የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የቱርኩ ንግግር የከሸፈው ኢትዮጵያ “የአገራቸውን ሉዓላዊነት ባለማክበሯ ነው” አሉ

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ

የፎቶው ባለመብት, @sntvnews1

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አንካራ ያደረጓቸው ንግግሮች ሳይሳኩ የቀሩት ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ባለማክበሯ ነው አሉ።

ፕሬዝዳንቱ ቅዳሜ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም. በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው ንግግራቸው፤ “ኢትዮጵያ ለሶማሊያን ሉዓላዊነት እውቅና በመከልከል ጸንታለች” ሲሉ ተደምጠዋል።

“በአንካራው ንግግር ላይ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና ነጻ የሆነች ጎረቤት አገር እንደሆነች ለመቀበል ፍቃደኛ እንዳልሆነች ደምድመናል። ይህንን [የሶማሊያን ሉዓላዊነት] እስክትቀበል ድረስ በምንም ጉዳይ ላይ አንነጋገርም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር የሚያስገኝላትን የመግባቢያ ሠነድ ከፈረመች በኋላ በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ መካከል ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።

ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ የምትለውን የባሕር በር ያስገኝላታል የተባለ ሲሆን፣ ሶማሊላንድ ደግሞ በምላሹ የአገርነት እውቅና ከኢትዮጵያ ታገኛለች ተብሏል።

ሶማሊያ በበኩሏ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት ሉዓላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን የሚጥስ ነው በማለት በአዲስ አበባ እና በሐርጌሳ መካከል የተደረሰውን ስምምነት አጥብቃ ስትቃወም ቆይታለች።

ይህን ተከትሎ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርክ መንግሥት አቀራራቢነት ሁለት ጊዜ ለድርድር አንካራ ላይ ተሰባስበው ነበር።

በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አደራዳሪነት የተደረገው ሁለተኛው ዙር ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ቢካሄድም ጉልህ የሆነ ለውጥ ሳያመጣ ከተጠናቀቀ በኋላ ሦስተኛ ዙር ንግግር ለማድረግ ለመስከረም 7/2017 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙ ተገልጾ ነበር።

ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ሐሰን ቅዳሜ ምሽት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የአገራቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እስካላከበረች ድረስ የሚደረጉ ድርድሮች ውጤት አያስገኙም ብለዋል።

“ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና እራሷን የቻለች ነጻ አገር መሆኗን አምና ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለችም። ይህ እስኪታረም ድረስ ስለ ባሕር በርም ሆነ በምንም ጉዳይ ላይ አንነጋገርም። ምክንያቱም ይህ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ይጥሳል” በማለት ፕሬዝዳንት ሐሰን በቱርክ መዲና አንካራ ለሁለት ዙር ሲካሄድ የቆየው ንግግር የተፈለገውን ውጤት ያላስገኘበትን ምክንያት ተናግረዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ለሦስተኛ ዙር ንግግር መስከረም 7/2017 ዓ.ም. አንካራ ላይ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, MFA OF TURKEY

የምስሉ መግለጫ, የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ለሦስተኛ ዙር ንግግር መስከረም 7/2017 ዓ.ም. አንካራ ላይ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ነበር።

አዲስ አበባ እና ሐርጌሳ የመግባቢያ ሠነዱን ከተፈራረሙ በኋላ ሞቃዲሾ ቅሬታዋን ከመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እስከ ተለያዩ አገራት በመውሰድ ስምምነቱን ተፈጻሚ እንዳይሆን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ስምምነቱን ከተፈራረሙ በኋላ ሶማሊያ ከቱርክ እና ከግብፅ ጋር ዝርዝሩ ይፋ ያልሆነ ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማለች።

ፕሬዝዳንቱ እንዲሁ ከስምምነቱ መፈረም በኋላ በቀጠናው እና በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ መሪዎች ጋር በአካል እና በስልክ በጉዳዩ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ቅዳሜ ምሽት ያደረጉትን ንግግርን ተከትሎ እስካሁን ከኢትዮጵያ በኩል የተባለ ነገር የለም።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከሶማሊያ ጋር ልዩነት የሚያጠብ እና ግንኙነታቸውን የሚያድስ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ስትል ቆይታለች።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በቀጥታ ንግግር ለችግሩ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ ሌሎች አገራት መውሰድን ትመርጣለች ስትል ትከሳለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ስለሶማሊያ ጉዳይ ሲናገሩ፤ “እኛን ለመክሰስ አገር ለአገር መሄድ አያስፈልግም፤ አዲስ አበባ መምጣት ይቻላል። ለመነጋገር ዝግጁ ነን. . . ” ብለው ነበር።