አደገኛው የሜክሲኮ ዕፅ አዘዋዋሪ እና የኤል ቻፖ ልጅ አሜሪካ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

"ኤል ማዮ" [በስተግራ] እና የኤል ቻፖ ልጅ ዮዋኪን ጉዝማን ሎፔዝ

የፎቶው ባለመብት, DEA/ICE

የምስሉ መግለጫ, "ኤል ማዮ" [በስተግራ] እና የኤል ቻፖ ልጅ ዮዋኪን ጉዝማን ሎፔዝ

ከዓለም ፈርጣማ የዕፅ አዘዋዋሪዎች አንዱ የሆነው የሜክሲኮዋ ሲናሎዋ ዕፅ ንግድ አለቃ ኢስማኢል “ኤል ማዮ” ዛምባዳ ከኤል ቻፖ ልጅ ዮዋኪን ጉዝማን ሎፔዝ ጋር በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ኤል ፓሶ ከተማ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የ76 ዓመቱ ዛምባዳ፤ አሁን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እስር ላይ ካለው ዮዋኪን “ኤል ቻፖ” ጉዝማን ጋር ነው የወንጀለኞች ቡድን የመሠረተው።

የኤል ቻፖ ልጅ ዮዋኪን ጉዝማን ሎፔዝ ከዛምባዳ ጋር በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስትር በመግለጫው አስታውቋል።

ዛምባዳ ባለፈው የካቲት ፌንታኒል የተባለውን አደገኛ ዕፅ በማምረትና በማሰራጨት ወንጀል በአሜሪካ አቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦበት ነበር።

ፌንታኒል የተባለው ዕፅ ከሄሮዊን የበለጠ ኃይል ያለው ሲሆን አሜሪካ ውስጥ ለተከሰተው የኦፒዮይድ ቀውስ ምክንያቱ ይህ ዕፅ ነው ይባላል።

የአሜሪካው አቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ በለቀቁት የፅሑፍ መግለጫ ሁለቱ ግለሰቦች “በዓለማችን በጣም አደገኛና አመፀኛ ከሚባሉ የዕፅ ዝውውር ድርጅቶች አንዱን የሚመሩ ናቸው” ብለዋል።

“ኤል ማዮ እና ጉዝማን ሎፔዝ በፍትሕ ሚኒስትር እጅጉን ከሚፈለጉ የዕፅ ንግድ መሪዎች መካከል ናቸው” ሲሉ አክለዋል አቃቤ ሕጉ።

“ፌንታኒል ማለት ሀገራችን ውስጥ ቀውስ የፈጠረ ገዳይ ዕፅ ነው። የፍትሕ ሚኒስትር ማኅበረሰባችንን በዚህ ዕፅ የሚመርዙ እያንዳንዳቸው የዕፅ ዝውውር መሪዎች፣ አባላት እና አጋሮች በቁጥጥር ሥር እስኪውሉ ድረስ እረፍት የለውም” ብለዋል የአሜሪካው ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ ባለሥልጣን።

የአሜሪካ ባለሥልጣን እንደሚሉት የሲናሎዋ አዘዋዋሪዎች ወደ አሜሪካ ከፍተኛ መጠን ያለው ዕፅ ይልካሉ።

ከዚህ ቀደም የአሜሪካ ባለሥልጣናት ባወጡ መረጃ መሠረት ፌንታኒል የተባለው ዕፅ ዕድሜያቸው ከ18-45 ባሉ አሜሪካዊያንን ዘንድ ቁጥር አንድ የሞት መንስዔ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካው መድኃኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ [ዲኢኤ] ዛምባዳ ያለበትን ለጠቆመ 15 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እሰጣለሁ ማለቱ ይታወሳል።

በአውሮፓውያኑ 2019 የ ኤል ቻፖ ችሎት ሲካሄድ የጉዝማን ጠበቃዎች ዛምባዳ የሜክሲኮ መንግሥትን “ጠቅልሎ” በጉቦ በመያዝ ያለምንም ከልካይ በነፃነት እየተዘዋወረ ነው ሰሉ ወቅሰውት ነበር።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚለው ዛምባዳ ሜክሲኮ ውስጥ በርካታ ሕጋዊ “ንግዶች” ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል “ትልቅ የወተት አምራች ኩባንያ፣ የሕዝብ ማመላሻ ባስ እና ሆቴል” እንዲሁም ሪል ስቴት ይገኙበታል።

ዛምባዳ፤ ፌንታኒል የተባለውን ዕፅ ከማዘዋወር ባለፈ በሌሎች ዕፆች ዝውውር፣ በግድያ ወንጀል፣ በእገታ፣ ሕገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር እና በተደራጀ ወንጀል ክስ ይቀርብበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ባፈለው ግንቦት የዛምባዳ ዘመድ የነበረው ኤልሲዮ ኢምፔሪያል ካስትሮ አሊያም በቅፅል ስሙ “ቼዮ አንትራክስ” ሜክሲኮ ውስጥ በደረሰበት ጥቃት መገደሉ ይታወሳል። ቼዮ አንትራክስ በአሜሪካ ይፈለግ ነበር።

ዛምባዳ በዓለማችን ከሚንቀሳቀሱ ትላልቅ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አንዱ ሲሆን በተለይ በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ግለሰብ ነው።

ላለፉት አስርት ዓመታት ከፖሊስ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ሲንቀሳቀስ የቆየ ሲሆን የግለሰቡ መያዝ ዜና ብዙዎችን አስደንግጧል።

ሁለቱ ግለሰቦች እንዴት ባለ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ እስካሁን ግልፅ ባይሆንም ወደ አሜሪካ በአውሮፕላን ሳይገቡ እንዳልቀረ ተገምቷል።

ዎል ስትሪት ጆርናል የአሜሪካ እና የሜክሲኮ ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ሆምላንድ ሴኪዩሪቲ ኢንቬስቲጌሽንስ እና ኤፍቢአይ ለወራት ባቀናጁት ሰንሰለት መሠረት ነው ዛምባዳ በአንድ ከፍተኛ የሲናሎዋ አባል ጉትጎታ አውሮፕላን የተሳፈረው።

ጋዜጣው አክሎ እንደፃፈው ዛምባዳ ሜክሲኮ ውስጥ የሚገኙ ሚስጥራዊ አየር ማረፊያዎችን ለማየት በሚል ነው አውሮፕላን የተሳፈረው።