ዶናልድ ትራምፕ ከተመረጡ አንድ ሚሊዮን ስደተኞችን ሊያባርሩ ይችላሉ?

ስደተኞች በግዳጅ ከአገር ሲባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካን ለመምራት ፕሬዚዳንታዊ ዘመቻ እያደረጉ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ከተመረጡ በአገሪቱ ውስጥ ለመቆየት ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ስደተኞች በጅምላ እንደሚያባርሩ እየተናገሩ ነው።

ትራምፕ በዘመቻቸው ምን ያህል ስደተኞች እንደሚባረሩ የተለያዩ መልሶች ቢሰጡም፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት አብረዋቸው በዕጩነት የሚቀርቡት ጄዲ ቫንስ አንድ ቁጥር ጠቅሰዋል።

“ከአንድ ሚሊዮን እንጀምር” ሲሉ ከኤቢሲ ኒውስ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

አክለውም “ካማላ ሃሪስ ይህንን ልታሳካ አልቻለችም። ከአንድ ሚሊዮን ጀምረን መቀጠል እንችላለን” ብለዋል።

በትራምፕ የምርጫ ዘመቻዎች ላይ “የጅምላ ማባረሮችን” የሚያበረታቱ መፈክሮች ደምቀው ቢታዩባቸውም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ማባረር ቀላል እንዳልሆነ እና ሕጋዊ እንዲሁም የገንዘብ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥም ተንታኞች ያስረዳሉ።

የኢሚግሬሽን ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በበኩላቸው ቤተሰቦችን በመነጣጠል፣ ማኅበረሰቦችን በመበታተን እንዲሁም ማኅበራዊ እሴቶችን የሚበጣጥስ ስደተኞችን የማባረር ተግባር በሰው ልጅ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን እያስጠነቀቁ ነው።

ስደተኞች እንዲባረሩ የሚጠይቁ መፈክሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሕግ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?

በአሜሪካ ውስጥ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰነድ አልባ ስደተኞች እንደሚኖሩ የአገር ውስጥ የደኅንነት ዲፓርትመንት እና ፒው የተሰኘው ተቋም የሠሩት ጥናት ያሳያል። ይህ አሀዝ ከአውሮፓውያኑ 2005 ጀምሮ ብዙም እንዳልተቀየረ ማሳያ ነው።

አብዛኞቹ እነዚህ ስደተኞች ለረዥም ዘመናት በአሜሪካ ውስጥ የኖሩ ናቸው። ወደ አራት አምስተኛ የሚጠጉት በአገሪቱ ውስጥ ቢያንስ ከአስር ዓመታት በላይ ቆይተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሜሪካ ሕግ መሠረት ሰነድ አልባ ስደተኞች ከመባረራቸው በፊት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት መሰማትን ጨምሮ ሌሎች ፍትህን የማግኘት መብቶች አላቸው።

በከፍተኛ ቁጥር ስደተኞችን ማባረር በኢሚግሬሽን ፍርድ ቤት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ መጨናነቅን የሚፈጥር መሆኑም ይነገራል። በአሜሪካ ውስጥ አብዛኞቹ ስደተኞች የሚባረሩት በኢምግሬሽን እና ጉምሩክ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት (አይሲኢ) ወኪሎች ሳይሆን በተለያዩ ግዛት ባሉ የፀጥታ ኃይሎች ነው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የአሜሪካ ትላልቅ ከተሞች እና ግዛቶች ፖሊሶች ከኢምግሬሽን መሥሪያ ቤቱ (አይሲኢ) ጋር ያለውን ትብብር የሚገድቡ ሕጎችን አውጥተዋል። ለሰነድ አልባ ስደተኞች የተሻለ ሁኔታን ለመፍጠር እነዚህን ሕጎች ባወጡ ከተሞች እና ግዛቶች ላይ የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን እርምጃ እንወስዳለን ብሏል።

በኢምግሬሽን መሥሪያ ቤቱ (አይሲኢ) እና በግዛቶች ባለሥልጣናት መካከል ሊኖር የሚችል ትብብር ስደተኞችን በጅምላ የማባረር ፕሮግራም “ወሳኝ” እንደሆነ በዋሽንግተን መቀመጫውን ያደረገው ኤምፒአይ የተሰኘው የፍልሰት ፖሊሲ ተቋም የፖሊሲ ተንታኝ ካትሊን ቡሽ ጆሴፍ ይናገራሉ።

“ለመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች የፀጥታ ኃይሎች ከተባበሯቸው ሰነድ አልባ ስደተኞችን በየቤቶቻቸው እየሄዱ ከመፈለግ ይልቅ ከእስር ቤት መውሰድ ይቀላቸዋል” ይላሉ።

ተንታኟ ለአብነት ያህል የሚጠቅሱትም የፍሎሪዳ እና የፓልም ቢች ግዛቶች ሰነድ አልባ ስደተኞችን በጅምላ ለማባረር ፖሊሶቻቸውን እንደማያሰማሩ መመሪያዎችን አውጥተዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የትራምፕን ሰነድ አልባ ስደተኞችን በጅምላ የማባረርን ዕቅድ የማይደግፉ በርካታ ግዛቶች ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ሊፈጸም እንደማይችል ማሳያ ነው ይላሉ።

በተጨማሪም ስደተኞችን በጅምላ የማባረር ፕሮግራም ከኢሚግሬሸን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በኩልም በርካታ የሕግ ተግዳሮቶች ሊገጥመው ይችላል።

ስደተኞች እያለቀሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሎጂስቲክ በኩልስ?

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በሕጋዊ መንገድ ስደተኞችን ማባረር ቢችሉ እንኳን ከፍተኛ የሆነ የሎጂስቲክ ችግር ይገጥማቸዋል።

በባይደን አስተዳደር ወቅት ይባረሩ የነበሩ ሰነድ አልባ ስደተኞች በድንበር ላይ በቅርቡ የተያዙ ናቸው።

ሌሎች ከድንበር ከራቁ አካባቢዎች የተባረሩ ስደተኞች ወንጀል የፈጸሙ ወይም የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ተብለው የተፈረጁ ናቸው።

በትራምፕ አስተዳደር ወቅት ከሥራ ቦታዎቻቸው ላይ ተይዘው ሲወሰዱ የነበሩ አወዛጋቢ ማባረሮች ከሦስት ዓመታት በፊት ታግደዋል።

ከድንበር በራቁ አካባቢዎች የተባረሩ ስደተኞች ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት ከ100 ሺህ በታች ሲሆኑ፣ በኦባማ አስተዳደር የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ከ230 ሺህ በላይ ደርሰው ነበር።

“በአንድ ዓመት ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ስደተኞችን ማባረር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እና ሀብት ማፍሰስ የሚያስፈልገው ነው። ይህን ያህል ሀብት ደግሞ የለም” ሲሉ የአሜሪካ የኢሚግሬሽን ምክር ቤት የፖሊሲ ዳይሬክተር አሮይ ሬይችሊን መልኒክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤቱ 20 ሺህ ወኪሎች እና ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች በትራምፕ ዘመቻ የተጠቀሱትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ ስደተኞች ለማግኘት እና ተከታትሎ ለመያየዝ በቂ ናቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ባለሙያዎች ጥርጣሬ አላቸው።

ዳይሬክተሯ ስደተኞችን የማባረር ሥራ ረዥም እና ውስብስብ ነው ይላሉ። ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ከተለዩ እና በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ወደ ኢሚግሬሽን ዳኛ ፊት ከመቅረባቸው በፊት በተመረጡ ቦታዎች መቆየት አለባቸው። የኢሚግሬሽን ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያልሰጠባቸው የዓመታት ጉዳዮችን ከመያዙ ጋር ተያይዞ ሂደቱን የተወሳሰበ አድርጎታል።

ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ነው ስደተኞቹ ከአሜሪካ የሚባረሩት ሆኖም ይህ ሂደት የተቀባይ አገራትን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የሚጠይቅ ነው።

ትራምፕ ስደተኞችን ለማባረር እንዲያግዙ የብሔራዊ ጥበቃውን ወይም የአሜሪካን ጦር አሳትፋለሁ ብለዋል። የአሜሪካ ጦር ከስደተኞች ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ሜክሲኮ ድንበር ላይ ባሉ ተግባራት ላይ ብቻ ተገድቦ ቆይቷል።

ትራምፕ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር ጦሩን ወይም የግዛቶችን የፀጥታ ኃይሎችን ከማሳተፍ በዘለለ ዕቅዱ እንዴት ሊተገበር እንደሚችል ዝርዝሮችን አላቀረቡም። ትራምፕ ከታይም መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አዳዲስ የስደተኞች ማቆያ ስፍራዎችን ሊገነቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ስደተኞችን በማባረር የሚሳተፉ ግዛቶች እና የአካባቢ ፖሊስ መምሪያዎች ማበረታቻዎች እሰጣለሁ ሲሉም ተደምጠዋል።

ቢቢሲ ለተጨማሪ አስተያየት የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድንን አነጋግሯል።

ጥብቅ የኢሚግሬሽን ቁጥጥርን የሚደግፈው ‘ነምበር ዩኤስኤ’ የተባለው የምርምር ተቋም ዳይሬክተር ኤሪክ ሩዋርክ ከድንበር በራቁ የአሜሪካ ግዛቶች አካባቢ ስደተኞችን ከአገር የማባረር ውጤታማ የሚሆነው ድንበርን ከማስከበር ጋር በተቆራኘ መልኩ ሲካሄድ ነው ይላሉ።

ዳይሬክተሩ አክለውም “ሕጋዊ ያልሆኑ ስደተኞችን” በሚቀጥሩ ኩባንያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነም አጽንኦት ይሰጣሉ።

ስደተኞችን የሚያጓጉዝ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የገንዘብ ወጪ እና ፖለቲካዊ ዋጋ

አንድ ሚሊዮን ስደተኞችን ከአገር ለማባረር በአስር ወይም በመቶዎች የሚቆጠር ቢሊዮን ዶላሮችን እንደሚያስወጣ ባለሙያዎች ይገምታሉ።

የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤቱ ባለፈው ዓመት ለትራንስፖርት እና ስደተኞችን ለማባረር ይዞት የነበረው በጀት 420 ሚሊዮን ዶላር ነበር። በዚሁ ዓመት መሥሪያ ቤቱ 140 ሺህ ገደማ ስደተኞችን ከአገር አባሯል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የፍርድ ሂደታቸውን ወይም የሚባረሩበትን ጊዜ ለመጠበቅ በመጠለያዎች መቆየት የሚኖርባቸው ሲሆን፣ የትራምፕ የዘመቻ ቡድን ሁሉም የሚታጎሩበት ትልቅ ካምፕ ለመገንባት ጥሪ እያደረገ ነው።

በተጨማሪ ስደተኞቹን ወደ ሌላ አገራት ለማጓጓዝ የበረራዎችን ቁጥር መጨመር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ምናልባት ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ማሳተፍ ያስፈልጋል ተብሏል። ይሄም ወጪውን በከፍተኛ ሁኔታ ያንረዋል።

በዋሽንግተን የላቲን አሜሪካ የስደት እና የድንበር ባለሙያ የሆኑት አዳም አይሳክሰን ስደተኞችን በጅምላ ማባረር የትራምፕ አስተዳደርን ከሕዝብ ግንኙነት አንፃር ፖለቲካዊ በሆነ መልኩ ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል ይላሉ።

“በአሜሪካ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚያውቃቸው እና የሚወዳቸው ሰዎች በአውቶብሶች በግዳጅ ሲወሰዱ ሊመለከቱ ነው” በማለት በቀሪው ሕዝብ ላይ የሚፈጥረው ስሜት ቀላል እንደማይሆን ይናገራሉ።

አክለውም “በቴሌቪዥን መስኮቶቻችን የሚያለቅሱ ልጆች፣ የሚለያዩ ቤተሰቦችን ስቃይ ልንመለከት ነው። ይህ ሁሉ በማይታመን ሁኔታ መጥፎ ፕሬስ ነው” ይላሉ።

ስደተኞች በጅምላ ተባረው ያውቃሉ?

በትራምፕ አራት ዓመታት አስተዳደር ወቅት ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ከዩናይትድ ስቴትስ ተባረዋል።

የባይደን አስተዳደርም እስከ ዘንድሮው ዓመት የካቲት ወር ድረስ ወደ 1.1 ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን በማባረር ከትራምፕ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አሀዝ አስመዝግቧል።

ባይደን ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩበት በሁለቱ የኦባማ አስተዳደር የሥልጣን ዘመናት ወቅት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ከአገር ተባርረዋል። በዚህም ተሟጋቾች ባራክ ኦቦማን “ዋነኛው አባራሪ” የሚል ስያሜ ሰጥተዋቸው ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1954 እስከ 1.3 ሚሊዮን የሚደርሱ ስደተኞች በማባረር በጅምላ እንዲወጡ ተደርገዋል።

አሀዙ በአንዳንድ ታሪክ ምሁራን አከራካሪ ቢሆንም በወቅቱ ፕሬዚዳንት ድዋይት አይዘንሃወር ተፈጻሚ የሆነው ይህ ፕሮግራም ከፍተኛ የሕዝብ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።

ለዚህም አንዳንድ የአሜሪካ ዜጎች መባረራቸው፣ የገንዘብ እጥረት ጋር ተያይዞ ሲሆን፣ ፕሮግራም በአውሮፓውያኑ 1955 በአብዛኛው እንዲቋረጥ ተደርጓል።