አደገኛው የሜክሲኮ ዕፅ አዘዋዋሪዎች መሪ እንዴት አሜሪካ ውስጥ ተገኝቶ ሊያዝ ቻለ?

ኤል ማዮ የተሳፈረባት አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኤል ማዮ የሚያውቀው የሚገዝበት አውሮፕላን ወደ ሰሜናዊ ሜክሲኮ እንደሚበር ቢሆንም፣ ነገር ግን ያረፈው በጥብቅ በምትፈልገው የአሜሪካ ግዛት ውስጥ ነበር። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው?

እስማኤል ‘ኤል ማዮ’ ዛምባዳ በአህጉረ አሜሪካ በሚካሄደው በዕፅ ዝውውር እና ንግድ ስሙ የገነነ ሰው ነው።

‘ኤል ማዮ’ በተጨማሪም በሚፈጽማቸው የጭካኔ ድርጊቶች ይታወቃል።

በዕጽ አዘዋዋሪዎች መካከል በሚነሳ ጦርነት ውስጥ እጅግ በከፋ ጭካኔ የተሞላበት አመራሩ ይታወቃል። ብዙዎች ‘ኤል ማዮ’ን ሲገልጹት እራሱ የስቃይ እና የሞት አምሳያ ነው ይላሉ።

ይህ ግለሰብ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ በእስር ላይ ከሚገኘው ዮአኪን ‘ኤል ቻፖ’ ጉዝማን ጋር በመተባበር በዓለም ግዙፍ የሚባለውን የሲናሎዋ አደንዛዥ ዕጽ አምራች እና አከፋፋይ ቡድንን መሥርቷል።

ኤል ማዮ ግን ከኤል ቻፖ ጉዝማን በተለየ መልኩ ለ35 ዓመታት በቁጥጥር ስር ሳይውል ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ከቀናት በፊት በአንድ የቅርቤ በሚለው የሲናሎዋ ቡድን አባል ተከድቶ በመጨረሻ በአሜሪካ የፀጥታ ኃይሎች እጅ ላይ ወድቋል።

የ78 ዓመቱ አዛውንት ሐሙስ ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም. ስለመዳረሻው ሐሰተኛ መረጃ ተሰጥቶት አውሮፕላን ከተሳፈረ በኋላ ቴክሳስ ግዛት ኤል ፓሶ ከተማ አቅራቢያ ነበር የተያዘው።

የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ በግድያ፣ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር እንዲሁም በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በመጠቀም የሚሉ እና ሌሎች ተደራራቢ ክሶች መስርቶበታል።

ኤል ማዮ ባለፈው ሳምንት አርብ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሏል።

ከኤል ማዮ በአሜሪካ ከመያዝ በላይ ትልቁ መነጋገሪያ የሆነው፤ ኤል ማዮ ተታሎ በአሜሪካውያን እጅን የገባበት ሁኔታ ዋነኛ ጉዳይ ሆኗል።

የሲናሎዋ ካርቴል መሪ የተከዳው በቀድሞ የንግድ አጋሩ ኤል ቻፖ ልጅ በሆነው ጉዝማን ሎፔዝ መሆኑ ደግሞ ከሁሉ በላይ አግራሞትን ፈጥሯል።

የኤል ማዮ መያዝ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የኤል ማዮ መያዝ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኤል ቻፖ ወራሽ ይሆናል የሚባለው ዮአኪን ጉዝማን ሎፔዝ፤ በሰሜን ሜክሲኮ የሚገኝ አየር ማረፊያን ላስጎብኝህ በማለት ኤል ማዮን አታሎ ነው ወደ አሜሪካ የወሰደው።

እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም የኤል ቻፖ ልጅ ኤል ማዮን አሳልፎ የሰጠው ከአሜሪካ መንግሥት ጋር አንዳች ስምምነት ላይ በመድረሱ ነው እየተባለ ነው።

ዮአኪን ጉዝማን ሎፔዝ ከሜክሲኮ ተነስቶ መዳረሻቸው በሆነችው የአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ከኤል ማዮ ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል።

እአአ 2010 ላይ ኤል ማዮ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ፤ “እያዛለሁ ብለህ አትፈራም ወይ?” ተብሎ ሲጠየቅ፤ “እስር ቤት የመግባት ሃሳብ በራሱ በጣም ይረብሸኛል። እራሴን የማጥፋት አቅሙ አለኝ ብዬ ባላስብም በእስር ከመቆየት እራሴን ማጥፋት እምርጣለሁ” ብሎ ተናግሮ ነበር።

ይህ ለበርካታ ዓመታት በከፍተኛ ጥንቃቄ እየኖረ ሳይያዝ የቆየው ዋነኛው የዕፅ አዘዋዋሪ እንዴት እንዲህ ባለ ቀላሉ ዘዴ ሊታለል እና ቀጥታ በአዳኞቹ እጅ ሥር ሊገባ ቻለ? የሚለው መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው።

የቀድሞው የአሜሪካ የአደንዥ ዕፅ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ባልደረባ ማይክ ቪዲል፤ ኤል ማዮ አውሮፕላኑን የተሳፈረው ወዶ ላይሆን ይችላል የሚል ግምት አለው።

“ዕድሜው በ70ዎቹ ውስጥ ያለ እና ጤና የራቀው ሰው ነው” ሲልም ያክላል።

የኤል ቻፖ እንዲሁም የኤል ማዮ በቁጥጥር ስር መዋል እንዲሁም ሎስ ቻፒቶስ በሚል መጠሪያ ስሙ የሚታወቀው የኤል ቻፖ ልጅ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር መሻረክ፤ በቀጣይ የሲናሎዋ ካርቴል መሪ ማን ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄንም አስነስቷል።

ኤል ቻፖ በቁጥጥር ስር ውሎ ለአሜሪካ ተላልፎ በተሰጠበት ወቅት የቡድኑ መሪ ለመሆኑ የእርስ በርስ ፍትጊያዎች ከመኖራቸው በተጨማሪ ባላንጣ ቡድኖች ግዛት ለማስፋፋት ጥረት አድርገው ነበር።

ከኤል ቻፖ መያዝ በኋላ እአአ 2019 ላይ ሌላ የሲናሎዋ ከፍተኛ አመራር እና የኤል ቻፖ ልጅ የሆነው ኦቪዲዮ ጉዝማን ሎፔዝ በሜክሲኮ ፖሊስ በተያዘበት ጊዜ ያልተጠበቀ ክስተት አጋጥሞም ነበር።

እስማኤል ዛምባዳ ጋርሺያ (ኤል ማዮ) እና ዮአኪን ጉዝማን ሊፔዝ

የፎቶው ባለመብት, US Drug Enforcement Administration

የምስሉ መግለጫ, እስማኤል ዛምባዳ ጋርሺያ (ኤል ማዮ) እና ዮአኪን ጉዝማን ሊፔዝ

ኦቪዲዮ ከፖሊስ ቁጥጥር በአስቸኳይ እንዲለቀቅ የጠየቁ የሲናሎዋ ካርቴል ቡድን አባላት ኩሊካና በምትባል የሜክሲኮ ከተማ ላይ ሰላማዊ ሰዎችን እና የፖሊስ ተቋማትን ዒላማ ያደረገ የከባድ መሳሪያ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።

ይህም የሜክሲኮ ፖሊስ ኦቪዲዮን እንዲለቅ አስገድዶታል።

ከሦስት ዓመታት በኋላ ዳግም በቁጥጥር ስር ውሎ ለአሜሪካ ተላልፎ የተሰጠው ኢቪዲዮ አሁን እስር ላይ ሆኖ የፍርድ ሂደቱን እየተከታተለ ይገኛል።

የሜክሲኮ ባለሥልጣናት የኤል ማዮን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ ሊፈጠር የሚችል የደኅንነት ችግርን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፀጥታ ኃይሎችን ወደ ሲናሎዋ ግዛት አሰማርቷል።

የቀድሞ የአሜሪካ የዕፅ ቁጥጥር ባለሥልጣል ባልደረባ ቀጣዩ የሲናሎዋ ካርቴል ቡድን መሪ የኤል ቻፖ ወንድም ሊሆን ይችላል ይላል።

ይሁን እንጂ በዕፅ ዝውውር ንግድ ውስጥ መሰል የሥልጣን ከፍተቶች እንዴት ሊሞሉ እንደሚችሉ በትክክል መገመት አስቸጋሪ ነው።

የኤል ማዮ በቁጥጥር ስር መዋል ከተሰማ በኋላ በርካቶች እየጠየቁ ያለው ጥያቄ እስሩ አሁን ለምን? የሚል ነው።

ይህ ኤል ማዮን የመያዝ ዘመቻ ለወራት ሲታቀድ ቆይቷል። አሜሪካ ይህን ግለሰብ ለመያዝ ቆርጣ እንድትነሳ ያደረጋት የአደንዣ ዕፅ ዝውውር በማኅብረሰቡ ውስጥ እየፈጠረ ያለው ቀውስ ቀዳሚ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ይህንንም በአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ የቪዲዮ መልዕክት ላይም ተነስቷል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የኤል ማዮን በቁጥጥር ስር መዋል ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “አገራችን ከገጠሟት አደገኛ ፈተናዎች ሁሉ ፌንታሊን ቀዳሚው ነው” ሲሉ በዕፅ አዘዋዋሪዎቹ የሚመረተው እና የሚሠራጨውን ዕፅ ጠቅሰዋል።

“ማኅበረሰባችንን የመመረዝ ተግባር የፈጸሙ እያንዳንዱ የካርቴል ቡድን መሪዎች፣ አባል እና ተባባሪ ተጠያቂ እስኪሆን ድረስ አናርፍም” ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ዕድሜያቸው በ18 እና 45 ላሉ አብዛኞቹ አሜሪካውያን ሞት ምክንያት ፌንታሊን የተባለው አደገኛ ዕፅ ነው።

ባለሙያዎች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የሚገባውን ፌንታሊን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ባይቻልም፤ የፅዕ አዘዋዋሪ ቡድኖችን መሪዎች በቁጥጥር ሥር በማዋል የፌንታሊን ምርት እና ሥርጭትን በከፍተኛ መጠን ለማስተጓጎል ያስችላል ይላል።

ኤል ማዮ ዛምባዳ ምንም እንኳ በእርጅና ዘመኑ፣ ጤናው ተቃውሶ እና ተከድቶ በአሜሪካ ሕግ አስከባሪዎች እጅ ላይ ቢወድቅም፤ እስሩ በአሜሪካ ያለውን የፌንታሊን ሥርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ላይ ምን ያህል ተጽእኖ ይኖረዋል የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው።