ዝነኛው ፓስተር ቲቢ ጆሽዋ ምዕመናንን መድፈሩን እና ማሰቃየቱን የቢቢሲ ምርመራ አጋለጠ

ፓስተር ቲቢ ጆሽዋ
የምስሉ መግለጫ, ፓስተር ቲቢ ጆሽዋ

የዓለማችን ትልቅ ቤተ እምነቶች መካከል አንዱ የሆነው ቤተ-ክርስቲያን መሥራች እና መሪ ፓስተር ቲቢ ጆሽዋ ምዕመናን አስገድዶ መድፈሩን እና ማሰቃየቱን የቢቢሲ ምርመራ አጋለጠ።

የሲኖግ ቸርች ኦፍ ኦል ኔሽን የቀድሞ አባላት የሆኑ አምስት እንግሊዛውያን በናይጄሪያዊው ፓስተር ቲቢ ጆሽዋ አስገድዶ መድፈር እና በግዳጅ ጽንስ ማቋረጥን የሚጨምር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።

መስል ጥቃቶቹ ምሥጢራዊ ተብሎ በተለየና በሌጎስ ከተማ በሚገኝ አንድ ግቢ ውስጥ ለ20 ዓመታት ሲፈጸም ቆይቷል።

እአአ 2021 ዓ/ም ላይ ሕይወቱ ያለፈው ፓስተር ቲቢ ጆሹዋ ስመ ገናና እና ስኬታማ ሰባኪ የነበረ ሲሆን በመላው ዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተከታዮች ማፍራት ችሎ ነበር።

ቢቢሲ ለሁለት ዓመታት ባደረገው የምርመራ ዘገባ ሰዎችን በሰንሰለት ማሰር እና መግረፍን የሚጨምር አካላዊ ጥቃት መፈጸሙን ከበርካታ የዓይን ምስክሮች ሰምቷል።

በርካታ ሴቶች ሌጎስ ከተማ በሚገኘው ግቢ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በተደጋጋሚ ሲደፈሩ ቆይተዋል።

በጆሹዋ አስገድዶ መድፈር ምክንያት የተረገዘ ጽንስ በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ በግዳጅ እንደሚወጣ ተጎጂዎች ገልጸዋል።

በተጨማሪም ጆሽዋ “ተዓምራዊ የሆኑ ፈውሶችን” ለሚሊዮኖች በሚሰራጭ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በማታለል እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል።

በጆሹዋ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሴቶች መካከል ሪያ የተባለች እንግሊዛዊት ሴት ትገኝበታለች። ሪያ ለጆሽዋ ቤተ-ክርስቲያን ስትመለመል ገና የ21 ዓመት ወጣት ነበረች።

ሪያ እአአ 2002 ላይ ቤተ-ክርስቲያኑን ከተቀላቀለች በኋላ በኮንክሪት ግንብ በታጠረው የሌጎሱ ጊቢ ውስጥ ከጆሹዋ “ደቀ መዛሙርት” መካከል አንዷ ሆና ለ12 ዓመታት ኖራለች።

“ሁላችንም ገነት እንደገባ ነበር የምናስበው፤ የነበርነው ግን ሲኦል ውስጥ ነበር። እጅግ አስከፊ ነገሮች ተከስተዋለ” በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሪያ በቲቢ ጆሾዋ ጾታዊ ጥቃት እንደተፈጸመባት እና ለሁለት ዓመታት ለብቻዋ በአንድ ክፍል ውስጥ እንድትቆይ መደረጓን ትገልጻለች።

የሚደርስባት ጥቃት እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ እራሷን ለማጥፋት ብዙ ሙከራ ማድረጓን ሪያ ትናገራለች።

ዘ ሲኖግ ቸርች ኦፍ አል ኔሽንስ የተባለው ቤተ-ክርስቲያን በመላው ዓለም እጅግ በርካታ ያላቸው ተከታዮች ያሉት ሲሆን ኤማኑኤል የተባለው የቤተ-ክርስቲያኑ የቴሉቪዥን ጣቢያ እና ማኅብራዊ ሚዲያዎቹ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች አሉት።

እአአ በ1990ዎቹ እና በ2000ዎቹ መጀመሪያ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከደቡብ ምሥራቅ እሲያ እና ከአፍሪካ በቤተ-ክርስቲያኑ አገልግሎት ላይ ለመሳተፍ እና የቲቢ ጆሹዋን “አስደናቂ ፈውስ” ለመመልከት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ሌጎስ ሲተሙ ቆይተዋል።

ምሥጢራዊ ነው በሚባለው በሌጎሱ ግቢ ውስጥ 150 የሚሆኑ ጎብኚዎች ‘ደቀ መዛሙርት’ ተብለው ከጆሹዋ ጋር አብረው ኖረዋል።

አንዳንዶቹ ታዲያ በግቢው የኖሩት ለዐሥርተ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ነው።

ሪያ
የምስሉ መግለጫ, ሪያ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከ25 በላይ የሆኑ የቀድሞው የጆሽዋ ‘ደቀ መዛሙርት’ ለቢቢሲ ቃላቸውን ሰጥተዋል። ግማሾቹ ከዩኬ፣ ከናይጄሪያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከናሚቢያና ጀመርን ናቸው።

በጆሽዋ ቸርች ውስጥ ስለተፈጸመባቸው ግፍ፣ ጾታዊ ትንኮሳ፣ መደፈር እማኝነታቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።

ብዙዎቹ የጥቃት ሰለባዎች በጆሽዋን ቸርች ማምለክ ሲጀምሩ በዐሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ነበሩ።

አንዳንዶቹ የዩኬ አማኞች ወደ ሌጎስ የአውሮፕላን ወጪያቸውን ተችለው ነው የሄዱት። ይህም የሆነው የጆሽዋ ቸርች እንግሊዝ ካሉ ቤተ-ክርስቲያነት ጋር በመቀናጀት ነው።

ሪያ እና ሎሎች ቃላቸውን የሰጡ የጆሽዋ ‘ደቀ መዛሙርት’ የነበሩ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበራቸውን ቆይታ ከባዕድ አምልኮ ጋር ያቀራርቡታል።

ጄሲካ ከናሚቢያ ናት። በጆሽዋ ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈችው ፍዳና ስቃይ ለአምስት ዓመታት የዘለቀ ነው። ፓስተር ጆሽዋ መጀመርያ አስገድዶ ሲደፍራት ገና 17 ዓመቴ ነበር ትላለች። ከዚያ በተከታታይ አብራው ለመተኛት ተገዳለች።

በዚህም የተነሳ አምስት ጊዜ ጽንስ ለማቋረጥ ተገዳለች።

“እነዚህ ውርጃዎች ሕገ ወጥ የሆኑ ናቸው። መድኃኒቶቹ አደገኛ ናቸው። ምናልባትም ልሞት እችል ነበር” ትላለች።

ሌሎች የጆሽዋ ‘ደቀ መዛሙርት’ የሆኑ ሴቶች ከርሱ ጋር አልተኛም በማለታቸው በተደጋጋሚ በኤሌክትሪክ ሽቦ ይገረፉ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፓስተር ጆሽዋ በፈረንጆቹ 2021 ሰኔ ወር ላይ ሕይወቱ ሲያልፍ በአፍሪካ ታሪክ ታላቁ ተጽእኖ ፈጣሪና ነቢይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ በሚል ስሙ ናኝቶ እንደነበር ይታወሳል። እርሱ የገነባው የእምነት ‘ሥርወ መንግሥት’ ታላላቅ ፖለቲከኞችን፣ ሥመ ጥር ሰዎችን፣ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ያካተተ ነበር።

በ2014 ደግሞ የርሱ እንግዳ መቀበያ አዳራሽ ተንዶ 116 ሰዎች ሕይወታቸው በመጥፋቱ ዜና መሆን ችሎ ነበር።

ቢቢሲ ከኦፕን ዲሞክራሲ ጋር በመተባበር የዚህን ፓስተር ተጠቂዎች ሲያጋልጥ የመጀመርያ ጊዜ ነው።

የርሱ ‘ደቀ መዛሙርት’ ወደ ሚዲያ ወጥተው ለመናገር ሲደፍሩም የመጀመርያ ነው። ከዚህ ቀደም ይህን ለማድረግ የሞከሩ እርሱ በዘረጋው ሰፊ መረብ አፋቸውን እንዲዘጉ ይደረጉ ነበር።

በርካታ ናይጄሪያ የሚገኙ ቃላቸውን ለቢቢሲ የሰጡ ሰዎች ስለ ጆሽዋ እናጋልጣለን በማለታቸው መደብደባቸውን ተናግረዋል። አንድ ሰው ደግሞ በጥይት ተመቶ ቆስሏል። በጥይት የቆሰለው ግለሰብ በዩትዩብ ጆሽዋን ለማጋለጥ በመሞከሩ ነው።

በመጋቢት 2022 የቢቢሲ ጋዜጠኞች ቡድን በሌጎስ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ቀረጻ ለማድረግ በሞከረ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂዎች ተኩስ ተከፍቶባቸዋል። የተወሰኑትም ለሰዓታት ታስረው ነበር።

ቢቢሲ በጉደዩ ዙርያ ቤተክርስቲያኑን ለማነጋግረ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ይሁንና በፓስተራችን ዙርያ የሚወራው ሐሰት ነው ሲል አስተባብሏል።

“መሠረተ ቢስ ክስ በነቢይ ቲቢ ጆሽዋ ላይ መፈብረኩ አዲስ አይደለም። አንዱም ክስ ተጨባጭነት የለውም። ” ሲል በጽሑፍ ምላሸ ሰጥቷል።

አራት የእንግሊዝ ዜጎች በቤተ ክርስቲያኑ ስለሚፈጸመው በደል ለዩኬ ባለሥልጣናት አቤት ቢሉም የተወሰደ እርምጃ እንዳልነበረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንድ እንግሊዛዊና ባለቤቱ የደረሰባቸውን ስቃይ በቪዲዮ ጭምር ለቢቢሲ አሳይተዋል። ፖሊስ ነን በሚሉ የጆሽዋ ሰዎች ሽጉጥ ተገደግኖባቸው መረጃውን በናይጄሪያ ለእንግሊዝ ኤምባሲ እአአ 2010 ላይ ሰጥተው ነበር።

ይህ እንግሊዛዊ እንደሚለው ሚስቱ በፓስተር ጆሽዋ በተደጋጋሚ መደፈሯን እና ሌሎች እንግሊዛዊያንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደሚገኙ ለኤምባሲው አስታውቆ ነበር።

ይሁንና በናይጄሪያ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ የወሰደው እርምጃ የለም።

አኔካ
የምስሉ መግለጫ, አኔካ

የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በጉዳዩ ዙርያ ከቢቢሲ ተጠይቆ የሰጠው ምላሽ የለም። ይሁንና በእንግሊዛዊያን ላይ የትም አገር የሚደርስ የመደፈርና ጾታዊ ጥቃቶችን በዋዛ እንደማይመለከት ገልጿል።

የጆሽዋ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም ድረስ ከፈተኛ ተከታዮች አሉት። አሁን ቤተ ክርስቲያኑን የምታስተዳድረው የጆሽዋ ባለቤት የነበረቸው ኤቨሊን ናት። ባለፈው ሐምሌ ምዕመናንን ይዛ ወደ ስፔን ተጉዛ ነበር።

አኔካ ከደርቢ ዩኬ ወደ ጆሽዋ ቤተክርስቲያን ስትሄድ 17 ዓመቷ ነበር። ለቢቢሲ እንደተናገረችው በጆሽዋ ግፍ የተፈጸመባቸው ነገር ግን ወደ አደባባይ ያልወጡ እጅግ በርካታ ሰዎች አሉ።

“ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጣቸው ሊፈተሽ ይገባል። ይህ ሰው ለዚህን ያህል ዘመን እንዴት ግፍ እየፈጸመ ምንም ሳይባል ቀረ የሚለው ከርሱ ጋር የሚሰሩ አብያተ ክርስቲያናትንም ሊያስጠይቅ ይገባል” ትላለች።