ትራምፕ ከምሥጢራዊ ሰነዶች ጋር በተያያዘ የቀረበባቸው ክስ ውድቅ ተደረገ

የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Pool

የዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ ቢሮ ምሥጢራዊ ሰነዶችን በተመለከተ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የከፈተውን ክስ የፍሎሪዳ ዳኛ ውድቅ አደረጉ።

ይህም ከቀናት በፊት የግድያ ሙከራ ለተደረገባቸው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትልቅ ድል ተደርጎ ተቆጥሯል።

የፍትህ ቢሮው ልዩ ዐቃቤ ሕግ አድርጎ ጃክ ስሚዝ የሾመበት መንገድ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት የሚጥስ መሆኑን በመጥቀስ የፍርድ ቤቱ ዳኛ አይሊን ካነን ትራምፕ ጉዳዩ ውድቅ እንዲደረግላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብለዋል።

ትራምፕ የአገሪቱ መከላከያ መረጃዎችን ሆን ብሎ መያዝን ጨምሮ ከምሥጢራዊ ሰነዶች አያያዝ ጋር በተገናኘ የተመሰረቱባቸውን በርካታ ክሶች ጥፋተኛ አይደለሁም ብለዋል።

የዐቃቤ ሕግ ጃክ ስሚዝ ቃል አቀባይ የፍትህ ቢሮው ይግባኝ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ትራምፕ እአአ በ2021 ከዋይት ሐውስ ከለቀቁ በኋላ በፍሎሪዳ በሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው መታጠቢያ እና ማከማቻ ክፍሎችን ጨምሮ በርካታ ምሥጢራዊ ፋይሎችን ያላአግባብ ይዘው ተገኝተዋል።

“ፍርድ ቤቱ በዚህ ጉዳይ ስሚዝ የተሾሙበት መንገድ ሁለት ሕገ መንግሥታዊ መሠረቶችን የሚጣረሱ ናቸው” ሲሉ ዳኛ ካነን ውሳኔውን በሰጡበት ባለ 93 ገጽ ትዕዛዝ ላይ አስፍረዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ምሥጢራዊ ሰነዶችን አላግባብ በመያዝ በርካታ የወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በቀረቡባቸው 37 ክሶች መሠረት ትራምፕ ፋይሎቹን በፍሎሪዳ መኖሪያ ቤታቸው ከማስቀመጥ ባለፈ መርማሪዎችን ዋሽተዋል ተብለዋል። በሰነዶቹ አያያዝ ዙሪያ የሚደረገውን ምርመራ ለማደናቀፍም ሞክረዋል ተብሏል።

የቀድሞ ረዳታቸው ዋልት ናውታ እና የቀድሞ ሠራተኛቸው ካርሎስ ዴ ኦሊቬራ ጋር አብረዋቸው ቢከሰሱም ሁሉም ጥፋተኛ አለመሆናቸው ገልጸዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ በ2002 ነበር ስሚዝ ከቀድሞው ፕሬዝደንት ጋር የተያያዙ ሁለት የፌዴራል ምርመራዎችን እንዲመሩ የሾሟቸው።

ዳኛ ካነን በውሳኔያቸው የሚመለከተው ይህንን ጉዳይ ነው እንጂ የ2020 ምርጫን ለመቀልበስ የተደረገውን ጥረት በሚመለከት ​​ስሚዝ የሚመሩት ሁለተኛው ጉዳይ አይደለም።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጠበቆች ጉዳዩን ውድቅ ለማድረግ ተመሳሳይ ጥያቄ አላቀረቡም ተብሏል።

በትራምፕ የተሾሙት የፍሎሪዳ ዳኛ ከፌደራል ሰነዶች ጋር በተያያዘ ቀድሞው ፕሬዝዳንት ሊመልሷቸው የሚገቡ ጉልህ ጥያቄዎች አሉ በማለት የፌደራል ምሥጢራዊ ሰነዶችን ጉዳይ ላልተወሰነ ጊዜ አራዝመዋል።

የሕግ ባለሙያዎች ስሚዝ ያቀረቡትን የሁለቱን የፌዴራል የወንጀል ጉዳዮች ጥንካሬ እና ድክመት በማንሳት ተከራክረዋል።

ሰኞ ዕለት ዳኛ ካነን ጣልቃ ገብተው ዝርዝሮቹ ምንም ለውጥ አያመጡም ሲሉ ተናግረዋል።

የልዩ አማካሪዎች የተሾሙበት እና ገንዘብ ያገኙበት መንገድ ብቻ የአሜሪካን ሕገ መንግሥት ይጥሳል ብለዋል።

የዳኛ ካነን ውሳኔ በልዩ ሁኔታ የተሾሙ ዐቃብያነ ሕጎችን በተመለከተ ሌሎች የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ተቃርነዋል።

በዶናልድ ትራምፕ መታጠቢያ ቤት የተጠራቀሙ ሰነዶች

የፎቶው ባለመብት, US District Court Southern District Of Florida Handout

በአንዳንድ ወግ አጥባቂ የሕግ ምሁራን እና በተለይም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ክላረንስ ቶማስ በቅርቡ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በተላለፈው ፕሬዝዳንታዊ ያለመከሰስ ጉዳይ ላይ ካቀረቡት ንድፈ ሃሳቦች የተወሰደ ነው።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ ትራምፕን ጨምሮ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች “በኦፊሴላዊ ድርጊቶች" በወንጀል ከመከሰስ ነፃ መሆናቸውን ተናግሯል።

ዳኛ ካነን በውሳኔያቸው ሦስት ጊዜ ልዩ አማካሪ ለመሰየም ሕጋዊ መሠረት አለ ወይ? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

የቀድሞው የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ነአማ ራህማኒ ሰኞ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የዳኛ ካነንን ውሳኔ “የሚያስደንቅ ነው” ብለዋል።

ዳኛ ካነን ውሳኔያቸው በዚህ ላይ ብቻ ያተኮረ እንደሆነ ቢናገሩም፤ ራህማኒ ደግሞ ይህ ውሳኔ በሌሎች ጉዳዮች ላይም ልዩ አማካሪዎች መሾም ላይ ጥርጣሬን ይፈጥራል ብለዋል።

ይህ በልዩ አማካሪ የተመረመረውን እና ባለፈው ወር ሕገወጥ ጠመንጃ የመያዝ ክስ የተፈረደበት የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ልጅ ሃንተር ባይደን ጉዳይን ያጠቃልላል።

ዋናው ልዩነት በሃንተር ጉዳይ ላይ ልዩ አማካሪ ዴቪድ ዌይስ የተሾሙት በዴላዌር ተወካይ ሲሆን ጠበቃ ስሚዝ ደግሞ ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ በፕሬዚዳንቱ ተመርጠው በሴኔት ይሁንታ ያገኙ ናቸው።

ስሚዝ ይግባኝ ከማለት በተጨማሪ በጉዳዩ ላይ አዲስ ዳኛ እንዲሾምላቸው መጠየቅ ይችላሉ።