“ቁጥር 7 ኢትዮጵያዊነት የሚበየንበት ክፍል ነው” – ፓስፖርት ለማግኘት የሚንገላቱ የትግራይ ተወላጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“ሌባ አይደለሁም፣ ትክክለኛ ማስረጃዎች ይዤ፣ ምንም ሳላጠፋ ነው የሄድኩት። እንዲህ መዋሸት፣ ፀጉሬን ቀይሬ መሄድ፣ መንገላታት አያስፈልገኝም ነበር” ይላል ከትግራይ ተወላጅ ቤተሰቦች መገኘቱ ፓስፖርት ለማውጣት ፈተና ያሳየው ናሆም ሰለሞን*።
የአዲስ አበባ ነዋሪው ናሆም፤ ከሁለት ወር መመላለስ እና እንግልት በኋላ ፓስፖርት ማግኘት የቻለው የእናት እና አባቱን የትውልድ ስፍራ በመቀየር “ደሴ እና ድሬዳዋ” ብሎ ከተናገረ በኋላ እንደሆ ያስረዳል።
ይህንንም ሲያደርግ በተደጋጋሚ የተመላለሰባቸው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ኦፊሰሮች እንዳይለዩት ገጽታውን ቀይሮ መቅረቡን ይገልጻል።
“ፀጉሬን አፍሮ ነበር ወደላይ የማበጥረው፤ [ከአንድ ቀን በፊት] በሻምፖ አድርጌ በጣም ደምድሜው፣ በሹራብ ኮፍያ አድርጌ ነው ያሳደርኩት” ይላል፤ ደጋግሞ ካነጋገራቸው ኦፊሰሮች ራሱን ለመደበቅ የተጠቀመውን መንገድ ሲያስታውስ።
“አያቴ ልጅ እያለች ነው [ከትግራይ] አዲስ አበባ የመጣችው። ኖራ የሞተችው ጣልያን ሰፈር ነው። እናቴም እዚያው ነው የተወለደችው” ሲል እንግልት ያሳየው የአያቱ የትግራይ ተወላጅነት መሆኑን ይገልጻል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ፓስፖርት ለማውጣት በሄደበት የቀጠሮ ቀን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ኦፊሰር ዘንድ ሲቀርብ የቀረበለት የመጀመሪያ ጥያቄ “ወላጆችህ ከየት ናቸው?” የሚል ነበር።
“የእናቴን እና አባቴ አዲስ አባባ እንደሆኑ ስነግረው ‘አያቶችህስ?’ ብሎ ጠየቀኝ። ‘በእናቴ ከአድዋ እና አዲግራት ናቸው’ አልኩት። የዛኔ ነው ወረቀቴ ላይ ‘ይጣራ’ የሚል ፅፎ ወደ ሰባት ቁጥር የላከኝ” የሚለው ናሆም፤ ማጣራት ወደሚደረግበት “ቢሮ ቁጥር ሰባት” ከተላከ በኋላ ፓስፖርት ሳያገኝ ለወራት መመላለሱን ይናገራል።
የልደት ምስክር ወረቀት፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የውጤት ካርዶች፣ የዩኒቨርስቲ ዲግሪ ሰርቲፊኬት፣ የሥራ ልምዶች እንዲሁም የእናት እና አባት መታወቂያ ፓስፖርት ለማግኘት ያቀረባቸው ማስረጃዎች ናቸው።
በኦፊሰሮች ዘንድ ግን ከእነዚህ ማስረጃዎች በላይ ተፈላጊ የነበረው ትግራይ ክልል ውስጥ የተሰጠ የአጎት ወይም አክስት መታወቂያ እንዲያቀርብ መሆኑን ናሆም ይገልጻል።
“እኔ አክስቶቼም አጎቴም የተወለዱት እዚሁ አዲስ አበባ ነው። መጨረሻ ላይ እንዲያውም የእናቴን አጎት መታወቂያ [ፎቶ] ከአዲግራት በቴሌግራም አስልኬ ነበር። እርሱን ፕሪንት አድርጌ ይዤላቸው ሄድኩ። ‘ይህ የእናትህ እንጂ ያንተ አጎት አይደለም’ ነው ያሉኝ።”
“ይህንን ለምን እንደሚያደርጉ ምንም አላስረዱኝም። የመጨረሻ ቀን በጣም ስሜታዊ ሆኜ ‘ለኢትዮጵያዊነቴ ከዚህ በላይ ማረጋገጫው ምንድነው? ፊቴን እንኳን አይተህ እንዴት አትናገርም’ ብዬው ጭምር ምንም ምክንያት ሊያቀርብልኝ አልቻለም” የሚለው ናሆም የመጨረሻ አማራጭ ሆኖ የታየው የቤተሰቦቹን የትውልድ ስፍራ ቀይሮ መናገር እንደሆነበር ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, fana/screenshot
“ተጨማሪ ማስረጃ አቅርቡ”
“ማንነት እና ዜግነት” የሚገልጽ ፓስፖርት እና ሌሎች የጉዞ ሰነዶች የመስጠት ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት፤ በአዲስ አበባ ያለውን ዋና መሥሪያ ቤቱን ጨምሮ በ12 ከተሞች ቅርንጫፎ ጽህፈት ቤቶች አሉት።
ከእነዚህ ቅርንጫፎቹ ውስጥ አንዱ የሆነው በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ የሚገኘው የአገልግሎቱ ጽህፈት ቤት፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከሦስት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ሥራ አቋርጦ ቆይቷል።
የመቀለው ቅርንጫፍ አዲስ ፓስፖርት ከማውጣት ውጪ ያሉትን ፓስፓርት የማደስ፣ የጠፋ ፓስፖርት እና የተበላሸ ፓስፖርት የመተካት አገልግሎቶችን መስጠት የጀመረው ባለፈው ሰኔ ወር ነበር።
ቅርንጫፉ አገልግሎት ባቆመባቸው ባለፉት ዓመታት የፓስፖርት አገልግሎት ፈላጊ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በኦንላይን ቀጠሮ ካስያዙ በኋላ መዳረሻቸው አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ አካባቢው የሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ወደ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ያቀኑ አራት የትግራይ ተወላጆች፤ ከመደበኛው ፓስፖርት የማውጣት ሂደት ባሻገር ተጨማሪ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ እንደተጠየቁ እና “በተለየ መንገድ” እንደተስተናገዱ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Immigration and Citizenship Service
የአገልግሎቱ መረጃ እንደሚያመለክተው አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት የሚፈልጉ አመልካቾች ማሟላት የሚጠበቅባቸው ሰነዶች ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው የተረጋገጠ የልደት ምስክር ወረቀት ነው። ሌላኛው አስፈላጊ ሰነድ የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ ሲሆን፣ መታወቂያው ጊዜያዊ ከሆነ ከቀበሌው የድጋፍ ደብዳቤ ማቅረብ ያስፈልጋል።
የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የፓስፖርት አገልግሎት ፈላጊዎች በአንጻሩ “የስምንተኛ ክፍል ትምህርት መረጃ እንዲሁም የወላጅ እና ሌሎች ዘመዶች መታወቂያ” እንዲያቀርቡ እንደተጠየቁ ገልጸዋል። ከዚህም ባሻገር “ኤርትራዊ ናችሁ” በሚል ምርመራ እንደሚደረግባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች - ኢትዮጵያ የተሰኘው በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሰራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው ሪፖርት ይህንኑ አንጸባርቋል።
የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ተቋም፤ የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት የሚያመለክቱ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች “ከፍተኛ የሆነ እንግልት፣ ወከባ እና ማስፈራራት” እየደረሰባቸው እንደሆነ በምርመራ እንዳረጋገጠ በባለ ሰባት ገፅ ሪፖርቱ አስታውቋል።
“ከ20 በላይ” ሰዎችን በማነጋገር በተደረገው ምርመራ “በሕግ ያልተጻፉ መመሪያዎች በትግራይ ተወላጆች ላይ ተፈጻሚ” እንደሚደረጉ እንደተረጋገጠ የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ ብርሃነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህ አይነቱ አሠራር የሚያስከትለው ችግር “በሶማሌ ክልል ተወላጆች ላይም ጭምር” እንደሚፈጸም ተቋሙ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
“ቢሮ ቁጥር ሰባት”
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል እና የትግራይ ተወላጅ ነዋሪዎች በሙሉ በተመሳሳይ የሚያነሱት አንድ ቢሮ “ቁጥር ሰባት” የሚል ነው።
ቀጠሯቸው ደርሶ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና መሥሪያ ቤትን ደጃፍ የረገጡ ነዋሪዎች የያዙት መረጃ የትግራይ ተወላጅ ስለመሆናቸው ሲያሳይ አልያም ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚሰጡት ምላሽ ይህንን ሲያመለክት ወደዚህ ቢሮ እንደተላኩ ገልጸዋል።
የአያቱ የትውልድ ቦታ ትግራይ ክልል መሆኑ ሲታወቅ ወደዚህ ክፍል መላኩን የሚናገረው የአዲስ አበባ ነዋሪው ናሆም፤ ክፍሉ “ሁለት ወይም ሦስት” ሆነው የተቀመጡ ኦፊሰሮችን የያዙ ጠረጴዛዎች የሚገኙበት እንደሆነ ያስታውሳል።
“ክፍሉ ውስጥ ያሉት ትግረኛ የሚናገሩ [ባለሙያዎች] ናቸው” የሚለው ናሆም፤ በክፍሉ የሚገኙ ባለሙያዎች ሰነዶችን በማየት እና በመጠየቅ ምርመራ እንደሚያደርጉ ይናገራል።
ፓስፖርት ለማውጣት ሄዶ ወደዚህ ክፍል የተላከ አንድ በመቀለ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በፖሊስነት የሚያገለግል መኮንን፤ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳጋጠመው ለቢቢሲ ተናግሯል።
በመጀመሪያ ቀጠሮው በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት በተገኘበት ወቅት፤ ከትውልድ ቦታው አድዋ እንዳባጻህማ የድጋፍ ደብዳቤ እና የወላጆች መታወቂያ እንዲያቀርብ መጠየቁን ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, fana/screenshot
“[ቢሮ ቁጥር ሰባት ያለ ባለሙያ]፤ ‘የትውልድ ከተማህ የት ነው?’ አለኝ። 'አድዋ' አልኩት። ‘አድዋ የት?’ 'እንዳባጻህማ'። 'ማን ማን ያዋስኑታል?' ብሎ ጠየቀኝ። የወረዳውን ድንበር የሚያዋስኑትን ሁሉ ነገርኩት። ከዚያም በመታወቂያው ላይ ያለው ቁጥር ከክልሉ በተጻፈው የድጋፍ ደብዳቤ ውስጥ አልተካተተም ብሎ ውድቅ አደረገው። በዚህ ምክንያት ብቻ ሳልስተናገድ ቀረሁ” ሲል የደረሰበትን ያስረዳል።
ቢሮ ቁጥር ሰባት “ከትግራይ ክልል የመጡ ወይም የትግራይ ተወላጆች ብቻ” የሚስተናገዱበት እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ምክትል ዳይሬክተር አቶ መብርሂ፤ ተቋማቸው ባደረገው ምርመራ “የትግራይ ተወላጆች” የሆኑ የፓስፖርት አገልግሎት ፈላጊዎች ወደዚህ ቢሮ ለምርመራ እንደሚላኩ እንደተገነዘበ ያነሳሉ።
“ሰባት ቁጥር የሚባለው ምርመራ የሚደረግበት ነው። በመደበኛው ሁኔታ ፓስፖርት ለማውጣት የተለየ ምርመራ አይደረግም” የሚሉት አቶ መብርሂ፤ “በእኛ ግንዛቤ ቢሮው ኢትዮጵያዊነት የሚበየንበት ነው” ሲሉ ይገልጹታል።
በሕገ መንግሥቱ ላይ ከወላጆቻቸው አንዱ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ሰዎች ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደሆነ መደንገጉን የሚጠቅሱት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በቢሮ ቁጥር ሰባት ውስጥ ግን “ዜግነት የሚበየነው በምርመራ ነው” ይላሉ።
“የሕግ እና መብት ጥሰቶች”
የቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ያወጣው ሪፖርት፤ የፓስፖርት አገልግሎት ፈላጊ የትግራይ ተወላጆች የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያ ሦስት “የሕግ እና መብት ጥሰቶች” መፈጸማቸውን አስፍሯል። በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሰው የመጀመሪያው የሕግ ጥሰት በሕገ መንግሥቱ ላይ ከተጠቀሰው የዜግነት መብት ጋር የሚያያዝ ነው።
“ኢትዮጵያዊ ዜግነት አንዱ የሚያስገኘው ፓስፖርት የማግኘት መብት ነው” የሚሉት አቶ መብርሂ፤ “እነዚህ ሰዎች ከትግራይ ስለተወለዱ ብቻ ይህንን መብት አጥተዋል” ባይ ናቸው።
“የእኩልነት መብት” በተቋሙ ሪፖርት ላይ የተጠቀሰ ሌላኛው ጥሰት ነው። “[የተቋሙ አሠራር] በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 የተመለከተውን ‘ዜጎች በሕግ ፊት ዕኩል ናቸው’ የሚል ድንጋጌ የተላለፈ ነው። ይህ ማለት ሰዎች ከትግራይ ስለመጡ ብቻ ፓስፖርት ለመስጠት ተጨማሪ መስፈርት እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው። ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሆንክ በተቀመጠው መስፈርት ብቻ ነው መስተናገድ ያለብህ” ሲሉ ምክትል ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
በተጨማሪም፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት “በሚከተለው አሠራር ምክንያት” ፓስፖርት ማግኘት ያልቻሉ የትግራይ ተወላጆች “በሌላ መልኩ የመዘዋወር መብታቸው መገደቡን” አቶ መብርሂ ይከራከራሉ።
የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋሙ፤ በፓስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ሳቢያ "ተጥሰዋል" ያላቸው የሕግ እና መብት ጉዳዮች ግን በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አገልግሎት ቡድን መሪ ለሆኑት አቶ አዳነ ደበበ የሚዋጥ አይደለም።
“ከድንበር አካባቢዎች” የፓስፖርት አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ ተገልጋዮች ላይ "አጠራጣሪ ነገር ሲታይ" ተጨማሪ ማስረጃ እንደሚጠየቅ የሚናገሩት አቶ አዳነ፤ ይህ ዓይነቱ አሠራር ከዚህ ቀደምም የነበረ እና በትግራይ ተወላጆች ላይ ብቻ የሚፈጸም እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

የፎቶው ባለመብት, Immigration and Citizenship Service
ከጎረቤት አገሮች ጋር ተመሳሳይ “ቋንቋ እና ባህል” ከሚገኝባቸው “የሶማሌ እና ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ቦረና እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ አካባቢ” የሚመጡ ተገልጋዮች “ሁሉም ባይሆንም” ይህ ዓይነቱ የማጣራት ሥራ እንደሚከናወንባቸው ያስረዳሉ።
የፓስፖርት አገልግሎት ቡድን መሪው፤ “ቢሮ ቁጥር ሰባት ላይ የትግራይ ተወላጆችን የሚለዩ አሉ። የሶማሌ የሚለዩ አሉ፣ የኦሮሞ የሞያሌ አካባቢ የሚለዩ አሉ። የጋምቤላን የሚለዩ አሉ። ይህ ክፍል የትግራይ ተወላጆች ብቻ የሚለዩበት አይደለም” ሲሉ የቀረውን ወቀሳ አስተባብለዋል።
በትግራይ ተወላጆች ላይ ማጣራት የሚደረገው “ኤርትራውያን ፓስፖርት የሚገኙበት ሁኔታ እና ስጋት” በመኖሩ እንደሆነ የሚናገሩት የፓስፖርት አገልግሎት ቡድን መሪው፤ ሐሰተኛ መታወቂያ እና የልደት ምስክር ወረቀት መኖሩም ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
“[ኢትዮጵያ ውስጥ] መወለድ ኢትዮጵያዊ አያስብልም። አያቱ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ። ግን በሪፈረንደም ኤርትራ ትገንጠል ብሎ የፈረመ ኤርትራዊ፤ ቅድመ አያቱ ጀምሮ እዚህ የሆነ ኤርትራዊ እዚህ አለ። እሱ [ዜግነት] የሚሰጠው ወይ በሕግ ያመለክታል ዜግነት ይሰጠኝ ብሎ” ሲሉ ተቋማቸው ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድ ለሌላ አገር ዜጋ ፓስፖርት ላለመስጠት እየተከላከለ መሆኑን ይሞግታሉ።
አቶ አዳነ፤ “ኢሚግሬሽን የአገር ጉዳይ ነው የሚሠራው እንጂ በፍጹም አድልዎ የለውም። የፓርቲም አቅጣጫ የለውም። ሥራው ዜግነትን አጣርቶ መስጠት ብቻ ነው” ሲሉ ተቋሙ ላይ የቀረበውን ክስ አስተባብለዋል። ይሁንና የፓስፖርት አገልግሎት ፈላጊዎች ላይ የሚደረገው “የማጣራት ሂደት አንዳንድ ችግሮች ” ያሉበት መሆኑን አልሸሸጉም።

የፎቶው ባለመብት, Immigration and Citizenship Service
“ከአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር [በተያያዘ] አንዳንድ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ምክንያቱም አሁን ሰው በቀላሉ መቀለ፣ አዲግራት ሄዶ አይመጣም። ትራንስፖርቱም ችግር ነው። ከዚያ ጋር በተያያዘ ሰዎች እየተቸገሩ ነው። ይህ ስላለ ተመልሶ [መታወቂያ] የሚያመጣበት ሁኔታ ላይ ወይም ደግሞ አለመግባባት ችግሮች አሉ” ሲሉ ያስተዋሉትን ችግር ጠቅሰዋል።
አቶ አዳነ፤ በተቋሙ የፓስፖርት አገልግሎትን እንደሚመራ ኃላፊ ይህንን ችግር “እየፈቱ” መሆኑን ገልጸዋል። ከትግራይ ተወላጆች የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች ተከትሎም ችግሮች እንዲፈቱ “አቅጣጫ መስጠታቸውን” ተናግረዋል።
“ሠራተኞችንም ስለ ደንቡ ግንዛቤ ሰጥተናቸዋል። አንድን ሰው ዝም ብሎ [ተገልጋይ የሚያጉላላውን] ከቦታው ላይ እያነሳሁ ነው፤ በሌሎች እየቀየርኩ ነው። እየተተካካን እየሠራንበት ነው። ዛሬም ነገ ዜጎቻችን እንዲገላቱ አንፈልግም” ሲሉ ለውጦች እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
የፓስፖርት አገልግሎት ቡድን መሪው ከትግራይ ክልል ከሚመጡ አገልግሎት ፈላጊዎች ጋር በተያያዘ እንደ ትልቅ መፍትሔ የሚወስዱት በመቀለ ከተማ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ሙሉ በሙሉ የፓስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግን ነው።
ከሰኔ ወር ጀምሮ ጀምሮ በከፊል አገልግሎት መስጠት የጀመረው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ከዛሬ ሰኞ ከነሐሴ 13/2016 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ ፓስፖርትም መስጠት እንደሚጀምርም አስታውቀዋል።
____________
* ስሙ የተቀየረ












