስቴር በኩል ነው።
ዘዴው ከማስታወስ ይልቅ፣ ትኩረቱን ጉዳዩን በጥልቀት ወደ መረዳት ይሸጋግራል። ከቅርብ አስርተ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተለያዩ አገሮች በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሲንጋፖር ሂሳብ እንዴት ነው የሚሠራው?
የሲንጋፖር የሂሳብ ዘዴ ሁለት አንኳር ሃሳቦች ይከተላል። የኮንክሪት፣ ስዕላዊ፣ አብስትራክት አቀራረቡ (ሲፒኤ) እና የመብቃት እሳቤ ይባላሉ።
ሲፒኤ ለሲንጋፖር ሒሳብ አዲስ አይደለም። በአሜሪካው የሥነ ልቦና ባለሙያ ጄሮም ብሩነር በ1960ዎቹ የተዋወቀ ነው።
ህጻናት ወይም አዋቂዎች ሒሳብን ይከብዳቸዋል በሚለው ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ነው።
ስለዚህ ሲፒኤ ረቂቅ ፅንሰ-ሀሳቦችን በተጨባጭ መንገድ ያስተዋውቃል። ቀጥሎም ወደ ውስብስብ ርዕሰ ጉዳዮች ያመራል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ኤሪያል ሊንዶርፍ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ሲንጋፖር ሒሳብ ዘዴ ልጆች ሲማሩ ሁል ጊዜ ተጨባጭ ነገር ያከናውናሉ" ብለዋል።
"መደመርን ሲማሩ ኪዩቦች ሊኖራቸው ይችላል። እነሱንም አንድ ላይ ያስቀምጧቸዋል። ስዕላዊ የሆነ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። የአበባ ምስሎች ወይም የሰዎች ወይም የእንቁራሪቶች ወይም ከቁጥሮች ጋር ለመገናኘት ቀላል የሆነ ነገር ሊኖራቸው ይችላል።"
ስለዚህ ሲፒኤ ከቁጥሮች ይልቅ በእነዚህ የተለያዩ ተወካይ በሆኑ ቁሶች አማካኝነት ሒሳብን የመረዳት ዕድልን ይሰጣል።
ልጆቹ ስለ የሒሳብ ስሌት ተጨባጭ እና ስዕላዊ የሆነ ጠንካራ ግንዛቤ እንዳላቸው ካሳዩ በኋላ ወደ ሃሳባዊ ትምህርት ያልፋሉ።
"የሲንጋፖር የሒሳብ ዘዴ በማስታወስ ላይ የተንጠለጠለ አይደለም" ብለዋል ዶ/ር ሊንዶርፍ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"የመብቃት" ጽንሰ-ሀሳብ
ሌላው የሲንጋፖር የሒሳብ ዘዴ ምሰሶ "ማብቃት" እሳቤ ነው። በዚህ እሳቤ ሁሉም በክፍል ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ወደ ኋላ እንደማይቀሩ በማረጋገጥ አንድ ላይ ወደፊት እንዲራመዱ የሚደረግበት ነው።
ለምሳሌ ያህል ልጆች እንደ መደመር ያሉ አንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮችን ሲማሩ፣ አንዳንዶቹ ከሌሎቹ ፈጥነው ሊረዱት ይችላሉ።
መደመርን የለመዱት ተማሪዎችን ወደ ሌላ ትምህርት ከማዘዋወር ይልቅ፣ ግንዛቤያቸውን የበለጠ ለማሳደግ ከመደመር ጋር የተያያዙ ተጨማሪ ተግባራት ይሰጣቸዋል።
"ይህ ማለት እያንዳንዱ ተማሪ እስኪገባው ቀድመው የተረዱትም መጠበቅ አለባቸው ማለት አይደለም" ብለዋል ዶ/ር ሊንዶርፍ።
"አንዳንድ ልጆች ስለ መደመር ጥሩ ግንዛቤ ካላቸው መምህሩ ስለመቀነስ አያስተምሯቸውም። ይልቁንም የመደመር ጽንሰ-ሐሳብን ትንሽ ጠለቅ አድርገው ይሰጧቸዋል።"
በትልልቅ ቁጥሮች ወይም በተለያዩ ቅርጾች ላይ የሚሠሩ መደመሮች ሊሆኑ ይችላሉ።
ስለዚህ የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ልጆች ከሌሎቹ ተማሪዎች ጋር መደመር ይቀጥላሉ። የሚደምሩት ግን በተለየ መንገድ ይሆናል።
በሲንጋፖር ሒሳብ መሠረት ተማሪዎቹ ሒሳብን እንደ አስፈላጊ እና ቀላል ሆኖላቸው እንዲገነዘቡ ማድረግ ወሳኝ ነው።
"ሃሳቡ ሁሉም ሰው ሒሳብ መጅራት የሚችል መሆኑን ማሳየት ነው። ሁሉም ሰው ያንን ጽንሰ-ሀሳብ በተወሰነ ደረጃ ማወቅ መቻል አለበት" ብለዋል ዶ/ር ሊንዶርፍ።
“አንዳንዶቹ ፈጣን ሊሆኑ ይችላሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ትንሽ ጠለቅ ያለ መረዳት ሊኖራቸው ይችላል… ብዙውን ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ሒሳብን ያውቃሉ ሌሎች ደግሞ አያውቁም ብለን እናስባለን። ይህንን እኔ አላምንበትም። ይህ በሲንጋፖር ሒሳብ ላይ የተመሠረተም አይደለም።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሲንጋፖር ሒሳብ ለሌሎችም ሊሠራ ይችላል?
ዘዴው እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እስራኤል፣ እንግሊዝ እና በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ ቀደም ብሎ ጥቅም ላይ ውሏል።
እንደ ዶ/ር ሊንዶርፍ ከሆነ ግን የሲንጋፖር ሒሳብ ስኬታማ የሆነው ከትምህርት ባህል፣ ካለው አውድ እና ከሲንጋፖር ታሪክ ጋር በቅርበት የተገናኘ በመሆኑ እንደሆነ ያምናሉ።
"ዘዴውን ብቻ በመውሰድ ሌላ አገር መጠቀም የምትችል አይመስለኝም" ብለዋል።
"ሲንጋፖር አስደሳች እና ልዩ ታሪክ አላት። በጣም ትንሽም ናት። ስለትምህርት ለውጥ ሲታሰብ በሲንጋፖር እና እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ወይም አሜሪካ ያሉትን አንድ ላይ መመልከት ተገቢ አይደለም።”
በሲንጋፖር ያሉ አስተማሪዎች ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ጥሩ የሥራ ዕድል እና የተሻለ ድጋፍ አላቸው ብለው ያስባሉ። የሲንጋፖር ተማሪዎች ስለሒሳብ ትምህርት ያላቸው አመለካከትም ለሲንጋፖር ሒሳብ ስኬት ሌላኛው ምክንያት ነው።
"ሰዎች የሒሳብ ትምህርትን መማር ምክንያት እና ጥቅሙ ምን እንደሆነም ያስባሉ" ሲሉ ይጠይቃሉ።












