ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገው ወጣት እንዴት ከፀጥታ ኃይሎች ዕይታ ሊሰወር ቻለ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንዴት ሆኖ ነው በርካታ ፖሊስ እና የደኅንነት አባላት ባለቡት ወጣት ተጠርጣሪ አልፎ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረሰው? የሚለው ጥያቄ አሁንም በበርካቶች ዘንድ አለ።
በአሜሪካዋ ፔንሲልቬኒያ ግዛት በትለር ክፍለ-ግዛት ነበር ባለፈው ቅዳሜ ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ያደረጉት። ቅስቀሳ ክፍት ሥፍራ ላይ ነው የተደረገው።
ቶማስ ማቲው ክሩክስ፤ ትራምፕ አትሮኖሳቸውን ተጠግተው ከቆሙበት መድረክ 130 ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ጣሪያ ነው አነጣጥሮ የተኮሰባቸው።
የዩናይትድ ስቴትስ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ከግድያ ሙከራው በኋላ በሰጠው አስተያየት ሕንፃው በአካባቢው ፖሊስ እንዲጠበቅ አደራ ብሎ እንደነበር አሳውቋል።
ትራምፕ የተተኮሰባቸው ጥይት ጆሯቸውን ጨርፎ ሲያልፍ ከታዳሚዎች መካከል አንድ ሰው ተገድሏል፤ ሁለት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ተጎድተው የሕክምና ዕርዳታ በማግኘት ላይ ይገኛሉ።
የደኅንነቱ ቃል አቀባይ አንተኒ ጉግሊየልሚ እንደሚሉት የአካባቢው ፖሊስ እርዳታ እንደሚያደርግላቸው ተማምነው ነበር።
ቃል አቀባዩ አክለው በሰጡት መግለጫ የደኅንነቱ ሠራተኞች ቅስቀሳው የሚደረግበትን የውስጠኛውን እንዲጠብቁ፤ የአካባቢው ፖሊስ ደግሞ ተኳሹ የተጠቀመበትን ሕንፃ ጨምሮ የውጭኛውን ክፍል እንዲጠብቁ ነበር ኃላፊነት የተሰጣቸው።
የአካባቢው ፖሊስ ዲፓርትመንት ከቢቢሲ የቀረበለትን ጥያቄ ለግዛቱ ፖሊስ ፅህፈት ቤት የመራ ሲሆን የግዛቲቱ ፖሊስ ደግሞ ሕንፃውን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳልተሰጠው ተናግሯል።
የግዛቲቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ያቀረበውን “የሰውና ቁሳቁስ ኃይል” ጥያቄ በማፅደቅ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ ፖሊሶችን መድበዋል።
በርካታ ታዛቢዎች እንዴት የፀጥታ ኃይሎች እያሉ ታጣቂው ጣራ ላይ ወጥቶ ዶናልድ ትራምፕ ላይ አነጣጥሮ መተኮስ ቻለ ሲሉ ይጠይቃሉ።
የቅስቀሳው ታዳሚዎች እንደሚሉት ተጠርጣሪው ከመተኮሱ ከደቂቃዎች በፊት ጣራ እያለ ተመልክተውት ነበር። የበትለር ክፍለ ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ማይክል ስሉፕ ደግሞ አንድ የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ሰውየውን ቢመለከተውም ሊያስቆመው እንዳልቻለ ተናግረዋል።
የፖሊስ ኃላፊው አካባቢውን በመጠበቅ በኩል “ጥፋት ተሠርቷል” ብለው ቢያምኑም ነገር ግን ማንም ሰው ተጠያቂ ሊሆን አይገባም ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት መሰል ቅስቀሳዎች ሲኖሩ የአካባቢውን ፖሊስ እርዳታ መጠየቁ የተለመደ ነው ይላሉ ሴኪዩር ኢንቫይሮመንትስ የተሰኘ አማካሪ ድርጅት ያላቸው፤ እንዲሁም ከአውሮፓውያኑ 2002-2010 የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ጭምር የደኅንነት ኃይል ሆነው ያገለገሉት ጄሰን ረስል።
“የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ በፈለገው ቦታ ሁሉ የሚያሰማራቸው በቂ ጠባቂዎች አሉት ማለት አይደለም” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ባለሙያው እንደሚያስረዱት የደኅንነት ሠራተኞች የምርጫ ቅስቀሳ ከመካሄዱ ከቀናት በፊት ወደሥፍራው መጥተው ፍተሻ ያደርጋሉ፤ ከአካበቢው ፖሊሶች ጋር ይመክራሉ።
በትራምፕ ጉዳይ የግድያ ሙከራ ያደረገው ግለሰብ የተጠቀመበት ሕንፃ የምርጫ ቅስቀሳ ከሚካሄድበት ውጭ በመሆኑ ኃላፊነቱ የሚወድቀው የአካባቢው ፖሊስ ላይ ነው ይላሉ።
አክለው እንደሚያስረዱት እንዲህ ባሉ ቅስቀሳዎች ላይ መረጃ ለሁሉም አካላት መሰራጨት አለበት። ነገር ግን መረጃው በሚሰራጭበት “10 ሰከንድ ውስጥ” ታጣቂው ደጋግሞ የመተኮስ ዕድል ሊያገኝ ይችላል።
ኤንቢሲ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ከሁለት የደኅንነት መሥሪያ ቤት ምንጮቹ እንዳጣራው ተኳሹ የተጠቀመበት ሕንፃ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ጥርጣሬ ነበር።
ረስል እንደሚሉት የደኅንነት ሠራተኞች ይህ ሕንፃ አደጋ ሊያመጣ ይችላል ብለው ጠርጥረው ለአካባቢው ፖሊስ አሳውቀው ሊሆን ይችላል፤ ፖሊስ ደግሞ ሕንፃውን መጠበቅ ነበረበት።
“ለምን እንደሆነ አላውቅም ግን ይህ ተግባራዊ አልሆነም” ይላሉ።
የአሜሪካ ወታደር ሆኖ ለ21 ዓመታት ያገለገለው ቶማስ ግሊሰን የተባለ የዓይን እማኝ “ከርቀት ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎች ለመከላከል ጠንከር ያለ ጥበቃ ያስፈልግ ነበር” ይላል።
“የሆነ ሰው ራቅ ካለ ሥፍራ አነጣጥሮ ተኮሱ [ትራምፕን] መግደል ከፈለገ፤ ይህ ሕንፃ በጣም ወሳኝ ሥፍራ ነው” ይላል።
ኤፍቢአይ ከግድያ ሙከራው በኋላ ጉዳዩን ተረክቦ ምርመራ ማድረግ የጀመረ ሲሆን የላይኛው እና ታችኛው የአሜሪካ ምክር ቤትም የተለያዩ ምርመራዎች ከፍተዋል።
የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር አሌሃንድሮ ማዮርካስ ክስተቱን የደኅንነት “ውድቀት” ሲሉ የኮነኑት ሲሆን “መሰል ክስተት ድጋሚ ሊታይ አይገባም” በማለት ለሲኤንኤን ተናግረዋል።
የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ዳይሬክተር ኪምበርሊ ቺትል ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለቻ መሥሪያ ቤታቸው ከፌዴራል እና ከአካባቢው ፖሊስ ጋር በመተባበር “ምን ተፈጠረ? እንዴት ሊሆን ቻለ? ድጋሚስ እንዳይከሰት ምን ማድረግ አለብን?” በሚሉት ጉዳዮች ላይ እየሠሩ እንደሆነ አሳውቀዋል።
ዳይሬክተሯ አክለው የቀድሞው ፕሬዝደንት ላይ የደረሰውን የግድያ ሙከራ በተመለከተ ከኮንግረሱ መርማሪዎች ጋር እየተባበሩ እንደሆነ ገልጠዋል።
ቺትል ከሳምንት በኋላ የተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከተወካዮች ለሚሰነዘሩላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ።












