እስራኤል ሊባኖስ ላይ በሰነዘረችው የአየር ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ

የሒዝቦላህ ግምጃ ቤት ነው ተብሎ ጥቃት የተሰነዘረበት ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ እናት ከሁለት ልጆች ጋር ተገድላለች

በደቡብ ሊባኖስ፣ በእሰራኤል ጥቃት 10 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

ነባቲያ በምትባል ከተማ አንድ የሶሪያ ስደተኞች ሥራ ሠርተው ማታ የሚያርፉበት ሕንጻ በአየር ጥቃቱ ተመቷል ሲሉ የጤና ሚኒስትሩ ፊራስ አቢያድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስራኤል በበኩሏ ሕንጻው የሒዝቦላህ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ነው ብላለች።

ይህን ተከትሎ በኢራን የሚደገፈው ሒዝቦላህ በርካታ ሮኬቶችን በሁለት ዙር ወደ እስራኤል ያስወነጨፈ ሲሆን በሰሜናዊ እሰራኤል ኪቡዝ አካባቢን ዒላማ አድርጓል።

ይሁንና በእስራኤል ጥቅም ላይ ስለደረሰ ጉዳት የተባለ ነገር የለም።

በመጀመርያው ዙር የሒዝቦላህ ጥቃት ጉዳት ባይደርስም በሁለተኛው ዙር የሮኬት ጥቃት ግን ሁለት ወታደሮቼ ተጎድተዋል ብሏል የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር።

በእስራኤልና ሒዝቦላህ መካከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መካረር የታየ ሲሆን በተለይም እስራኤል በደቡብ ቤይሩት ታዋቂውን የሒዝቦላህ ኮማንደር ፉአድ ሹኩርን ከገደለች ወዲህ ቡድኑ ለበቀል ዝቷል።

የሒዝቦላህ መሪ ሐሰን ነስረላህ ግድያውን መበቀላችን ጥርጥር የለውም ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ የሒዝቦላህ እና የእስራኤል ፍጥጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማየል በተለይ እስራኤል በጋዛ የምታደርሰውን መጠነ ሰፊ ጥቃትና ይህን ተከትሎም እየደረሰ ያለውን ሰብአዊ የንጹሐን ሞት ይቀንሳል የተባለ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ጥላውን እንዳያጠላ ተፈርቷል።

ኳታር፣ ግብጽና አሜሪካ በዶሓ ሐማስና እስራኤልን የሰላም ስምምነት ለማፈራረም ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ይታወሳል።

የዚህ ስምምነት መፈረም ኢራን በዋና ከተማዋ ቴህራን የተገደሉትን የሐማሱን መሪ ኢስማኤን ሐኒያን ደም ለመበቀል እወስደዋለሁ ያለቸውን እርምጃ ለማስቀረት ጠቃሚ ነው እየተባለ ነው።

ኢራን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በእስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንዳትወስድ የሚያደርግባትን ግፊት ውድቅ አድርጋለች።

ኢራን ይህን ትበል እንጂ የሰላም ስምምነቱ ከሰመረ በሚል የበቀል እርምጃዋን እንዳዘገየች ተንታኞች እየተናገሩ ነው።

የሌባኖስ የጤና ሚኒስትር አቢያድ እስራኤል ለሰላም ስምምነትም ሆነ ለሰዎች ነፍስ ደንታ የላትም ብለዋል።

ከሟቾቹ መካከል እናትና ሁለት ልጆቿ ይገኙበታል።

ከሞቱት ዐሥር ሰዎች ሌላ 5 ተጨማሪ ሰዎች በአደገኛ ሁኔታ ቆስለው ሆስፒታል ጽኑ የሕሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

እስራኤል የሒዝቦላህ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ነው ያለችው ሕንጻ ባለቤት ሑሴን ቶህማዝ ቦታው በጭራሽ የሒዝቦላህ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት እንዳልሆነና ለፍቶ አዳሪዎች ቀን ቀን ብረታ ብረት ሥራ ሠርተው ማታ የሚያርፉበት መኖርያ እንደሆነ ተናግሯል።