ሐሰተኛ ዶላርን ለመቆጣጠር ተቋቁሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶችን ወደ መጠበቅ የተሸጋገረው ሴክሬት ሰርቪስ

የሴክሬት ሰርቪስ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ ቡድን (ሴክሬት ሰርቪስ) ተልዕኮው አንድ ነው። ይህም በፕሬዝዳንቱ እና በሚተኮስባቸው ጥይት መካከል ዘሎ መግባት።

እነዚህ የፕሬዝዳንታዊው ጥበቃ አባላት ብዙውን ጊዜ በፕሬዝዳንቶች ዙሪያ ፊታቸውን ቅጭም አድርገው ጥቁር መነጽር እና ጥቁር ሱፍ ለብሰው አካባቢውን በትኩረት ሲቃኙ ይታያሉ።

የአሜሪካ ሴክሬት ሰርቪስ አባላት ፕሬዝዳንቶችን፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶችን እና ዕጩ ፕሬዝዳንቶችን በመጠበቅ የሚታወቁ ሲሆን፣ የሚጠብቁትን ግለሰብ ደኅንነት በማረጋገጥም ትልቅ ስም አላቸው።

ባለፈው ሳምንት ግን የሚጠበቅባቸውን ፈተና ወድቀዋል። የቀድሞው ፕሬዝዳንት የአሁኑ ዕጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ከ150 ሜትር ርቀት ላይ ጥይት ተተኩሶባቸው። ትራምፕ የዕጣ ፈንታ ነገር ሆኖ እንጂ የሴክሬት ሰርቪስ አባላቱ ከዚያ ጥይት አላዳኗቸውም።

የጥይት እሩምታ ከተሰማ በኋላ ግን የሴክሬት ሰርቪስ አባላት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ከሚተኮሰው ጥይት በሰውነታቸው ለመከላከል አላቅማሙም። በፍጥነት ወደ መድረኩ ወጥተው ከበቧቸው።

ተኳሹ ስጋት አለመሆኑን እንዳረጋገጡ በፍጥነት ዕጩ ፕሬዝዳንቱን ወደ ሕክምና ይዘው በመሄድ ኃላፊነታቸው ተወጡ።

ሐሰተኛ ዶላርን መቆጣጠር

የሴክሬት ሰርቪስ ቡድን ከ150 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 1865 ላይ ሲመሠረት ዓላማው እጅግ በጣም አስፈላጊ ሰዎችን እንዲጠብቅ አልነበረም።

ቡድኑ ቀድሞ የተቋቋመው በእርስ በርስ ጦርነት በወደመችው አገር የሐሰተኛ ገንዘብ ሥርጭትን እንዲቆጣጠር ነበር።

የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲያበቃ በአዲሷ አሜሪካ ከሚሠራጨው ሦስት የገንዘብ ኖት አንዱ ሐሰተኛ እንደሆነ ይታመን ነበር።

ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው የሐሰተኛ የገንዘብ ዝውውር የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ሆነ።

የአገሪቱ ግምጃ ቤት ይህን ስጋት ለመቀልበስ “ሴክሬት ሰርቪስ” (ምሥጢራዊ አግልግሎት) የተባለ ድብቅ የደኅንነት ቡድን አቋቋመ።

በጊዜ ሂደት ይህ ክፍል ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ከኢኮኖሚው በማስወገድ ስኬት ማስመዝገቡን ተከትሎ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር የሚገቡ ቁሶች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጠው።

ይሁን እንጂ የፕሬዝዳንት ዊሊያም ማክኪንለይ ግድያን ተከትሎ የሴክሬት ሰርቪስ ተልዕኮ አቅጣጫውን ቀየረ።

አንድ የሴክሬት ሰርቪስ ቡድን አባል ከፕሬዝዳንቱ መኪና ጎን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የሴክሬት ሰርቪስ አዲስ ኃላፊነት

እአአ 1901 ላይ ሊዮን ክዞለጎስዝ 25ኛውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ማክኪንለይ ሰላምታ ለመቅረብ በትዕግስ እየተጠባበቀ ነበር።

ከረዥም ሰልፍ በኋላ ተራው ሲደርሰው ሊዮን ለፕሬዝዳንቱ ሰላምታ ለማቅረብ እጁን ሳይሆን የዘረጋው ደብቆት የቆየውን ጦር መሳሪያ ነበር የመዘዘው።

ፕሬዝዳንቱን ሁለት ጊዜ ሆዳቸው ላይ በጥይት መታ። ፕሬዝዳንቱ ክፉኛ ቆስለው በቀናት ልዩነት ሕይወታቸው አለፈ።

ከዚህ ክስተት በኋላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ለእነርሱ ብቻ የተመደበ የጥበቃ ቡድን ያስፈልጋቸዋል ተባለ። ከዚያም ሴክሬት ሰርቪስ ፕሬዝዳንቶችን፣ የፕሬዝዳንት ቤተሰቦችን እና ለጉብኝት ወደ አሜሪካ የሚገቡ የውጭ አገራት መሪዎችን እንዲጠብቅ ኃላፊነት ተሰጠው።

ከሴክሬት ሰርቪስ በፊት ለፕሬዝዳንቱ ጥበቃ ያደርጉ የነበሩት ዋይት ሐውስን የሚጠብቁ የግል ጠባቂዎች ነበሩ።

ሩዝቬልት በሲመተ በዓላቸው ዕለት በምሥጢር አገልግሎት አባላት ታጅበው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቴዎዶር ሩዝቬልት በሴክሬት ሰርቪስ በመጠበቅ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ናቸው። ይህ ፎቶም በ1905 ሩዝቬልት በሲመተ በዓላቸው ዕለት በምሥጢር አገልግሎት አባላት ታጅበው

ጥበቃ የሚያደርገው ለማን ነው?

ሴክሬት ሰርቪስ በሥልጣን ላይ ያሉ ፕሬዝዳንቶች፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እና የትዳር አጋሮቻቸውን እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆቻቸውን ይጠብቃል።

ከዚህ በተጨማሪም ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት የአሜሪካ ምድርን የሚረግጡ የውጭ አገር ባለሥልጣናትም ጥበቃው አይለያቸውም።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 120 ቀናት ሲቀሩት ጀምሮ ለዋነኛ ዕጩዎች ሴክሬት ሰርቪሱ የጥበቃ አገለግሎት ይሰጣቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሴክሬት ሰርቪስ ከእአአ 1998 ጀምሮ የወንጀለኞች ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ዝግጅቶችን ደኅንነት የማስጠብቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል።

ዝግጅቶቹ የፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የፕሬዝዳንት በዕለ ሲመት፣ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች፣ ብሔራዊ የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን እንዲሁም ስፖርታዊ ሁነቶችን ሊጨምር ይችላል።

ይህ መንግሥታዊ የደኅንነት አገልግሎት ባለፉት 125 ዓመታት ታሪኩ አቅሙን በገንዘብ እና በሰው ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ አጠናክሯል።

በአሜሪካ ውስጥ እና በውጭ አገራት የተሰማሩ ከሰባት ሺህ በላይ ባልደረቦት አሉት።

በ1981 ሮናልድ ሬገን ላይ የግድያ ሙከራ ሲደረግ የሴከሬት ሰርቪስ አባላት አና ፖሊሶች ፐሬዝዳንቱን ለመከላከል ሲጥሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ1981 ሮናልድ ሬገን ላይ የግድያ ሙከራ ሲደረግ የሴከሬት ሰርቪስ አባላት አና ፖሊሶች ፐሬዝዳንቱን ለመከላከል ሲጥሩ

የፕሬዝዳንቶች ተባባሪ አለመሆን

ይሁን እንጂ የኤጀንሲው ሥራ ፈተና አልተለየውም። የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች ከሚገጥሟቸው ፈተናዎች መካከል የሚጠብቋቸው ሰዎች ትብብርን አለማግኘት አንዱ ነው።

አንዳንድ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ለደኅንነታቸው ሲባል ከሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች ጋር ለመተባበር ፍላጎት ሳያሳዩ የሚቀሩባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው።

በተገደሉት ዊሊያም ማክኪንለይ የተተኩት ፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት በሴክሬት ሰርቪስ አባላት ጥበቃ እና ክትትል ይሰላቹ እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።

እንደ ዋይት ሐውስ ሂስቶሪካል አሶሲዬሽን ከሆነ ከአጠገባቸው በማይለዩ የሴክሬት ሰርቪስ አባላት የተሰላቹት ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ከዋይት ሐውስ ተደብቀው ወጥተው በመናፈሻ ስፍራ ብቻቸውን የእግር ጉዞ ያደርጉ ነበር።

በፕሬዝዳንት ሩዝቬልት የተተኩት ዊሊያም ሃርድ ታፍት እንዲሁም በአንድ የገና በዓል ዋዜማ ከባለቤታቸው ጋር ከዋይት ሐውስ ተደብቀው ወጥተው ከጓደኞቻቸው ጋር የበዓል ጊዜን አሳልፈዋል።

ሴክሬት ሰርቪስ ከሚለይባቸው ነገሮች መካከል ለሚጠብቃቸው ፕሬዝዳንቶች የሚሰጣቸው ምሥጢራዊ ስያሜ ነው።

ቢል ክሊንተር መጠሪያቸው ‘ኢግል’ የነበር ሲሆን ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ‘ትሬልብሌዘር’፣ ባራክ ኦባማ ‘ሪነጌድ’፣ ዶናልድ ትራምፕ ‘ሞጉል’ እንዲሁም ጆ ባይደን ‘ሴልቲክ’ የሚል መጠሪያ አላቸው።

ኬኔዲ ተተኩሶባቸው በተገደሉበት ወቅት በመኪናቸው ውስጥ የሴክሬት ሰርቪስ አባል አብሯቸው ነበረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኬኔዲ ተተኩሶባቸው በተገደሉበት ወቅት በመኪናቸው ውስጥ የሴክሬት ሰርቪስ አባል አብሯቸው ነበረ

ግድያዎች እና የገጠሙት ቅሌቶች

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምንም እንኳ ሴክሬት ሰርቪስ ጥሩ ስም ቢኖረውም በታሪኩ ትልቅ ክፍተት የፈጠሩ ጥቁር ጠባሳዎች አልጠፉም።

ለዚህ ደግሞ ማሳያው እአአ 1963 የፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኒዲ ግድያ ነው።

ይህን ክስተት ተከትሎ ኤጀንሲው የጆን ኤፍ ኬኔዲ ባለቤት እና ልጆች የሕይወት ዘመን ጥበቃ እንዲያደርግ ተወስኗል።

በ1950 ዎቹ አጋማሽ ሁለት የፖርቶ ሪኮ ግዛት ነዋሪዎች ፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማንን ለመግደል ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

ሁለቱ ጥቃት ፈጻሚዎች ፕሬዝዳንቱን መምታት ባይችሉም የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረባ የሆነውን ሌይሊ ኮፍለትን በሦስት ጥይት መትተውታል። የኤጀንሲው ባልደረባም ምንም እንኳ በጥይት ቢመታም አንዱን ጥቃት ፈጻሚ ጭንቅላቱን በጥይት መትቶ ገድሏል።

ሌይሊ ኮፍለት ከጥቃቱ በኋላ ሕይወቱ አልፏል። እስካሁንም በፕሬዝዳንታዊ ጥበቃ አባል ላይ የተገደለ ብቻው የኤጀንሲው ባልደረባ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።

እአአ 1981 ላይም ሴክሬት ሰርቪስ ለወቅቱ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን ጥበቃ እያደረገ፤ በፕሬዝዳንቱ ላይ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞ ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ከአንድ ሆቴል እየወጡ ሳለ በከባዱ የታጠቀ ግለሰብ በፕሬዝዳንቱ፣ በፕሬስ ሴክሬታሪው፣ በሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች እና በፖሊስ ላይ ተኩስ ከፈተ።

ፕሬዝዳንት ሬጋን ሳንባቸውን በጥይት ተመትተው ነበር። ይሁን እንጂ ከጉዳታቸው ማገገም ችለዋል። ጥቃቱ ሲፈጸም በተኳሹ ጥይት እና በፕሬዝዳንቱ መካከል ዘሎ የገባው ጆን ሂንክሊይ እንዲሁ በጥይት ተመትቶ ከጉዳቱ አገግሟል።

ፕሬዝዳንት ሬጋን ላይ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራን ተከትሎ ኤጀንሲው ማሻሻያ አደረገ። ኤጀንሲው ማስፋፊያ ተደረገለት። ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንም ለሥራው መጠቀም ጀመረ።

እአአ 2012 ላይ በፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመን ኤጀንሲው በከፍተኛ ቅሌት ስሙ በክፉ ተነሳ።

ከዴሞክራቲክ ፓርቲ ብሔራዊ ጉባኤ በፊት በነበረ ምሽት የኤጀንሲው ባልደረቦች መጠጥ ጠጥተው ሲሰክሩ እና ዝሙት ሲፈጽሙ ማደራቸው ከፍተኛ የሥነ ምግባር ጥሰት ከመሆኑም በላይ የደኅንነት ክፍተት የሚፈጥር ስህተት ነው ተባለ።

ፕሬዝዳንት ኦባማ በጉኤው ለመሳተፍ በስፍራው ከመድረሳቸው ከጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ የኤጀንሲው ባልደረቦች በርካታ ሴተኛ አዳሪዎችን ወደ ክፍሎቻቸው አስገብተው እንደነበር የሚዲያ ዘገባ አጋልጦ ነበር።

ይህን ተከትሎ የወቅቱ የኤጅንሲው ኃላፊ የነበሩት ማርክ ሱሊቫን ሥልጣናቸውን ለቀቁ።

ትራምፕ ጥቃት ከተፈጸመባቸው በኋላ በሴክሬት ሰርቪስ አባላት ታጅበው ከመድረክ ሲወርዱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕን ከጥቃት አልጠበቃቸውም በሚል የሚወቀሱት የሴክሬት ሰርቪስ ቡድኑ መሪ ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ነው

ትራምፕን ከጥቃት መጠበቅ አልቻሉም?

ባለፈው ሳምንት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስሰቀሳ ላይ ሳሉ አንድ የታጠቀ ግለሰብ ጣራ ላይ ወጥቶ ትራምፕ ላይ መተኮሱ በርካቶች በሴክሬት ሰርቪስ አገልግሎት ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።

የቀድሞው የፌደራል መንግሥቱ ልዩ ኃይል እንዲሁም የአሜሪካ የባሕር ኃይል አባል የነበረው ጆናታን ጊሊያም፤ በፔንስልቬኒያ ያጋጠመው “የሴክሬት ሰርቪስ ውድቀትን ያሳያል” ይላል።

ጆናታን ጊሊያም ለቢቢሲ ሲያስረዳ፤ በሴክሬት ሰርቪስ አሠራር መሠረት የምርጫ ቅስቀሳው ከመደረጉ ከአንድ ሳምንት በፊት የአካባቢ ቅኝት በማድረግ ጥበቃ የሚያደርጉ የሚሰማሩበት ቦታን በመለየት የሚጠብቁትን ሰው ደኅንነት እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል ይለያል ይላል።

እንደ እርሱ ከሆነ የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች ተኳሹ የወጣበትን ሕንጻ ቀድመው መፈተሽ ነበረባቸው።

በእርግጥ ዘግይቶ የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በዕለቱ የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች ጥቃት ፈጻሚው ትራምፕ ላይ መተኮስ ከመጀመሩ ከአንድ ሰዓት በፊት ጠርጥረውን ሊይዙት ቢሞክሩም በሰዎች መካከል ተቀላቅሎ ሊይዙት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተኳሹ ጥቃቱን ከመክፈቱ ከ20 ደቂቃዎች በፊት በጣራው ላይ ታይቶ የነበረ ቢሆንም የሴክሬት ሰርቪስ ባልደረቦች እርምጃ ሳይወስዱ ረዥም ጊዜ ወስዶባቸዋል።

የበትለር ከተማ ኃላፊ የሆኑት ቶም ናይትስ ደግሞ ለሲቢኤስ ሲናገሩ ጥቃት ፈጻሚው ከመተኮሱ ከሰከንዶች በፊት ከከተማዋ ፖሊስ አባል ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጦ ነበር ብለዋል።

የፖሊስ አባሉ አንድ አጠራጣሪ ግለሰብ ጣራ ላይ እንዳለ ተነግሮት እርሱን ፍለጋ በሌላ የፖሊስ ባልደረባ ድጋፍ ጣራ ላይ ወጣ።

የፖሊስ አባሉ ጣራ ላይ እንደወጣ ጥቃት የከፈተው ቶማስ ማቲው ክሩክስ መሳሪያውን የፖሊስ አባሉ ላይ አነጣጠረ። ከዚያም የፖሊስ አባሉ በደረቱ እንዲተኛ አስገደደው። በመቀጠል ክሩክስ መሳሪያውን ወደ ትራምፕ አዙሮ ቃታውን ሳበ።

ክሩክስ ወደ ትራምፕ ከተኮሰ ከ26 ሰከንዶች በኋላ በሴክሬት ሰርቪስ አልሞ ተኳሽ ተገድሏል።

ከዚህ ክስተት በኋላ የሴክሬት ሰርቪስ ዳይሬክተር ኪምበርሊ ቻተል ሥራቸውን እንዲለቁ ጫና እየተደረገባቸው ነው። እርሳቸው ግን ኤጀንሲው ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ቢሉም ከሥልጣናቸው ግን እንደማይለቁ ለኤቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሯ ከቀናት በኋላ ክስተቱን በተመለከተ ከአገሪቱ ምክር ቤት አባላት ፊት ቀርበው ለተነሱላቸው ጥያቄዎች መልስ የሰጡ ሲሆን፣ በትራምፕ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ምክንያት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ በርካታ የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል።