ትራምፕ ምርጫውን ቢያሸንፉ የስደተኞች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር 2017 ዓ.ም. የሚደረገውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን እንደሚያባርሩ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ከ'ታይም' መጽሔት ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በሥልጣን ዘመናቸው ከ15 - 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕገ ወጥ ያሏቸውን ስደተኞችን ከአገር ጠራርገው እንደሚያስወጡ ዝተዋል።
ከመቼው ጊዜ በላይ በስደተኞች እየተጥለቀለቀች ባለችው አሜሪካ የሠነድ አልባ ስደተኞች ጉዳይ የምርጫ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ዘልቋል።
ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ታዲያ፤ በመንግሥት ሥርዓት ላይ ጫና እያሳደሩ እና ለወንጀል መበራከት ምክንያት የሆኑትን ስደተኞች ወደመጡበት አገር በጅምላ እመልሳለሁ ሲሉ በተደጋጋሚ ለደጋፊዎቻቸው ቃል ገብተዋል።
ትራምፕ ይህን ዕቅዳቸውን ለማስፈጸም የአገሪቱ ጦር አካል የሆነው ብሔራዊ ዘብን (ናሽናል ጋርድ) የማሰማራት ዕቅድ እንዳላቸው ጨምር ተናግረዋል።
ትራምፕ እአአ 1954 በ34ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አይዘንአወር አስተዳደር ተግባራዊ ተደርጎ የነበረውን ‘ኦፕሬሽን ዌትባክ’ የተባለውን ዘመቻ እርሳቸውም ሥራ ላይ እንደሚያውሉት ተናግረዋል።
‘ኦፕሬሽን ዌትባክ’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የነበረው ዘመቻ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የጎረቤት አገር ሜክሲኮ ዜጎችን ከአገር ያስጣ ዘመቻ ነበር።
በ2020 በአሜሪካ ከ11 ሚሊዮን የማያንሱ ሠነድ አልባ ስደተኞች እንደሚገኙ የአሜሪካ መንግሥት አሃዝ ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርብ ዓመታት ደግሞ ድንበር ተሻግረው ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከፍ ማለቱን ተከትሎ የሠነድ አልባ ስደተኞች ቁጥር ከፍ ስለማለቱ ይገመታል።
ባለፉት 12 ዓመታት 3.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕገ ወጥ የተባሉ ስደተኞች ከአሜሪካ እንዲባረር ተደርጓል። ከእነዚህም መካከል ደግሞ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት የባራክ ኦባማ አስተዳደር ከአገር ያበረራቸው ስደተኞች ናቸው።
ከእአአ 2012 እስከ 2016 በኦባማ ሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ከአገር እንዲወጡ ተደርገዋል።
ባራክ ኦባማን ተከትሎ ከ2016 እስከ 2020 በዘለቀው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከአሜሪካ የተባረሩ ስደተኞች ቁጥር 1.25 ሚሊዮን ገደማ መሆናቸውን የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት አሃዝ ያሳያል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ አሜሪካ ከሜክሲኮ በምትዋሰንባት የደንበር አካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕገ-ወጥ ስደተኞች ድንበር እያቋረጡ እየገቡ ይገኛሉ።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2023 ብቻ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ለመግባት የሞከሩ 2.5 ሚሊዮን ስደተኞች በሕግ አስከባሪዎች ተይዘዋል።
የባይደን አስተዳደር ስደተኞቹን ወደ አሜሪካ እንዲገቡ እየፈቀደ ይገኛል በሚል ይተቻል።
የትራምፕ የቅስቀሳ ቡድን የጆ ባይደን አስተዳደር “አሜሪካ በስደተኞች እንድትወረር ፈቅዷል” የሚሉ ሲሆን፤ ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈው ሥልጣን ሲይዙ፤ “ስደተኞቹ በአገራችን እንዲቆዩ አይፈቀድላቸውም” ይላሉ።
ዶናልድ ትራምፕ ከታይም ጋር በነበራቸው ቆይታ ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት አገሪቱ ከባድ የፀጥታ ስጋት ባጋጠማት ጊዜ የሚሰማራውን ብሔራዊ ዘብ እንደሚጠቀሙ ገልጸው፤ ነገር ግን ስደተኞችን በእስር ቤት ወይም በስደተኞች ማቆያ ስፍራዎች እንደማያስቀምጡ ተናግረዋል።
ትራምፕ “ከአገር ስለምናስወጣቸው በማቆያ ስፍራዎች ማስገባት አይጠበቅብንም” ብለዋል።
‘በወንጀለኞች ወረራ እየተፈጸመብን ነው’
በቀጣይ ዓመት ለሚደረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የኢሚግሬሽን ጉዳይ ለአሜሪካውያን መሠረታዊ ጉዳይ እየሆነ ነው።
ሲኤንኤን ከሕዝብ የሰበሰበው አስተያየት እንዳመለከተው ከሆነ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙ ድምጽ ሰጪዎች በኢሚግሬሽን ጉዳይ ከጆ ባይደን ይልቅ በዶናልድ ትራምፕ ላይ እንደሚተማመኑ ገልጸዋል።
ዶናልድ ትራምፕም ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የሪፐብሊካን ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲሁ ስደተኛ ጠል የሆነ ንግግራቸውን በማሰማት ለሠነድ አልባ ስደተኞች ወደኋላ እንደማይሉ አረጋግጠዋል።
ትራምፕ በኢሚግሬሽን ዙሪያ ባደረጉት ንግግር በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የጀመሩትን የድንበር ላይ አጥር ግንባታ እንደሚጨርሱ ቃል ከመግባታቸው በተጨማሪ አሜሪካንን ከሜክሲኮ የሚያዋስናትን ድንበር ጠንካራ ጥበቃ ይደረግበታል።
“ወረራ” ባሉት የስደተኞች ፍልሰት ምክንያት በተለይ ጥቁር እና ሂስፓኒክ የሆኑ ስደተኞች አሜሪካውያንን ሥራ እያሳጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“በነገራችን ላይ ሥራውን ማን እየወሰደ እንደሆነ ታውቃለሁች? የሥራ ዕድልን ማን እንደሚነጥቅ ታውቃለችሁ?” ብለው ከጠየቁ በኋላ፤ “ከእነዚህ ሥራዎች 107 በመቶ የሚሆኑት ሥራዎች የሚወሰዱት ሕገ-ወጥ በሆኑት መጤዎች ነው” ብለዋል።
ትራምፕ የፓርቲያቸው ይፋዊ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ መሆናቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር፤ አሜሪካ እየገቡ ያሉት ስደተኞች ከእስር ቤት እና ከአእምሮ ሆስፒታል የወጡ ናቸው ሲሉ መረጃ ላይ ያልተደገፈ አስተያየት ሰጥተዋል።
“አደገኛ ወንጀለኞች ከእስር ቤቶች እና ከአእምሮ ሕክምና ማዕከላት እንዲሁም አሸባሪዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታቅ መጠን እየገቡብን ነው።
“በደቡብ ድንበራችን በኩል ባለው ወረራ ከፍተኛ የሆነ ወንጀል፣ ድህነት፣ በሽታ እና ውድመት ማኅብረሰባችን ላይ ደርሷል” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ስደተኞች ለአሜሪካ ስጋት ናቸው?
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳዎቻቸው ላይ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ በስደተኞች ምክንያት በአሜሪካ የወንጀል መጠን ጨምሯል ይላሉ።
ምንም እንኳ አብዛኞቹ የትራምፕ ወቀሳዎች በመረጃ ያልተደገፉ እና የተጋነኑ ሆነው የሚቀርቡ ቢሆንም፤ ዴሞክራቶች ጨምር የሚስማሙበት ስደተኞች በመንግሥት አገልግሎት ላይ መጨናነቅን መፍጠራቸውን ነው።
በተለይ ከሜክሲኮ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ በአሜሪካ ከተሞች የመንግሥት አገልግሎቶች ላይ ጫና ተፈጥሯል። ባለሥልጣናት ጥገኝነት ጠያቂዎችን መመገብ፣ መጠለያ መስጠት እና ማስተማር ከብዷቸዋል።
ስደተኞችን በከፍተኛ ቁጥር ማስወጣት ምን ይፈጠራል?
ሠነድ አልባ ስደተኞች የመንግሥት ሥርዓት ላይ ጫና ይፈጥራሉ እንዲሁም የደኅንነት ስጋት ናቸው ቢባልም፤ ስደተኞች ለአሜሪካ ምጣኔ ሃብት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ትራምፕ እንደዛቱት ሥልጣን ላይ ወጥተው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከአአሜሪካ የሚያባርሩ ከሆነ የሠራተኛ እጥረት ተፈጥሮ በአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከፍ ሊል ይችላል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የሠራተኛ ቁጥር ሲቀንስ ቀጣሪዎች በከፍተኛ ወጪ ሠራተኛ ለመቅጠር ይገደዳሉ። ከዚህ በተጨማሪ የሠራተኛ ቁጥር መቀነስ የምርት ዋጋ እና ብዛትም ይቀንሳል። ይህም የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል።












